የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 0-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ

በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች ተከታዮቹን ሀሳቦች ሰንዝረዋል።

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም – ወላይታ ድቻ

ስለጨዋታው

እንደውጤት ተሸንፈናል ፤ ሦስት ነጥብ አጥተናል። ብናሸንፍ የተሻለ ነበር ግን ዛሬ ያየሁት ጥሩ ነገር የሜዳ ላይ እንቅስቃሴውን ነው ፤ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ። ኳስ ይዘን ለመጫወት የሞክርንበት መንገድ ለእኔ ተመችቶኛል። ብዙ ጊዜ እነሱ ቶሎ ቶሎ እንዳያጠቁን ኳስ እንከለክላቸው ነበር። ተጋጣሚያችን ቅዱስ ጊዮርጊስም የዋዛ ቡድን አይደለም። ተቀይረው የሚገቡ ተጫዋቾቻቸው ውጤት ቀያሪ ናቸው። ተሰላፊዎቻቸውም ልምድ ያላቸው ናቸው። በነበረው የስብስብ ጥራት ልዩነት እኛ ቀይረን ስናስገባ የነበረው ነገር ይወርዳል። እነሱ ቀይረው ሲያስገቡ ደግሞ የተሻለ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ። ዞሮ ዞሮ በኳስ ቁጥጥሩ ላይ የተሻለ ለውጥ አይቻለሁ ብዬ አስባለሁ።

የግብ ሙከራዎች ስለማነሳቸው

እኛ ለማሸነፍ ነው የገባነው። ሰው ሳይኖር ነው ልዩነቱ የሚታወቀው። የሥንታየሁ አለመኖር ብዙ ነገር ጎድቶናል ማለት ይቻላል። በግልፅ የሚታይ ነገር ነው። የአየር ላይ ኳስ አጠቃቀሙ ጥሩ ነው። እስካሁን ያገባናቸው ኳሶች በሥንታየሁ የሚገኙ ነበሩ። የእሱ እንቅስቃሴ እና ጥረት የሚታከልባቸው ነበሩ። ዛሬም ረጃጅም የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾችን ለመቆጣጠር ቢያንስ በተክለ ሰውነቱ ገዘፍ ያለ ተጫዋች ያስፈልግ ነበር። አሁንም ቢሆን እሱን አግዘን ወደ እንቅስቃሴ ማምጣት የውዴታ ግዴታ ነው ብዬ አስባለሁ።

በቅርብ ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር ስላለመቻላቸው

በተከታታይ የገጠሙን ቡድኖች በጣም ጠንካራ ናቸው። በሊጉ የሚጠበቁ ናቸው። በስብስብም ደረጃ ፋሲልም ባህር ዳርም ሆኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ የሚጠበቁ ናቸው። በእኛ በኩልም መሻሻል የሚገቡ ነገሮች ላይ መስራት ይጠበቃል።

አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለጨዋታው

የሰራነው እና ማድረግ የፈለግነው ነገር ነበር። ያን ማድረግ ችለዋል ፤ ብዙ የግብ ዕድሎችን አግኝተናል። ጎል ስር ስንደርስ የምንስታቸው ኳሶች ልዮላይ ዒላማ መጠበቅ እና ትኩረት እንጂ የፈለግኩትን እና አድርጉ ያልኳቸውን ነገር ነው ያደረጉት።

ስለአማካይ ክፍሉ አዲስ ጥምረት

ከእነሱም የምፈልገውን አግኝቻለሁ። ይበልጥ አጥቅቶ ለመጫወት እና ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል ለመሄድ ነበር የፈለግነው ኳሶቻችንን በትክክል መስርተን። ያልኳቸውን ነገር አድርገው ጥሩ ውጤት ይዘን ወጥተናል።

ከግቡ በኋላ በማጥቃቱ በኩል ስለመቀዛቀዛቸው

ውጤቱን ለማስጠበቅ እና ከታክቲካዊ ነገሮች አንፃር ነው። ጎሉንም መታሰቢያነቱን ለመንግሥቱ ወርቁ አድርገናል።

ስለመንግሥቱ ወርቁ የ11ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ

እኔንም ከወጣት ቡድን ያሳደገኝ ዋናው እና ትልቁ መንግሥቱ ወርቁ ነው። ለዛሬ ላለሁበት ትልቁን ነገር የሰጠኝ እሱ ስለሆነ ይህ ነገር ይገባዋል እላለሁ።