የወቅቱ የሴካፋ ባለድሎች ከነገው ጨዋታ በፊት የመጨረሻ ልምምዳቸውን አከናውነዋል

ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ልምምዱን ዛሬ ረፋድ አከናውኗል።

በአሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመራው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከወራት በፊት በዩጋንዳ አስተናጋጅነት በተከናወነው የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ አሸናፊ ሆኖ መመለሱ ይታወሳል። ከሻምፒዮንነት መልስ በኮስታሪካ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ የሦስተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ ሲዘጋጅ የነበረው ቡድኑም ከሁለት ሳምንት በፊት ከሜዳው ውጪ የቦትስዋና አቻውን ሦስት ለአንድ የረታ ሲሆን የመልሱን ጨዋታ ደግሞ በነገው ዕለት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ያከናውናል።

ማረፊያውን ሲ ኤም ሲ አካባቢ በሚገኘው የካፍ የልዕቀት ማዕከል ያደረገው ስብስቡ መስቀል ፍራወል በሚገኘው 35 ሜዳ ረፋድ ላይ ልምምድ ሰርቷል። በትናንትናው ዕለት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ልምምዱን የሰራው ቡድን በጨዋታው ዋዜማ ቀለል ያለ እንቅስቃሴ ያለው ልምምድ ሲሰራ ተስተውሏል። በተለይ ደግሞ ተጫዋቾቹ እንዲያፍታቱ ከተደረገ በኋላ መሐል ባልገባ ይዘት ያለው እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር።

ሁሉም ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ የሚገኙ ሲሆን ጨዋታቸውም ነገ 10 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚያከናውኑ ይሆናል።