ሪፖርት | አዲስ አበባ እና ሀዋሳ ነጥብ ተጋርተዋል

የምሽቱ ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማን አገናኝቶ በ1-1 ውጤት ተጠናቋል።

አዲስ አበባ ከተማ ከወልቂጤው ሽንፈት አንፃር ጉዳት የገጠመው ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመን በዋኬኔ አዱኛ ፣ ተከላካዩ ሳሙኤል አስፈሪን በዘሪሁን አንሼቦ እንዲሁም አማካዩ ብዙአየሁ ሰይፉን በሙሉቀን አዲሱ በመተካት ጨዋታውን ጀምሯል። ሀዋሳዎች በበኩላቸው ሰበታን ካሸነፉበት ጨዋታ ግራ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ ዮሐንስ ሱጌቦን አሳርፈው መድሀኔ ብርሀኔን አሰልፈዋል።

ቀዝቀዝ ባለ እንቅስቃሴ በጀመረው ጨዋታ አዲስ አበባዎች የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል። የሀዋሳ ቅብብሎች ወደ ግብ ክልላቸው እንዳይደርሱ በማድረግ ወደ ግራ መስመር ያደሉ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ጥረዋል። ሆኖም በርከት ባሉ የቆሙ ኳሶች የታጀበው ጨዋታ በቀላሉ ሙከራዎች አልታዩበትም። ቀስ በቀስ ከሜዳቸው መውጣት የቻሉት ሀዋሳዎች በሙከራ ቀዳሚ የነበሩ ሲሆን እምብዛም ግን አስደንጋጭ አልነበሩም። 20ኛው ደቂቃ ላይ ሀዋሳዎች በአዲስ አበባ ሳጥን ውስጥ ሲዱርሱ ብሩክ በየነ ከኤፍሬም አሻሞ ጥሩ ኳስ ቢያገኝም የመጨረሻ ውሳኔው አላማረም። መስፍን ታፈሰም ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ዳንኤል ደርቤ ከቀኝ በረጅሙ ባሻገረው ኳስ ቢሞክርም ኢላማውን አልጠበቀም።


በእንቅስቃሴ ወደ መመጣጠን የመጣው ጨዋታ ግለቱ ከፍ እያለ ሲሄድ 35ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ታይቶበታል። ከሙሉቀን ታሪኩ ረጅም ኳስ የደረሰው እንዳለ ከበደ ከፍፁም ጋር ከተቀያየረበት የግራ መስመር ሲያሻማ ሪችሞንድ ኦዶንጎ ጊዜውን ጠብቆ ሳጥን ውስጥ በመድረስ በግንባሩ አስቆጥሯል። ሆኖም ሀዋሳ ከተማ የሦስቱ አጥቂዎቹን ጥምረት ተጠቅሞ ከሦስት ደቂቃ በኋላ አቻ ሆኗል። መስፍን ታፈሰ ከብሩክ የተቀበለውን ኳስ ወደ መሀል በጠበበው የአዲስ አበባ የኋላ ክፍል ግራ በኩል ሲያሳልፍለት ኤፍሬም አሻሞ ራሱን ነፃ አድርጎ በመግባት ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።


በቀጣይ ደቂቃዎችም ጨዋታው በጥሩ ፍልሚያ ሲቀጥል አዲስ አበባዎች ከቆሙ ኳሶች የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ ጥረዋል። ጭማሪ ደቂቃ ላይ በሌላኛው ጫፍ ብሩክ በየነ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ወደ ግብ የላከው ኳስ ግን ግብ ለመሆን ተቃርቦ ለጥቂት በጎን የወጣ ነበር።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ጉሽሚያዎች በርክተውበታል። በዚህም መነሻነት ቁራቸው ቀላል ያልሆኑ የቅጣት ምቶችን ብንመለከትም ወደ አደገኛ ሙከራነት አልተቀየሩም። የመጀመሪያው አደገኛ አጋጣሚ የታየውም 58ኛው ደቂቃ ላይ በሀዋሳ ከተማዎች በኩል ሲሆን ከግራ መስመር ኤፍሬም አሻሞ ያሻገረውን እና መስፍን ታፈሰ በሩቁ ቋሚ በመሆን ለማግኘት በጣረው እጅግ ለግብ የቀረበ ኳስ ወደ መሪነት ሊሸጋገሩ ነበር። ጨዋታው በቀጣይ ደቂቃዎች ሙከራዎች ባይታበትም ችኮላ በዛው እንጂ በሁለቱም በኩል የነበረው የማጥቃት ፍላጎት በግልፅ ይታይ ነበር።

በጨዋታው የቆመ ኳስ ዕድሎች መባከናቸውን ቀጥለዋል። ወደ ማብቂያው ሲቃረብ ሁለቱም ተደጋጋሚ ቅያሪዎችን በማድረግ የማጥቃት ኃይላቸውን በአዲስ ጉልበት ለማጠናከር ሞክረዋል። 86ኛው ላይ ከሀዋሳ ተቀያሪዎች መካከል ተባረክ ሄፋሞ ከመሀመድ ሙንታሪ በረጅሙ በተላከ እና በመስፍን በተጨረፈ ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ አምክኗል። እስከ ፍፃሜው በጥሩ ፉክክር የቀጠለው ጨዋታ ግን ተጨማሪ ግብ ሳይታይበት ተቋጭቷል።

ውጤቱን ተከትሎ ነጥባቸውን 11 ያደረሱት ተጋጣሚዎቹ ቀጣይ ጨዋታዎች እስኪከናወኑ ሀዋሳ ከተማ ወደ 6ኛ አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ወደ 7ኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል።