የድሬዳዋ ከተማ የይግባኝ አቤቱታ ውድቅ ሆኗል

ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በክርክር የቆየው ጉዳይ በመጨረሻም የድሬዳዋ ከተማን ይግባኝ ባለመቀበል ተጠናቋል።

አሰልጣኝ ፍስሀ ጥዑመልሳን በ2013 በተካሄደው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የጅማው ውድድር እስከተጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ ድሬዳዋ ከተማን በዋና አሰልጣኝነት ሲያገለግሉ ቆይተው በስምምነት መለያየታቸው ይታወቃል። ሆኖም ”በስምምነቱ መሠረት የውል ማፍረሻ ክፍያ እንደሚሰጠኝ ቃል ተገብቶልኝ ሳለ ክለቡ በምንም ጉዳይ ሊያናግረኝ አልፈለገም።” ሲሉ ቅሬታቸውን በመያዝ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በደብዳቤ አስገብተዋል።

የዲሲፒሊን ኮሚቴ የአሰልጣኙን ቅሬታ ተቀብሎ ክለቡ በሰባት ቀን ውስጥ በውላቸው ጊዜ ያልተከፈላቸው ደሞዝ እንዲከፍል ተወስኖበት ነበር። ይህ ውሳኔ ተገቢ አይደለም ይሻርልኝ በማለት ድሬዳዋ ከተማ ይግባኝ መጠየቁም ይታወሳል። ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴም ጉዳዮን ከመረመረ በኃላ የዲሲፒሊን ኮሚቴ ውሳኔን የሚሽር የተፈጠረ ፍሬ ነገር ሆነ የህግ ስህተት በቀረበው ማስረጃ ያላገኘን በመሆኑ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ውሳኔ አሳልፏል። በውሳኔው መሠረት የድሬዳዋ አቤቱታ ውድቅ ሆኖ አሰልጣኙ በውላቸው ጊዜ ያልተከፈላቸው ደሞዝ እንዲከፍል የተወሰነው ውሳኔ ተግባራዊ እንዲሆን አዟል።

አሰልጣኝ ፍስሀ ጥዑመልሳን ባሳለፍነው ዓመት ፈገግታን በሚጭሩ አስተያየታቸው በብዙዎች የስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ትኩረትን ይስቡ የነበሩ አሰልጣኝ መሆናቸው አይዘነጋም።