ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና አራተኛ ተከታታይ ድሉን አሳክቷል

በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ወልቂጤ ከተማን 1-0 አሸንፏል።

ወልቂጤ ከተማ ከጉዳት የተመለሰው ተከላካያቸው ውሀብ አዳምስን በአበባው ቡታቆ ከመተካታቸው በቀር ተጋጣሚዎቹ ባለፈው ሳምንት ለድል ያበቃቸውን አሰላለፍ ይዘው ገብተዋል።

በጥሩ መነቃቃት በተጀመረው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና የተሻለ አስፈሪነትን ተላብሶ ታይቷል። ከሚያንሸራሽራቸው ኳሶች በግራ መስመር ያደላ ጥቃት ለመሰንዘር ሲሞክር ይታይ ነበር። ከእነዚህ ውስጥ 4ኛው ደቂቃ ላይ የሮቤል ተክለሚካኤል እና አስራት ቱንጆ ጥምረት ከግራ አቅጣጫ ጥሩ ኳስ ወደ ውስጥ ቢያደርስም አቡበከር ናስር ተንሸራቶ ለማስቆጠር ያደረግው ሙከራ በዮናስ በርታ ጥረት ከሽፏል።


ቀስ በቀስ ወደ እርጋታ የመጡት ወልቂጤ ከተማዎች ግን የኢትዮጵያ ቡና የኳስ ምስረታ ሂደት ከግብ ክልሉ እንዳይወጣ ከፊት የተሳካ ጫና በማሳደር የጨዋታው እንቅስቃሴ ከግብ ክልላቸው እንዲርቅ ማድረግ ችለዋል። ቀጥተኛነት በቀላቀለ ጥቃታቸውም 12ኛው ደቂቃ ላይ በያሬድ ታደሰ ከጥን ውስጥ ያደረጉት ሙከራ ተጠቃሽ ነበር።

 

ከዚህ በኋላ ጨዋታው ፈጣን ሙከራዎችን ያሳየን 21ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ቡና ከተቸገረበት ከኋላ የመጀመር ጥረት ውስጥ በድንገት ከቀኝ አቅጣጫ በረጅሙ ወደ ሳጥን ውስጥ ኳስ ሲጥል ዊሊያም ሰለሞን ተቆጣጥሮ አስቆጠረ ሲባል ከመወሰኑ በፊት ተስፋዬ ነጋሽ አስጥሎታል። ይህ ኳስ በመልስ ምት ቡና ሳጥን ውስጥ ሲደርስ ደግሞ ጌታናህ ከበደ ከቀኝ አቅጣጫ ወደ ግብ የላከው የአጋማሹ አደገኛ ሙከራ በግቡ አግዳሚ ነበር የተመለሰው።


ከውሀ ዕረፍቱ በኋላ እንደመጀመሪያው ሁሉ የኢትዮጵያ ቡና ጥቃቶች ወደ ወልቂጤ ከተማ ሳጥን መድረስ ጀምረዋል። ያም ሆኖ የወልቂጤ የመሀል ተከላካዮች ጥምረት አቡበከርን እና የቡናን ጥቃት በአግባቡ ተቆጣጥረዋል። ወልቂጤዎች በሰጡት ምላሽ ዳግም ጥቃቱን ማርገብ ችለው ጨዋታው ወደ መመጣጠን መጥቷል። ቀሪው የአጋማሹ ደቂቃዎች ዊሊያም ከሳጥን ውጪ ጌታነህ ከበደ እና ኃይሌ ገብረትንሳይ ደግሞ ከቅጣት ምት ያደረጓቸውን ሙከራዎች ቢያሳዩንም ሁለቱን ግብ ጠባቂዎች የፈተኑ አልነበሩም።


ከዕረፍት መልስ ጨዋታው 50ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አግኝቷል። የቡናዎቹ ዊሊያም እና አቡበከር በወልቂጤ የማዕዘን ምት ከበኃሉ ተሻገር የቀሙትን ኳስ እየነዱ በመልሶ ማጥቃት ሳጥን ውስጥ ደርሰው ዊሊያም ከአቡበከር ተቀብሎ በጥሩ አጨራረስ መሪ ያደረጋቸውን ግብ አስቆጥሯል። ከግቡ በኋላ በሂደት እየተጋጋለ በመጣው ጨዋታ ሁለቱም በድኖች የማጥቃት ፍጥነታቸውን ጨምረው ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሲጥሩ ታይተዋል። ከሁሉም በላይ 68ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ ሁለተኛ አጋማሽ እያሳለፈ የነበረው ሮቤል ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ለአቡበከር ያሳለፈው ኳስ ሲሆን የአጥቂው ሙከራ በግቦሆ ጥረት ድኗል። ያም ሆኖ ይህ እንቅስቃሴ የአይቮሪኮስቱ ግብ ጠባቂ የመጨረሻ ነበር። በዛው ቅፅበት በኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ተከታታይ ቢጫ ካርዶች ከሜዳ ተወግዷል።


የቁጥር ብልጫ ያገኙት ቡናዎች የቅብብሎቻቸውን መቋጫ አቡበከር ናስርን በማድረግ በተሻለ ጫና ፈጥረዋል። ተጫዋቹ የጨዋታ ውጪ ውሳኔዎች ያደበዘዛቸው ሁለት ሙከራዎችን ማድረግ ችሎ ነበር። ወልቂጤዎችም በፊናቸው ፊት ላይ ፈጣን አጥቂዎቻቸውን ቀይረው በማስገባት የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ጥሩ ጥረት አድርገዋል።


ቡናዎች በጭማሪ ደቂቃዎች የወልቂጤን በር ደጋግመው አንኳኩተዋል። አቡበከር ከዊሊያም ተቀብሎ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል። አራተኛው ጭማሪ ደቂቃ ላይ ግን አቡበከር ተከላካይ ሳንጣቂ ኳስ ተቆጣጥሮ ለማግባት ያደረገው ጥረት ተቀይሮ በገባው ግብ ጠባቂ ሰዒድ ሀብታሙ ጥረት ሲድን ዊሊያም ተከላካዮችን አታሎ ወደ ግብ የመታው ፣ ቀጥሎ ወልቂጤዎች በስህተት ወደ ራሳቸው ግብ የላኩትን ከዚያም አቡበከር በግንባሩ የገጨውን ሦስቱንም ተከታታይ ኳሶች ውሀብ አዳምስ ከግቡ መስመር ላይ አፅድቷል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።


ድሉን ተከትሎ ነጥቡን ከባህር ዳር ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያስተካከለው ኢትዮጵያ ቡና ከ8ኛ ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ወልቂጤ ከተማ ከአምስት ወደ ስድስት ዝቅ ብሏል።