የዕለቱ ተጠባቂ የሆነው የወላይታ ድቻ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በሔኖክ አዱኛ አማካኝነት በተቆጠረ ብቸኛ ግብ ጊዮርጊስን አሸናፊ አድርጓል።
በሰባተኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር በባህር ዳር ከተማ የሦስት ለአንድ ሽንፈት የገጠማቸው ወላይታ ድቻዎች በመጀመሪያ አሰላለፋቸው ላይ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም የግብ ዘቡ ፅዮን መርዕድን ጨምሮ መልካሙ ቦጋለ፣ አበባየሁ አጪሶ እና ጉዳት ላይ የሚገኘው ስንታየሁ መንግስቱን በወንድወሰን አሸናፊ፣ አንተነህ ጉግሳ፣ ደጉ ደበበ እና እድሪስ ሰዒድ ተክተዋል። በምክትል አሠልጣኛቸው ዘሪሁን ሸንገታ ለሦስተኛ ተከታታይ ጨዋታ የሚመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ ከአዳማ ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ ከተለያዩበት ፍልሚያ አማካዩ ከነዓን ማርክነህን ብቻ በሀይደር ሸረፋ ተክተው ጨዋታውን ቀርበዋል።
ጨዋታውን በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ማከናወን የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ13ኛው ደቂቃ የጨዋታውን የሰላ የግብ ማግባት ሙከራ አሳይተዋል። በዚህም አቤል ያለው ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን የላከውን ኳስ በአስገራሚ ሁኔታ አንድም ተከላካይ ሳያየው ብቻውን ቆሞ የነበረው አማኑኤል ገብረሚካኤል አግኝቶት በቀኝ እግሩ ቢመታውም በዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የክለቡን ግብ የመጠበቅ ዕድል ያገኘው ወንድወሰን አሸናፊ አምክኖታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ከላይ ለተጠቀሰው የግብ ማግባት ዕድል መነሻ የሆነው አቤል በተመሳሳይ መስመር ከከንዓን የተላከለትን እና ፍጥነቱን ተጠቅሞ ያገኘውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ቢመታውም ወንድወሰን በድጋሜ መልሶታል።
ጨዋታውን በመቆጣጠሩ ረገድ ብልጫ የተወሰደባቸው ድቻዎች የጊዮርጊስ የኳስ ቁጥጥር ወደ ግብነት እንዳይቀየር ወደ ራሳቸው ሜዳ አፈግፍጎ መጫወትን መርጠው ቢንቀሳቀሱም አስደንጋጭ የመከላከል ክፍተቶችን እየፈፀሙ አሁንም ግብ ለማስተናገድ እየተቃረቡ ነበር። ከላይ ከተጠቀሱት ሁለት ጥሩ ጥሩ ሙከራዎች በተጨማሪም በ23ኛው ደቂቃ ከነዓን በሳጥን ውስጥ ሌላ ዕድል አግኝቶ በአጨራረስ ድክመት ሳይጠቀምበት የቀረውም አጋጣሚ የሚጠቀስ ነው። ይህ ቢሆንም ግን ከተከላካይ ጀርባ የሚላኩ ረጃጅም ኳሶችን እና የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎችን በመከተል ግብ ለማግኘት ሲጥሩ ነበር። ነገርግን አንድም ሙከራ በአጋማሹ ሳያደርጉ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል። ጊዮርጊስም የጨዋታ እና የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንዲሁም የተሻለ የግብ ሙከራ ድርሻ ቢኖረውም ከ23ኛው ደቂቃ በኋላ ሌላ ሙከራ ሳያደርግ የመጀመሪያውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አገባዷል።
የሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በሦስተኛው ደቂቃ ፈረሰኞቹ ሌላ ለግብ የቀረቡበት አጋጣሚ ተስተናግዷል። በዚህም የዓብስራ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ እስማኤል አውሮ-አጎሮ ራሱን አመቻችቶ ወደ ግብ የመታው ኳስ የግብ ዘቡን ቢያልፍም አናጋው ባደግ ደርሶ ከግብነት አግዶታል። ጫናዎችን ማምከን ላይ ተጠምደው የነበሩት ወላይታ ድቻዎች በ58ኛው ደቂቃ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ቻርለስ ሉኩዋጎን ለመፈተን ያደረጉት ሙከራ አስደንጋጭ ነበር። በዚህም በፈጣን የመልሶ ማጥቃት የተገኘውን የመጨረሻ ኳስ ምንይሉ አግኝቶት መረብ ላይ አሳረፈው ተብሎ ሲጠበቅ ተጫዋቹ ኳሱን ወደ ላይ አጉኖታል።
ጨዋታው 64ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመዓዘን ምት መነሻን ባደረገ ኳስ ወደ መሪነት ተሸጋግሯል። በተጠቀሰው ደቂቃም የመዓዘን ምቱ ሲመታ በረከት ወልደዮሐንስ በግንባሩ ሲያወጣው ከሳጥኑ ውጪ የነበረው ሔኖክ አዱኛ አግኝቶት በቀጥታ በመምታት መረብ ላይ አሳርፎታል። አንዱ ጎል ያላረካቸው ጊዮርጊሶች አሁንም የድቻ የግብ ክልልን እየጎበኙ መሪነታቸውን ለማስፋት ተንቀሳቅሰዋል። በተለይ በ80ኛው ደቂቃ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች የሆነው አውሮ-አጎሮ ከወደ ቀኝ ባደላ የሳጥኑ ክፍል ሙከራ ሰንዝሮ ነበር። ወላይታ ድቻዎች ለተቆጠረባቸው ጎል ምላሽ መስጠት ሳይችሉ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው ተጠናቋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሉን ተከትሎ ነጥቡን 14 በማድረስ ከነበረበት አምስተኛ ደረጃ ሁለት ደረጃዎችን በማሻሻል የወላይታ ድቻን ቦታ ሲረከብ ሦስት ነጥብ ያስረከበው ወላይታ ድቻ ደግሞ ከሦስተኛ ወደ አራተኛ ደረጃ ሸርተት ብሏል።