ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና ከ ድሬዳዋ ከተማ

ከድል እና ከሽንፈት መልስ የሚገናኙት ሀዲያ እና ድሬዳዋ የሚያደርጉት የነገ የመጀመሪያ ጨዋታ እንዲህ ተዳሷል።

ከስድስት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ መከላከያን በማሸነፍ ከድል ጋር የታረቁት ሀዲያዎች ለሁለት ወር ከተጠጋ ጊዜ በላይ ጠብቀውት ካገኙት የአሸናፊነት መንገድ ላለመልቀቅ እና በደረጃ ሰንጠረዡ መሻሻል ለማምጣት ጠንክረው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይገመታል።

በአሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የሚመሩት ሀዲያዎች ባደረጓቸው የከዚህ ቀደም ጨዋታዎች አዎንታዊ ውጤት ባያመጡም ለትችት የሚዳርጋቸው እንቅስቃሴ እንኳን አላደረጉም ነበር። በስድስቱ ጨዋታዎች የቡድኑ ዋነኛው ችግርም በማጥቃቱ ረገድ በግለሰቦች ላይ ጥገኛ መሆኑ እና የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር የሚሄድበት ርቀት ፍጥነት አልባ መሆኑ ነበር። መከላከያን በረቱበት ጨዋታ ግን በተወሰነ መልኩ ይህ በየጨዋታው ሲስተዋል የነረው ክፍተት ተሻሽሎ ነበር። በሁለቱ መስመሮች ሲደረጉ የነበሩ ፈጣን እንቅስዋሴዎችም ለወትሮ ጠጣር የነበረውን የመከላከያን የኋላ መስመር ሲፈትን ነበር። ከምንም በላይ ደግሞ በግራ ተመላላሽ ቦታ ተሰልፎ የነበረው ኢያሱ ታምሩ በተደጋጋሚ የተጋጣሚ የመከላከል ሲሶ እንዲደርስ ፍቃድ ተሰጥቶት የቡድኑን የማጥቃት አጨዋወት ሲዘውር ነበር። ይህ አዎንታዊ አጨዋወትም ነገ ለድሬዳዋ ከተማ ፈተና እንደሚሆን ይታሰባል።

በሦስት አልፎ አልፎ ደግሞ በአራት ተከላካዮች የሚጫወተው ቡድኑ በመከላከሉ ረገድ እምብዛም ክፍተት አይታይበትም። በተለያዩ የተከላካይ ጥምረቶችም ሲረባበሽ አይስተዋልም። በመከላከያው ጨዋታ ደግሞ በተጣጣሚው ያን ያህል ጫና ባይኖርበትም በእርጋታ ኳስን መስርቶ ለመውጣት ሲጥር እና የግብ ዘቡን ሲያጋልጥ አይታይም። በ6 ቁጥር ቦታ የሚጫወተው ተስፋዬ አለባቸው ደግሞ የተከላካይ መስመሩ እንዳይጋልጥ የሚያደርገው ጥረት መልካም ነው። ነገ ግን ከአራተኛ ሳምንት በኋላ ድል ከራቀው ድሬዳዋ ጋር መጫወቱ ተጋጣሚው ግቦችን ለማግባት እና ለማሸነፍ ከመቼውን ጊዜ በላይ ስለሚውተረተር ሊፈተን ይችላል።

ሊጉን በድል ጀምሮ ከዛ በኋላ በወጥነት ወጥ ብቃት ማሳየት ተስኖት ሲጫወት የነበረው ድሬዳዋ ከተማ በሦስት ጨዋታዎች የጣላቸውን ስምንት ነጥቦች እያሰበ ዳግም ሦስት ነጥብ ለማግኘት ነገ ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርግ ይታመናል።

በኢትዮጵያ ቡና በፍፁም ቅጣት ምት በተቆጠሩበት ሁለት ጎሎች የተረታው ድሬ በጨዋታው የወረደ ብቃት ነበር ያሳየው። በተለይ ቡድኑ ኳሱን ለተጋጣሚው በመተው በራሱ ሜዳ በመከማቸት ሲያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ የሚጠበቅ ቢሆንም ለቅፅበቶች የነበረው ምላሽ ዘገምተኛ መሆኑ በጨዋታው ውጤት እንዳያገኝ ያደረገው ይመስላል። በአንዳንድ የጨዋታ ሂደቶች ብቻ ቡና ኳስ ሲመሰርት ተጭኖ ለመቀበል ቢጥሩም በቡድናዊ ስልት አለመቃኘቱ ብክነት ብቻ እንዲሆን አድርጎት ነበር። ከቀደሙት ዓመታት በተለየ ጥሩ ስብስብ የያዘው ቡድኑም በቶሎ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ነገ ከመቼውም ጊዜው በላይ የማጥቃት አጨዋወቱ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚገባ መናገር ይቻላል።

በቡድኑ ወጥ ያለሆነ ጉዞ ውስጥ በአንፃራዊነት ወጥ ብቃት ሲያሳይ የሚስተዋለው ተጫዋች መሐመድ አብዱለጢፍ ነው። የግራ መስመር አጥቂው መሐመድ ፍጥነቱ፣ አካላዊ ጥንካሬው እና ቴክኒካዊ ብቃቱ ነገም ለቡድኑ የሚያስፈልግ ይመስላል። ምናልባት ድሬ ኳስ ለሀዲያ ሰጥቶ የሚጫወት ከሆነ ደግሞ በሽግግሮች ሊንቀሳቀስ ስለሚችል የተጫዋቹ ፍጥነት ጠቃሚ ነው። ከዚህ ውጪ ማማዱ ሲዲቤን ዒላማ ያደረጉ ተሻጋሪ ኳሶችም በነገው የድሬዳዋ የግብ ፍለጋ ሂደት የምናስተውለው እንቅስቃሴ እንደሚሆን ይታመናል።

ሀዲያ ሆሳዕና አጥቂው ዑመድ ኡኩሪ ከጉዳት ሲመለስለት ብርሃኑ በቀለ ግን ከጨዋታው ውጪ ሆኗል። ከዚህ ውጪ በመከላከያው ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደው ኤፍሬም ዘካሪያስ ልምምድ ቢጀምርም የመግባቱ ነገር አጠራጣሪ ነው ተብሏል። ድሬዳዋዎች ደግሞ አማካያቸው ዳንኤል ኃይሉን በቤተሰብ ሀዘን ምክንያት እንደማያገኙ ተጠቁሟል። በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ጉዳት አጋጥሞት ተቀይሮ የወጣው መሳይ ፓውሎስ ደግሞ ከጉዳቱ ማገገሙ እና የመስመር አጥቂው ጋዲሳ መብራቴም ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑ ለድሬዳዋዎች መልካም ዜና ነው።

ይህንን ጨዋታ ፌዴራል ዋና ዳኛ ዓለማየሁ ለገሰ እንደሚመሩትም ታውቋል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሀዲያ ሆስዕና እና ድሬዳዋ ከተማ እስካሁን በሊጉ አራት ጊዜ ሲገናኙ ድሬዳዋ ከተማ ሁለት ጊዜ ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ አንድ ጊዜ ድል ሲቀናቸው የአምናው የመጨረሻ ግንኙነታቸው ያለግብ ተጠናቋል። በጨዋታዎቹ ከተቆጠሩ ስምንት ጎሎችም ድሬዳዋ ሦስት ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ አምስት ግቦችን አስመዝግበዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዲያ ሆሳዕና (3-5-2)

ያሬድ በቀለ

ቃለዓብ ውብሸት – ፍሬዘር ካሳ – ኤሊያስ አታሮ

ኢያሱ ታምሩ – ሳምሶን ጥላሁን – ተስፋዬ አለባቸው – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን – ሔኖክ አርፊጮ

ባዬ ገዛኸኝ – ሀብታሙ ታደሰ

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ፍሬው ጌታሁን

እንየው ካሳሁን – መሳይ ጳውሎስ – አውዱ ናፊዩ – ሄኖክ ኢሳይያስ

ብሩክ ቃልቦሬ – ዳንኤል ደምሴ

ጋዲስ መብራቴ – ሙኸዲን ሙሳ – አብዱለጢፍ መሀመድ

ማማዱ ሲዲቤ

ያጋሩ