በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀው የምሽቱ ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች ከሱፐር ስፖርት ጋር ቆይታ አድርገዋል።
አሰልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ – አዲስ አበባ ከተማ
በዕቅዳቸው ደስተኛ ስለመሆናቸው
ደስተኛ ነኝ። ምክንያቱም ባለፈው ከሽንፈት ነው የመጣነው። መጫወት የሚገባንን መንገድ በደንብ ሰርተን እንዲሁም ደግሞ ማሸነፍ እንደሚገባን ተነጋግረን ነው የገባነው። ከተሸናፊነት እስከመጣን ድረስ የተሻለ ነገር ማሳየት ነበረብን ፤ ልጆቹም የሚጠበቀውን አድርገዋል።
የቡድኑ ቅርፅ በማጥቃት ሂደት ላይ ስለነበረው ተፅዕኖ
እኔ እንደፈለኩት ነበር። ምክንያቱም ከዚህ በፊት የምንጫወተው 4-3-3 ነው። እሱን ወደ 4-1-4-1 መቀየር በጣም ቀላል ነው ፤ ትንሽ ነው የሚቀየረው። በፊት የለመዱት ነው ከዛ አንፃር የተወሰነ ማሻሻያ ይኖረዋል እንጂ ተመሳሳይ ነው። በዛም የሚፈለገውን ነገር አግኝቻለሁ ፤ ጥሩ ነው።
ስለብሩክ ቅያሪ
የተጫዋች ቅያሪው በብዛት መሀል ላይ አካባቢ ነው። ብሩክ ደግሞ ከዚህ በፊት አልገባም ግን የኳስ ክህሎት አለው። ወደ ፊት ሊጉን እየለመደው ሲሄድ የተሻለ ይሆናል።
አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ
ስለጨዋታው
አንዳንዴ ኳስ ላይ ያላሰብከው ነገር ነው የሚፈጠረው። በጥቃቅን ስህተቶች ዋጋ እንከፍላለን ፤ በተመሳሳይ ደግሞ ያገኘናቸውን ኳሶች አለመጠቀም የፈለግነውን እንዳናሳካ አድርጎናል። አድርገዋል ፣ ሞክረዋል ግን አልተሳካም። አንዳንዴ የማይሳካበት ጊዜ አለ። በተለይ ቀይረን ያስገባነው ልጅ (ተባረክ ሄፋሞ) ያገኘውን ኳስ ቢጠቀም ኖሮ ሰዓቱም እያለቀ ስለነበር ሦስት ነጥብ መያዝ የምንችልበት ነበር። ወጣት ነው ፣ ገና ጀማሪ ነው ፣ ብዙ ተስፋ ያለው ልጅ ነው ስለዚህ አጨራረስ ላይ መስራት ነው። ከዛ ውጪ ጥቃቅን ስህተቶችን እያረምን በድናችንን ውጤታማ እናደርጋለን ብዬ አስባለሁ። ዛሬ ሦስት ነጥብ በጣም ፈልጌ ነበር ፤ አልተሳካም። በእንቅስቃሴ ጥሩ ቢሆንም በውጤቱ ግን ደስተኛ አይደለሁም።
ስለቡድኑ የመስመር ጥቃት
የተጋጣሚ ተከላካይ መስመር ያጠብ ስለነበር የመጫወቻ ቦታ ይኖረን የነበረው ዳር እና ዳር ነው። ሁለተኛ የእነሱ ተጫዋቾች ከመሀል ወደ ዳር ነው የሚወጡት እና ያለን አማራጭ ኳሱን ወደ ዳር ማውጣት ነበረብን። እንደዛም ሆኖ ብዙ ኳሶች አግኝተናል። የአጠቃቀም ችግር ነው ፤ በተለይ በግንባር የሚሞከሩ ኳሶች። በምንሄድበት እና በሰራነው መንገድ ኳሶችን እያገኘን ነበር። የአጠቃቀም ችግር ነው ፤ ወደ ዳር አዘንብለን እንድንጫወት ያደረገን የተጋጣሚ አጨዋወት ነው።
ብዙ ኳሶች ስለመሳታቸው
ቡድናችን ጎል ጋር የመድረስ ችግር የለበትም ፤ ከመጀመሪያው ሳምንት ጀምሮ አሁን እስካለንበት። አሁንም የብስለት ጉዳይ ነው። የምናገኛቸው ኳሶች ለመሳት የሚከብዱ ናቸው። ግን ወጣቶች ናቸው ልምድ እያገኙ ሲሄዱ ይሻሻላል ብዬ አስባለሁ።