የአፍሪካ ዋንጫን የሚመሩ ዳኞች ዝርዝር ይፋ ሲደረግ በአምላክ ተሰማ በዝርዝሩ ተካቷል

በቀጣዩ ወር በሚጀምረው የካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ጨዋታ እንዲመሩ ስልሳ ሁለት የአህጉሪቱ ዳኞች ሲመረጡ ሁለት ዳኛ ከኮንካ ካፍ ሀገራት በድምሩ 64 ዳኞች ተካቷል፡፡

የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ሀገራችን ኢትዮጵያን ከስምንት አመት በኋላ በድጋሚ ተካፋይ በማድረግ በካሜሩን አስተናጋጅነት ወርሀ ጥር ላይ መካሄድ ይጀምራል፡፡ ይህንን ውድድር የሚመሩ ዳኞችን ካፍ በዛሬው ዕለት ይፋ ሲያደርግ ከአህጉሪቱ በዋና ዳኝነት (23) ከአፍሪካ ውጪ እስማኤል ኢትፋ የተባለን ዋና ዳኛ ከሴንትራል አሜሪካ እና ካረቢያን ሀገራት እግር ኳስ ማህበር (CONCACAF) ሲካተት በድምሩ ቁጥራቸው 24 ሲደርስ በረዳት ዳኝነት በአንፃሩ 31 የአህጉሪቱ ዳኞች በዚህ ትልቅ መድረክ በዳኝነት እንዲመሩ ተመድበዋል፡፡ በዋና VAR ዳኝነት ደግሞ ቋሚ ዘጠኝ ዳኞች ሲመረጡ ከዘጠኙ መሀል ድሪው ፊሸር የተባለ ዳኛን ከኮንካ ካፍ ተካቷል፡፡

በዋና ዳኝነት ከተመረጡ 24 ዳኞች መሀል ግብፅ ሁለት ዳኞችን በማስመረጥ ቀዳሚ ስትሆን በረዳት ዳኞች ሞሮኮ ሶስት በማስመረጥ የላቀ ቁጥርን ይዛለች፡ ፡በዋና ዳኝነት ከተመረጡ ዳኞች መካከል ከዚህ ቀደም በዚህ የአፍሪካ ትልቁ ድግስ ላይ በዳኝነት ተሳትፎ የነበረው ኢትዮጵያዊው ዳኛ በአምላክ ተሰማ በመሀል እና በቫር ዳኝነት ለመምራት ወደ ስፍራው እንደሚያቀና ታውቋል፡፡ በአምላክ ተሰማ በአሁኑ ሰአት የኩዌት ሊግን በዳኝነት እየመራ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

ከተመረጡ ስልሳ አራት ዳኞች መሀል ከምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ዋና ዳኛ ከኢትዮጵያ ፣ ሩዋንዳ ፣ ኬኒያ እና ቡሩንዲ በረዳት ዳኝነት ደግሞ ኡጋንዳ ፣ ጅቡቲ ፣ ሱዳን እና ኬኒያ ተካተዋል፡፡