ቅድመ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከሽንፈት እና ከአቻ ውጤት በኋላ ወላይታ ድቻ እና ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚያፋልመው ጨዋታ ላይ ተከላዮቹ ነጥቦች ተነስተዋል።

ከሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ በሁለት ነጥቦች ብቻ የሚርቀው ወላይታ ድቻ ዳግም ሦስት ነጥብ በማግኘት የሊጉን መሪነት ለመቆናጠጥ ነገ ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርግ ይገመታል።

የአሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ቡድን ሊጉን በሽንፈት ቢጀምርም ሳይጠበቅ ቀስ በቀስ የደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ተገኝቷል። በተከታታይ የተመዘገቡት አዎንታዊ ውጤቶች ቡድኑን ለዋንጫ የሚፎካከር ቢያስመስሉትም በሰባተኛ ሳምንት በባህር ዳር ሦስት ለአንድ ከተረቱ በኋላ አሠልጣኙ “በግልፅ ለመናገር የእኛ ስብስብ ሊጉን ለማሸነፍ የተሰራ አይደለም” በማለት የሰጡት የድህረ-ጨዋታ አስተያየት የቡድኑን ዕቅድ የሚነግረን ነበር። ምንም ቢሆን ምንም ግን ከዚህም በኋላ በየጨዋታው የሚገኙ ውጤቶች ሳይጠበቅ በፉክክሩ ሊያዘልቀው ይችላል። ለዚህ ደግሞ ቡድኑ ጥቂት የግብ አጋጣሚዎችን ፈጥሮ እነሱን ወደ ግብነት የሚቀይርበት ንፃሬ ከፍ ማለቱ ነው። እንደ ተቀመጠበቅ ደረጃ ሰንጠረዥ ሦስተኛው የሊጉ ብዙ ግብ ያገባ ስብስብ ባለቤት የሆነው ድቻ በመልሶ ማጥቃት፣ በሽግግር እና በቀጥተኛ አጨዋወት ይሄንን ያህል ግብ ማስቆጠሩ የሚገርም ነው። ነገም በዚሁ የማጥቃት እሳቤ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ፈተናን እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

ለኳስ ቁጥጥር እምብዛም ቦታ የማይሰጠው ድቻ አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በራሱ ሜዳ የሚያሳልፍ በመሆኑ ያን ያህል የኋላ መስመሩ ተጋላጭ አይደለም። ይህ ቢሆንም ግን ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች (በፋሲሉ ጨዋታ እንዳልተቆጠረበት ልብ ይሏል) በድምሩ አምስት ግቦችን ማስተናገዱ እና በጨዋታዎቹ (ከሰበታ እና ባህር ዳር) የተቆጠሩት ግቦች ቁጥር ዘንድሮ ካስተናገዳቸው የላቁ መሆናቸው ሲታሰብ መጠነኛ መውረድ እንዳጋጠመው ይጠቁማል። እርግጥ ዋናዎቹ የመሐል ተከላካዮች ደጉ እና አንተነህ አለመኖራቸው ምናልባት ይህንን ክፍተት እንዳመጣው ቢታሰብም የመልካሙ እና በረከት ጥምረት ግን ለክፉ የሚሰጥ አይደለም። ነገም ቡድኑ የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች የያዘውን ጊዮርጊስ ስለሚገጥም በዚህ ረገድ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት።

ሰርቢያዊውን አሠልጣኝ ዝላትኮ ክራምፖቲች ካሰናበተ በኋላ ካደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አንዱን አሸንፎ አንዱን አቻ የወጣው ቅዱስ ጊዮርጊስ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት የሚገኙት ፋሲል እና ባህር ዳር ነጥብ መጣላቸውን ተከትሎ ነገ የሚገጥመውን ድቻ በማሸነፍ ወደ አናት ለመጠጋት ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

በስድስተኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ሀዋሳ ከተማን ሲረቱ ቀድሞ የሚታወቁበትን ቀጥተኝነት አግኝተው የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቀጣዩ ጨዋታ ይህንን ባህሪ ያስቀጥላሉ ተብሎ ቢጠበቅም የዋለለ እንቅስቃሴ ነበር ያደረጉት። በተለይ በሁለቱ መስመሮች የሚደረጉ ጥቃቶች እጅግ ተዳክመው የተመለከትን ሰሆን ነገ ግን ምናልባት ይህንን ከተነሳሽነት ሊመጣ የሚችል ክፍተት አርመው መቅረብ ከጨዋታው አዎንታዊ ነገር ይዞ ለመውጣት የሚረዳቸው ይመስላል። የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች (እስማኤል አውሮ-አጎሮ) የያዘው ጊዮርጊስ ዕድሎችን ብዙ አይፍጠር እንጂ በሳጥን ውስጥ አይምሬ አጥቂ አለው። ምንም እንኳን ድቻ ሳጥን ውጥ ፈዛዛ ባይሆንም ፈጣን እና ቁመታም አጥቂዎች ስለሚጠብቁት ሊፈተን ይችላል።

በአዳማው ጨዋታ ቡድኑ አይሸነፍ እንጂ የኋላው መስመር እጅግ የወረደ ጊዜ ነበር ያሳለፈው። በተለይ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ የማይጠፋው የመሐል ተከላካዩ ምኞት ደበበ በግል ያሳለፈው የጨዋታ ቀን መጥፎ ነበር። የኳስ ቅብብል ፣ የአቋቋም እና የሰዓት አጠባበቅ ስህተቶችን በተደጋጋሚ ሲሰራ የነበረው ተጫዋቹም ስህተቶቹ ወደ ግብነት አልተቀየሩም እንጂ ዋጋ የሚያስከፍሉ ነበሩ። ድቻ ሊከተለው ከሚችለው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት መነሻነት ደግሞ ይህ የላላው የኋላ መስመር እንዳይቀጣ ያሳስባል።

ወላይታ ድቻ በነገው ጨዋታ የወሳኝ አጥቂው ስንታየሁ መንግስቱን ግልጋሎት አያገኝም። ከዚህ ውጪ የግብ ዘቡ ቢኒያም ገነቱም ከጉዳቱ አለማገገሙ ተመላክቷል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ያለውን ወቅታዊ የቡድን ዜና ለማወቅ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ይህንን የዕለቱን ተጠባቂ ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ለሚ ንጉሴ የሚመሩት ይሆናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 14 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 6 ጊዜ ሲያሸንፍ ወላይታ ድቻ (አንድ ፎርፌ ጨምሮ) አምስቱን ድል አድርጓል። ቀሪዎቹን ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

– በአስራ አራቱ ጨዋታዎች ፈረሰኞቹ 19 ጎሎች ሲያስቆጥሩ የጦና ንቦቹ ደግሞ (ሦስት የፎርፌ ጎሎች ጨምሮ) 13 ጎሎች አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሠላለፍ

ወላይታ ድቻ (4-3-3)

ፅዮን መርዕድ

ያሬድ ዳዊት – ደጉ ደበበ – አንተነህ ጉግሳ – አናጋው ባደግ

እድሪስ ሰዒድ – ንጋቱ ገብረሥላሴ – ሐብታሙ ንጉሤ

ምንይሉ ወንድሙ – ቃልኪዳን ዘላለም – ቢኒያም ፍቅሬ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ቻርለስ ሉክዋጎ

ሱሌይማን ሀሚድ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሔኖክ አዱኛ

ያብስራ ተስፋዬ – ጋቶች ፓኖም – ሀይደር ሸረፋ

አቤል ያለው – እስማኤል አውሮ-አጎሮ – አማኑኤል ገብረሚካኤል