የሀገራችን ሁለተኛው የሊግ እርከን የሆነው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በ15 ጨዋታዎች ሲጀመር በእነዚህ ላይ የታዩ ዓበይት ጉዳዮችንም እንደሚከተለው አዘጋጅተናቸዋል።
ችላ የተባለው የተጫዋቾች የመለያ ቁጥር ጉዳይ
በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ ክለቦች በአመዛኙ በሜዳቸውና ከሜዳቸው ውጭ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የሚገለገሉባቸው ሁለት አለፍ ሲል ደግሞ ሦስት የተለያየ በቀለም አማራጮች የተዘጋጁ መለያዎች አሏቸው። በእነዚህ የተለያዩ መለያዎች ላይ ግን የተጫዋቾች መለያ ቁጥሮች በወጥነት ለተመላካች እይታ ምቹ ሆነው ሲሰፍር መመልከት ብርቅ ነገር ይመስላል። በተለይም ከርቀት መለየት የማያስችሉ የመለያና ቁጥሮች የሚፃፉበት የቀለም ስብጥር እንዲሁም መጠናቸው እጅግ ደቀቅ ያሉ የመሆናቸው ጉዳይ በመጀመሪያው የሊጉ ሳምንት ጨዋታዎች ተስተውለዋል። ምንም እንኳን ይህ ችግር በሁለተኛው የሀገሪቱ የውድድር እርከን የሚስተዋል ቢሆንም አወዳዳሪው አካል በትኩረት ሊመለከተው እና ክለቦቹ ጥቃቅን የሚመስለውን ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጡበት ማስገደድ ይገባዋል።
ስሜታዊ አሠልጣኞች
በከፍተኛ ሊግ ደረጃ የሚደረጉ ውድድሮችን ለሚከታተል ሰው በስሜታቸው የሚነዱ እና ለቁጥጥር አስቸጋሪ የሆኑ የአሰልጣኞች ባህሪን መመልከት የተለመደ ክስተት እንደሆነ ይገነዘባል። ይህም ችግር በሊጉ ረጅም ዓመታት ካሰለጠኑት አሠልጣኞች እስከ አዳዲሶቹ የሚታይ የጋራ ችግር ነው።
አሠልጣኞች ሜዳ ሲገቡ ዋነኛ ዓላማቸው መሆን የሚገባው የቡድኑን መንፈስ መጠበቅ እና ቡድናቸው ከጨዋታው አዎንታዊ ውጤት ይዞ እንዲወጣ መውተርተር እንጂ ከዕለቱ የጨዋታ ዳኞች ጋር አላስፈላጊ ሰጣ ገባ ውስጥ በመግባት የሚገኝ ይህ ነው የሚባል ትርፍ አለመኖሩን ሊረዱ ይገባል።
ታድያ በተለይ በምድብ ሀ የመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታዎች የታዘብናቸው አንዳንድ ገጠመኞች ስሜትን በመቆጣጠር ረገድ ያልተሰሩ ቀሪ የቤት ስራዎች ስለመኖራቸው ፍንትው አድርጎ ያሳዩ ነበር።
የትጥቅ አለማሟላት
ከፍተኛው ሊግ ከዚህ ቀደም የሚታወቅበት አንዱ እና ዋነኛው በቂ ትጥቅ አለማሟላት ነው። ይህ የትጥቅ ችግር ጉዳይ ቡድኖች ከዓመት ወደ ዓመት ይዘው በመጓዝ የውድድሩ እንቅፋት መሆናቸውን ደግሞ አሁንም ቀጥለዋል። ከዚህም መነሻነት በጊዜ ዝግጅታቸውን አለማከናወናቸው እንዳይታወቅባቸው ከዳኞች እና ከአወዳዳሪው አካል ጋር አላስፈላጊ ውዝግብ ውስጥ ሲገቡ ይስተዋላል። የዚህም ማሳያ በምድብ ለ የሚገኘው ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ይዞት የመጣው ካሶተኒ ከባለሜዳው ስልጤ ወራቤ ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ተለዋጭ እስኪመጣ ድረስ ጨዋታው ለ45 ደቂቃ ለመዘገየት ምክንያት ሲሆን ተስተውሏል ። ከጨዋታው በፊት የነበረው መዋከብ ቡድኑ በሙሉ ትኩረት ስለመጫወቱ ጥያቄ የሚያስነሳም ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይ አወዳዳሪው አካል በቅድመ ውድድር ስብሰባ ላይ ቀድሞ ስራዎችን ካልስራ የጨዋታ ሰዓት መዘግየት ዕድሎችን እየከፈተ ስለሚመጣ ቀድሞ የቤት ስራቸውን መጨርስ እና ማስጨርስ አለባቸው።
ከመመራት ተነስቶ ያሸነፈው ጌዲኦ ዲላ
በከፍተኛው ሊግ ከጨዋታ ጨዋታ ቡድኖች ይዘው ከሚገቡት የጨዋታ ስልቶች አንፃር ሦስት ነጥብ ይዞ መውጣት እጅግ በጣም ከባድ ነው። በተለይም ከመመራት አንስቶ ወደ አሸናፊነት መምጣት ድሉን ያማረ እና የተዋበ ያደርገዋል። በምድብ ሀ ያሉት ሀላባ ከተማ እና ጌዲኦ ዲላ ባደረጉት ጨዎታ ጊዴኦ ዲላ ይህን ድል ማሳካት ችሏል። በአሠልጣኝ ስመኘው ገመዳ የሚመሩት ጌዲዎዎች ብድሩ ነርሀሰን እና ክንዴ አብቹ ባስቆጠሩት ሁለት ተከታታይ ግቡች ከመመራት ተነስተው ማሸነፍ መቻላቸው የቡድናቸውን ተነሻሽነት እና ጥንካሬ ገና በመጀመሪያው ሳምንት ያሳየ ነበር።
የፌዴሬሽን አመራሮች መገኘት
በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ስር ከሚደረጉት ውድድሮች ውስጥ አንዱ የሆነው ከፍተኛ ሊግ ታህሳስ 2 ሲጀመር በሦስቱም ቦታዎች ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት፣ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት፣ የውድድር አመራሮች እና የከተማ አተዳደር ከንቲባዎች በስፍራው ተገኝተው ጨዋታ ማስጀመር ችለዋል። ከዚህ ቀደም በአመታዊ ስብሰባዎች ላይ ከለቦች እንደ ቅሬታ ከሚያነሷቸው ጉዳዮች መካከል በፌዴሬሽኑ ትኩረት እንደተነፈጋቸው የሚገልፁ ከመሆኑ አንፃር ይህ ተግባር በመልካምነቱ የሚጠቀስ ነው። ያም ሆኖ በመክፈቻ ጨዋታዎች ላይ ከመገኘት ባሻገር ከመደቨኛ ስራቸው ጋር በተስማማ ፕሮግራም አልፎ አልፎ ውድድሮችን መከታተል የሚመሩት እግር ኳስ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለመታዘብ የሚረዳ በመሆኑ ይበልጥ ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ ነው።
ከሰዓት ጋር ሩጫ
የዘንድሮው የከፍተኛ ሊግ መርሐ ግብር 4፡00 ፣ 8፡00 እና 10፡00 ላይ እንደሚደረጉ ይታወቃል። ታድያ የመጨረሻው ጨዋታ የሚደረግበት 10፡00 ከወዲሁ ሊታሰብበት እንደሚገባ ያመለከተ ሳምንት አሳልፈናል። ሊጉ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን የሌለው ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የጨዋታ መጀመርያ ሰዓቶች በተያዘላቸው ሰዓት የመጀመር ቸልተኝነት ያለ ከመሆኑ በተጨማሪ አስፈላጊ ቅድመ ስራዎች በአግባቡ የማይሰሩ ከመሆኑ በመነጨ ቡድኖች ዘግይተው ሜዳ የመድር እና ከደረሱም በኋላ ያልተሟሉ ጉዳዮች ካሉ እስኪሟሉ በሚል ዘግይተው ሲጀመሩ ይስተዋላል። ለዚህ መነሻ የሚሆነውም ቅዳሜ 8፡00 ላይ መጀመር የነበረበት የወራቤ እና ኮልፌ ጨዋታ 45 ደቂቃ ዘግይቶመጀመሩ ሲሆን የተጠናቀቀውም 10፡40 ላይ ነበር። የበዚህም ምክንያት ቀጣዩ የሰንዳፋ እና ቡታጅራ ጨዋታ መጀመር ከነበነበት 45 ደቂቃ ዘግይቶ ተጀምሮ ለዓይን ያዝ ሲያደርግ ተጠናቋል።
በመሆኑም እንዲህ አይነት ሰዓት የሚያዘገዩ ጉዳዮችን በዘላቂነት መቅረፍ አልያም የ10 ሰዓት ጨዋታዎች ቀደም ብለው የሚደረጉበትን መላ መፈለግ ይገባል።
የደጋፊዎች በስታደዮም መገኘት
በከፍተኛ ሊግ ደንብ ውስጥ በዝግ ስታዲየም ይደረጋል የሚለው እንዲሁም በውይይት ወቅት የተገለፀው የነበረው ተወዳዳሪዎቹ በዝግ ስታደዮም እንደሚደርጉ ቢገለፅም በመከፍቻው ቀን ደጋፊዎች በስታደዮሞቹ ተገኝተው ሲታደሙ ታይቷል። ይህም በቡድኖች ዙሪያ ቅሬታ የፈጠረ ሲሆን አወዳዳሪው አካል ውድድሩን ደጋፊ እንዲገባ ሲፈቅድ በደብዳቤ ለ30 ቡድኖች ሊሳውቅ ነበር የሚል ቅሬታ የያዘ ሀሳብ ተስምቷል። ፌዴሬሽኑ ደጋፊ እንዲገባ ከፈቀደም ምን ያህል ደጋፊ የሚለውን በግልፅ ሊሳውቅ ይገባል።