የጨዋታ ሳምንቱ መክፈቻ በነበረው እና ያለ ግብ በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ አሰልጣኞቹ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።
ዮሐንስ ሳህሌ – መከላከያ
ስለጨዋታው
“አምስት ቋሚ ተሰላፊዎች አለመኖራቸውን ተከትሎ አዳዲስ ተጫዋቾችን መመልከታችን ጥሩ ሆነልን። ጠንካራ ፈተና እንደሚገጥመን አስበን ነበር። ነገርግን ይዘን ከገባነው ስብስብ አንፃር አንድ ነጥብ ለእኛ በቂ ነው።”
በስምንቱ ሳምንቱ ቡድኑ ላይ የሚፈልገውን ነገር እያገኘ ስለመሆኑ
“ህብረትን ከመፍጠር ፣ ከዲሲፕሊን ፣ ተጫዋቾች ላይ ፍላጎትን ከመፍጠር አንፃር ጥሩ ነን አዲስ እየተዋቀረ የሚገኝ ቡድን እንደመሆኑ ከውጤት አንፃር አንዳንድ ጊዜ መዘበራረቆች አሉ ወጣ ገባ የማለት ነገር አለ በሚኖረን የእረፍት ጊዜ ልጆቹ ከከፍተኛ ሊግ የመጡ እንደመሆናቸው ሊጉን በደንብ ተጫውተውበት እየተረዱት እንደመምጣታቸው በእረፍቱ ጊዜ በደንብ ተነጋግረን አሻሽለን ለመምጣት እናስባለን።”
ገብረመድህን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና
ስለጨዋታው
“እንቅስቃሴው እንዳሰብነው አልነበረም። አንደኛው ምክንያት ሜዳው ነው፤ እኛ ኳስ ተቆጣጥረን ለመጫወት ስንፈልግ የሜዳ ሁኔታ ያንን አልፈቀደም። ዛሬ ደግም ውሃ አጠጥተው ምን እንዳረጉት እንጃ። ውጤት አጥተህ በተረጋጋ መልኩ ነገሮችን ማድረግ በተቸገርክበት በዚህ ጊዜ እንዲህ አይነት ነገር ሲገጥምህ ከባድ ነው። ምንም ማድረግ አይቻልም፤ በእንቅፋት ላይ እንቅፋት ያጋጥምሃል።”
ግብ ማስቆጠር ስላለመቻላቸው
“እንደ አጠቃላይ ከስነልቦና ጫና መሆን ካልቻልን በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው አሁን መጨረሻ ላይ የተሳተውን ኳስ ስትመለከት ሁኔታውን መረዳት ይቻላል አንዳንድ ፍላጎት ጣራ ሲነካ መሰል ነገሮች ያጋጥማሉ።”
ሙሉ ሦስት ነጥብ ማግኘት ስላለው አስፈላጊነት
“የዛሬው ጨዋታ መነሻ ይሆነናል ብለን ነበር ነገርግን ማሸነፍ የሚገባንን ጨዋታ ሳናሸንፍ ቀርተናል እንግዲህ እግርኳስ ሂደት በቀጣይ ጨዋታ መነሻ የሚሆነን ውጤት ለማስመዝገብ በስነልቦና ረገድ ስራዎች ይጠብቁናል።”
ቦርዱ በእሱ ላይ ስላሳየው እምነት
“ይህ ስራህን ተማምነህ ተረጋግተህ እንድትሰራ ያደርግሀል። ከመጀመሪያው ጀምሮ በቦርዱ ያለው ድጋፍ በቃላት የሚገለፅ አይደለም። እኔንም ብቻ ሳይሆን ቡድኑን በደምብ እየደገፉ ይገኛል። ነገርግን በሚፈልጉት ልክ ምላሽ እያገኙ አይደለም። በቀጣይ የተሻለ ነገር ሰርተን ለመካስ እንሞክራለን።”