የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 0-0 ፋሲል ከነማ

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታም ያለግብ የተጠናቀቀ ሲሆን ተጋጣሚ አሰልጣኞች ከሱፐር ስፖርት ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ባህር ዳር ከተማ

ያቀዱት የጨዋታ መንገድ ስለመተግበሩ

ከመጀመሪያው የፋሲል ጥንካሬ ኮሪደሩን በሚገባ መጠቀም ነው ፤ ያንን እንዳይጠቀሙ አድርገናል። የዛን ያህል ደግሞ እኛ ከተከላካይ መስመራችን በቀጥታ ወደ እነሱ የግብ ክልል የምንልካቸው ኳሶች አጥቂዎቻችን ተጠቅመው እንዲያገቡ ያደረግነው ሙከራ ወደ ግብ አለመቀየሩ ነው እንጂ ዓሊም ማዉሊም የተሻለ እንቅስቃሴ አድርገዋል። በተለይ ማዉሊ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በምንፈልገው አጨዋወት ሄዷል ብዬ ነው የማስበው።

ቡድኑ ስለታየበት የአጨራረስ ችግር

መሪ ሆኖ ለመጨረስ ከነበረ ጉጉት ተጫዋቾች ጎል ይፈልጋሉ። ከዛ የተናሳ (ከጉጉት) እና ከትኩረት ማነስ የተነሳ ጎሎችን ስተናል። በአጠቃላይ ግን በእኛም በፋሲልም በኩል ጥሩ ፉክክር ታይቷል ብዬ ነው የማስበው። አንድ ተጫዋች ከወጣብን በኋላም ያንን ውጤት ለማስጠበቅ እና ደረጃችንን ባለበት ቦታ ለማስቀጠል ተጫዋቾቼ ያደረጉትን ተጋድሎ ከልብ ማድነቅ እፈልጋለሁ።

ከመሪው ጋር ነጥብ መጋራት በቀጣይ ስለሚፈጥረው መነሳሳት

ፋሲል ክብሩን ለማስጠበቅ የሚጫወት ቡድን ነው ፤ ሉጉን የሚመራም ቡድን ነው። ነጥብ ይዞ መውጣት በተለይም ተጫዋችም ጎሎብን ነጥብ ይዘን መውጣት ለሚቀጥለው ጨዋታ በሥነ ልቦናው የተሻለ ዝግጅት እንዲኖረን ያደርጋል።

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

ያሰቡትን እንቅስቃሴ ስለመመልከታቸው

በመጀመሪያው አጋማሽ እንዳሰብኩት አልነበረም። ይህን ስል መኃል ላይም ከኋላም ገፍተን ጫና የመፍጠር ጉዳይ ላይ በመኃላችን ያለው ክፍተት መስፋቱ እነሱ የመጫወቻ ክፍተት በማግኘታቸው እንዲነሱ አድርገናቸዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ ጥሩ ነገር አድርገናል ብዬ አላምንም። ያንን ነው በዕረፍት ለማረም የሞከርነው። እነሱ ሜዳ መግባት አለብን አሸናፊነታችንን ለመቀጠል እና ግብ ለማግኘት የምንሞክር ከሆነ እነዚህን ጥቃቅን ነገሮች አሻሽለን መሄድ እንዳለብን አስበን ነው የገባነው። በዚያ መሰረት ሁለተኛው አጋማሽ ይሻላል። እንደዛም ሆኖ ግን በእነሱ በኩል ዕኩል መውጣትን ፈልገዋታል። የኳሶች ሪትም መቆራርጥም የእኛንም ስሜት የጎዳ ይመስላል። ያም ሆኖ ሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ሆኖ ውጤቱ ያው የተመዘገበው ነው። እነዚህን ነገሮች አሻሽለን የመጨረሻ ጨዋታችንን በድል ተወጥተን አሁንም ደረጃችንን አስጠብቀን ለመጨረስ ጥረት እናደርጋለን።

ስለቡድኑ የአማካይ ክፍል ቅርፅ

ለምሳሌ ተቃራኒ ቡድን በ4-2-3-1 የሚመጣ ከሆነ የእኛ አካሄድም ሊለይ ይችላል። ይሁን ግን ቦታው ላይ በቂ ነው። የእነ ኦኪኪን የፊቱን መስመር ለማጠንከር የሚችሉ ፣ የማግባት እና ኳስን የመቆጣጠር አቅም ያላቸው ፣ የተቃራኒን ቡድን እንቅስቃሴ ሊሰብሩ የሚችሉ ፣ በርካታ ጥሩ አማካዮች አሉን። እነሱን ማብዛታችን እነዚህን አማራጬች ለመፍጠር ነው። ከሲዳማ ጋር ስንጫወትም ያገኘነው ነገር ይህንን ነው። ዛሬም ትኩረት አድርገን የሰራነው በዚያ ዙሪያ ነበር። ግን እንደጠበኩት አላገኘሁትም ፤ የሚሻሻል ነው።

ስለሱራፌል ዳኛቸው ከጉዳት መመለስ

ሱራፌል መቶ በመቶ ተመልሷል ማለት አይደለም። ልምምድ ላይ ከ 50-60 በመቶው ነው ያለው። ነገር ግን ልምዱ እና አንዳንድ ነገሩ በዚህ በቀረችን ሰዓት ላይ የሆነ ነገር ያደርጋል የሚል የምንጠብቀው ነገር ነበር። ከዛ አኳያ እንጂ የአካል ብቃት ዝግጁነቱ ሙሉ ለሙሉ መጥቷል ማለት አይደለም። በቀጣይ ጊዜያት ግን እየሰራ ማንም እንደሚያውቀው ከፍተኛ ጠቀሜታ ሊሰጠን ይችላል። ዋናው ነገር ግን አገግሞ ወደ ሜዳ መመለሱ አዎንታዊ ነው።

የቡድኑ ሰፊ የቀኝ መስመር ጥቃት ወደ ውጤት ስላለመቀየሩ

አንደኛ ኳስ የምናደርስበት የጊዜ አጠባበቅ ነው። ኮሪደሩን መጠቀም ብቻ ሳይሆን አጨራረሱ ማማር አለበት። እነዛ መናበቦች ይቀራሉ። ዋናው ነገር በግራም በቀኝም መስመሩን ማግኘቱ ነው። ከኋላም እየተነሱ እንዲሄዱ ነው ጥረታችን ምክንያቱም በውስጥ ብቻ ማስቆጠር አይቻልም። ያንን አሁንም ማሻሻል አለብን። እዛ ጋር መሄዱ ጥሩ ነው። ነገር ግን ውጤታማ ነገሮች መገኘት አለባቸው።

ውጤቱ ፍትሀዊ ስለመሆኑ

በፍፁም ፍትሀዊ አልለውም። ምክንያቱም እንደአመጣጣችን የተሻለ ነገር ማድረግ ይገባን ነበር ብዬ ነው የማስበው። የኳስ አጋጣሚዎች እንዲህ ናቸው ። በስህተት ይታጀባል አንዳንድ ጊዜ ፤ በዚህ ተቆጭተን የተሻለ ሆነን ለመገኘት ጥረት እናደርጋለን።