ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

የመጨረሻው ፅሁፋችን በሳምንቱ የታዘብናቸው ሌሎች ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ተዳሰውበታል።

👉 ፍትጊያዎች የበዙበት የመከላከያ እና የሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ

በጨዋታ ሳምንቱ ከተካሄዱት ጨዋታዎች መካከል መከላከያን ከሀዲያ ሆሳዕና ያገናኘው እና በሀዲያ ሆሳዕናዎች 2-0 አሸናፊነት የተጠናቀቀው ጨዋታ በርከት ያሉ አካላዊ ፍትጊያዎች የበዙበት ጨዋታ ነበር።

በሁለቱም ቡድኖች በኩል በድምሩ አራት ተጫዋቾች በጉዳት ተቀይረው ከሜዳ ለመውጣት የተገደዱ ሲሆን በጨዋታ እንቅስቃሴ ወቅት በርከት ያሉ የኃይል አጨዋወቶችንም የተመለከትንበት ነበር።

በሀዲያ ሆሳዕናዎች በኩል የመስመር ተመላላሹ ብርሃኑ በቀለ እና አማካዩ ኤፍሬም ዘካርያስ በሁለተኛው አጋማሽ በኤልያስ አታሮ እና በፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን በጉዳት መነሻነት ተቀይረው የወጡ ሲሆን በመከላከያ በኩል ተከላካዩ ገናናው ረጋሳ እና የመስመር አስትቂው ኤርሜሚስ ኃይሉ እንዲሁ ባጋጠማቸው ጉዳት መነሻነት በኢብራሂም ሁሴን እና በዮሐንስ መንግሥቱ ተቀይረው ወጥተዋል።

👉 የአንጋፋው ክለብ ምስረታ መከበር ጀምሯል

በታህሳስ ወር 1928 በሁለቱ ጓደኛሞች አየለ አትናሽ እና ጆርጅ ሉካስ አራዳ ጊዮርጊስ አካባቢ ምስረታውን ያደረገው አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ 86ኛ የምስረታ ዓመቱ እየተዘከረ ይገኛል።

ይህንንም በማሰብ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ቡድናቸው ከአዳማ ከተማ ጋር ያደረገውን ጨዋታ በሜዳ ተገኝተው የታደሙት የክለቡ ደጋፊዎች ይህን በሚገልፅ መልኩ በ8 እና በ6 ቁጥር ቅርፅ የተሰሩ በአየር የሚሞሉ ፕላስቲኮችን ይዘው ተመልክተናል።

👉 የምሽት ጨዋታዎች ጉዳይ

የምሽት ጨዋታዎች ዳግም ወደ ሊጋችን መመለሱን ተከትሎ በንፅፅር የተሻሉ ፉክክሮችን በምሽቱ ጨዋታ እየተመለከትን እንገኛለን።

ቀትር ላይ የሚደረጉ ጨዋታዎች በሀዋሳ ከተማ ካለው ሞቃታማ የአየር ንብረት ጋር በተያያዘ አሰልቺ ይዘት ያላቸው ጨዋታዎችን ብንመለከትም የምሽት ጨዋታዎች ላይ የአየር ንብረቱ ቀዝቃዛ በመሆኑ ይመስላል የሜዳ ላይ ፉክክሩ ከፍ ብሎ ይታያል።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት እንኳን የተሻለ የሜዳ ላይ ፉክክር የተመለከትንባቸው ጨዋታዎች በሙሉ በሚያስብል መልኩ አመሻሽ አስራ ሁለት ሰአት ላይ የጀመሩት ጨዋታዎች ላይ ነበር። በቀጣይም ሁኔታዎች የሚፈቅዱ ከሆነ ሁኔታዎችን በደንብ በማጤን ጨዋታዎችን ከቀትር ይልቅ አመሻሽ ላይ እና በምሽት ሊደረጉ የሚችሉባቸው ሁኔታዎች አቅም በፈቀደው ልክ የሚገኙ ከሆነ በምሽት የሚደረጉ ጨዋታዎች ቁጥር መበራከት የሊጉን የፉክክር ደረጃ እና የማዝናናት አቅምን ከመጨመር አንፃር ጥሩ ሚና ሊኖረው ይችላል።