ከሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚቀመጠውን ትኩረት ሳቢ ጨዋታ እንደሚከተለው ቃኝተነዋል።
በአንድ ነጥብ ብቻ ተበላልጠው ሁለተኛ እና አንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህር ዳር እና ፋሲል የሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ ለመቀመጥ እና ለማስጠበቅ የሚያደርጉት ጨዋታ ከፍተኛ ፉክክር እንደሚነግስበት ይታሰባል። በተለይ ቡድኖቹ የሊጉ አናት ላይ ከመቀመጣቸውም ባለፈ በሊጉ ከፍተኛ ግብ ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠሩ ክለቦች (ፋሲል 14 ፣ ባህር ዳር 11) መሆናቸውም ጠንካራ እንቅስቃሴ እንደሚኖር ጠቋሚ ይሆናል።
በአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ የሚመራው ባህር ዳር ከተማ ከሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ያለማሸነፍ ጉዞው በኋላ ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ እና አናት የነበሩትን ጅማ አባጅፋር እና ወላይታ ድቻ በመርታት ዳግም ወደ ሊጉ ተፎካካሪነት ብቅ ብሏል። በየቦታው ካላው የተጫዋች የተትረፈረፈ ምርጫ አንፃር አሠልጣኙ በየጨዋታው ለውጦችን ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ግን ተመሳሳይ አስራ አንድ ተጫዋቾችን ሜዳ ላይ አስመልክተውናል። በዚህም በ4-4-2 (ዳይመንድ) የተጫዋች አደራደር ቅርፅ ከሁለቱ ፈጣን አጥቂዎች ኦሴ ማውሊ እና ዓሊ ሱሌይማን ጀርባ ፍፁም ዓለሙን በማድረግ ፈጣን ጥቃት የመሰንዘር አጨዋወት ሲከተሉ ነበር። በተጋጣሚ ሳጥን አካባቢ እንዲያሳልፉ ፍቃድ ከተሰጣቸው ሦስቱ ተጫዋቾች ውጪም በሁለቱ የዳይመንዱ የጎን ጫፍ የነበሩት አለልኝ እና ንኪማም ዘግየት ያሉ የሳጥን ውስጥ ሩጫዎችን እንዲያደርጉ በመዘየድ በተጋጣሚ የመከላከል ወረዳ የቁጥር ብልጫ እንዳይወሰድባቸው ሲያደርጉ ታይቷል። ይህ አጨዋወትም ነገ በተወሰነ ጥንቃቄ በተሞላበት ሀሳብ እንደሚደገም ይገመታል።
ባህር ዳር ነገ ከሚፋለመው ቡድን ጥንካሬ አንፃር እንደ ጅማው እና ድቻው ጨዋታ ጀብደኝነት የተሞላበት እንቅስቃሴ ላያደርግ ይችላል። በተለይ ደግሞ በተወሰኑ አጋጣሚዎች ሲስተዋልበት የነበረውን የመልሶ ማጥቃት ባህሪ ተላብሶም ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይታሰባል። ከምንም በላይ ደግሞ ወደ መሐል ሜዳ ተጠግተው የሚጫወቱትን የፋሲል ተከላካዮች ጀርባ ያለውን ቦታ ያነጣጠረ የማጥቃት እንቅስቃሴም ሊከተል ይችላል።
ዓምና ከነበረበት ጠንካራ ብቃቱ ዘንድሮም የቀጠለ የሚመስለው ፋሲል ከነማ እስካሁን ባሉት ሰባት የጨዋታ ሳምንታት ከ5 እና 6ተኛ ሳምንታት ውጪ የሊጉን መሪነት የተረከበው የለም። ነገም ቀጥተኛ የዋንጫ ተፎካካሪው የሚመስለውን ባህር ዳር በማሸነፍ ከሦስት ተከታታይ ያለማሸነፍ ጉዞ በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት ዳግም ያገኘውን የማሸነፍ መንገድ ለማስቀጠል ጠንክሮ እንደሚጫወት እሙን ነው። በሲዳማው ጨዋታ ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ ከፍተኛ የማሸነፍ ረሀብ ላይ ሆኖ ሲጫወት የነበረው ቡድኑ የተጋጣሚውን አስደንጋጭ የመከላከል አጨዋወት የተጠቀመበት ሂደት መደነቅ አለበት። መሪ ከሆነ በኋላም በቀጣዩ ደቂቃ ተጨማሪ ግብ አስቆጥሮ ውጤቱን ለማስፋት የሄደበት ርቀትም እንደዛው። ምናልባት ነገ ግን ከባህር ዳር ጥንካሬ አንፃር ቀላል የመከላከል አወቃቀር ስለማይጠብቀው የማጥቃት ስልቱ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ጨዋታውን መጀመር ይጠበቅበታል።
በ4-1-4-1 ቅርፅ ቡድናቸውን ወደ ሜዳ እንደሚያስገቡ የሚገመቱት አሠልጣኝ ሥዩም ከበደ እስካሁን ከጠንካራው የኋላ መስመራቸው መነሻነት መከላከሉ እምባዛም ያሳሰባቸው ባይመስላም ነገ ግን መጠነኛ ጥንቃቄ አዘል የተጫዋች ምርጫ እንደሚኖራቸው ይታሰባል። በሲዳማው ጨዋታ በተጋጣሚ የመከላከል ወረዳ በተደጋጋሚ የመገኘት ፍቃዱ የተሰጣቸው የመስመር ተከላካዮችም ነገ የተገደበ ሀላፊነት ኖሯቸው እንደሚጫወቱ ይገመታል። ይህ ቢሆንም ግን በጥሩ ወቅታዊ ብቃቱ ላይ በሚገኘው በረከት ደስታ ላይ የተመረኮዙ እና ቁመታሙን አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች እንደሚያስመለክት መናገር ይችላል።
በባህር ዳር በኩል አምበሉ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ አሁንም ከጉዳቱ ባለማገገሙ ነገ የማይኖር ሲሆን በፋሲል ከነማ በኩል ደግሞ ሳሙኤል ዮሐንስ አይኖርም። የአስቻለው ታመነ የመሰለፍ እና ያለመሰለፍ ጉዳይ ደግሞ ነገ ጠዋት እንደሚለይ ተነግሮናል። ከዚህ ውጪ ሱራፌል ዳኛቸው እና በዛብህ መለዮ ጨዋታውን ከተጠባባቂ ወንበር እንደሚጀምሩ ተመላክቷል።
ይህንን ጨዋታ ፌዴራል ዋና ዳኛ ቢኒያም ወርቃገኘሁ የሚመሩት ይሆናል።
እርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን ከተገናኙባቸው አራት ጨዋታዎች ሦስቱ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ አንዱን ፋሲል ከነማ አሸንፏል። ፋሲል ከነማ ስድስት ባህር ዳር ከተማ ደግሞ ሁለት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ባህር ዳር ከተማ (4-1-3-2)
ፋሲል ገብረሚካኤል
ግርማ ዲሳሳ – ፈቱዲን ጀማል – መናፍ ዐወል – አህመድ ረሺድ
በረከት ጥጋቡ
አብዱልከሪም ንኪማ – ፍፁም ዓለሙ – አለልኝ አዘነ
ዓሊ ሱሌይማን – ኦሴ ማውሊ
ፋሲል ከነማ (4-2-3-1)
ሚኬል ሳማኬ
ዓለምብርሃን ይግዛው – ያሬድ ባየህ – አስቻለው ታመነ – አምሳሉ ጥላሁን
ይሁን እንዳሻው – ከድር ኩሊባሊ
ሽመክት ጉግሳ – ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ – በረከት ደስታ
ኦኪኪ አፎላቢ