የስምንተኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ በሚከተለው መልኩ ተቃኝቷል።
በአራተኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር በወረቀት ላይ የዋንጫ ተፎካካሪ የሆነውን ባህር ዳር ከተማ ያሸነፈው አርባምንጭ ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ አሸናፊነት ዳግም ለመመለስ የሚያደርገው ጥረት ነገ ሲጠበቅ በሊጉ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ ጅማ አባጅፋርን ከረታ በኋላ ከድል ጋር መገናኘት ያልቻለው አዳማ ከተማም ሦስት ነጥብ አክሎ ደረጃውን ለማሻሻል የሚያደርገው ፍልሚያ ትኩረትን የሚስብ ይሆናል።
ሊጉን ዘንድሮ የተቀላቀለው አርባምንጭ ከተማ ያለፉትን ጨዋታዎች ለየት ባለ ሁኔታ የአጨዋወት ስልቱ ላይ ለውጥ ያደረገ ይመስላል። በመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች ከኳስ ጀርባ በመሆን ለመጫወት ሲሞክር እና የመስመር ተጫዋቾቹን ፍጥነት እና የፊት ተሰላፊዎቹን አካላዊ ቁመና ያገናዘበ ቀጥተኛ አጨዋወት ሲከተል ነበር። ሊጉ ከዕረፍት ከተመለሰ በኋላ ግን ኳስን ለመቆጣጠር ያለው ፍላጎት እምብዛም ለውጥ ባይስተዋልበትም የመከላከል መስመሩን ወደ ፊት ገፋ አድርጎ ተጋጣሚን ከሜዳው ጀምሮ አፍኖ በመጫወት ለስህተት ሲዳርግ እና ስህተቶቹን ተጠቅሞ ግብ ለማግኘት ሲውተረተር ነበር። ይህ አጨዋወት የተጫዋቾችን ጉልበት እጅግ የሚፈልግ ቢሆንም ነገም በዚሁ መንገድ ተዘጋጅቶ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይታሰባል።
ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች ነጥብ የተጋራው አርባምንጭ በእስካሁኖቹ ሰባት ጨዋታዎች የጠንካራ የተከላካይ ክፍል ባለቤት እንደሆነ ታይቷል። ትንሽ ግብ ካስተናገዱ ሦስት የሊጉ ክለቦች በመቀጠል የተቀመጠው አርባምንጭ በእንቅስቃሴ ደረጃ ጥሩ ብቃት እያሳየ ከጨዋታ ጨዋታ እየተብላላ ከመጣው አዳማ ከተማ ከባድ ፈተና እንደሚጠብቀው ይታመናል። በተቃራኒም ከሦስት ክለቦች ጋር በጣምራ የሊጉ ትንሽ ግብ ያስተናገደው አዳማም ለአርባምንጮች በቀላሉ ክፍተቶችን እንደማይሰጥ ይገመታል። እርግጥ አዳማ በሰባተኛ ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ሲጫወት ያን ያህል ጫና ኖሮበት በመከላከሉ ረገድ ባይፈተንም የአሚኑ እና ቶማስ ጥምረት የግብ ዘቡን በተደጋጋሞ ሲያጋልጥ አይታይም።
አዳማ ከተማ ከጊዮርጊስ ጋር ነጥብ ቢጋራም ካደረገው እንቅስቃሴ አንፃር ውጤቱ የሚያንስበት እንጂ የሚበዛበት እንዳልሆነ ተጉልህ ታይቷል። በተለይ በሙሉ 90 ደቂቃው ከነበራቸው ብልጫ እና ከፈጠሯቸው የግብ ዕድሎች አንፃር ጨዋታውን ማሸነፍ ይጠበቅባቸው ነበር። ነገርግን ፊት ላይ የነበራቸው የአፈፃፀም ግድፈት ሦስት ነጥብ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል። በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራው ክለቡ በመስመሮች በኩል የተጫዋቾችን ፍጥነት በመጠቀም ተደጋጋሚ አደጋ ሲፈጥሩ ይታያል(በተለይ አሜ እና ደስታ በተሰለፉበት ወገን)። ነገም ይህ የመስመር አጨዋወት የቡድኑ ዋነኛ የግብ ማግኛ አማራጭ እንደሚሆን እሙን ነው።
አርባምንጭ ከተማ አሸናፊ ፊዳን በቅጣት አብነት ተሾመን በጉዳት እንዲሁም እስከ አሁን ከክለቡ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ወደ ስብስቡ ያልተመለሰው አጥቂው ራምኬል ሎክን የማያገኝ ሲሆን ተካልኝ ደጀኔ እና ፍቃዱ መኮንን ግን ከገጠማቸው ጉዳት መመለሳቸው ተጠቁሟል፡፡ አዳማ ከተማ በበኩሉ ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ያላገለገለው አምበሉ ዳዋ ሁቴሳን ከጉዳት መልስ ያገኛል። ተጫዋቹ ከአጋሮቹ ጋር ሁለት ቀን ልምምድ ቢሰራም ግን የመሰለፉ ነገር ነገ እንደሚወሰን ተነግሮናል።
የሁለቱ ቡድኖችን ጨዋታ ፌዴራል አልቢትር ተፈሪ አለባቸው በመሐል ዳኝነት የሚመሩት ይሆናል።
እርስ በእርስ ግንኙነት
– ቡድኖቹ በሊጉ 12 ጊዜ ተገናኝተው አርባምንጭ 5 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን አዳማ 4 አሸንፏል። በቀሪዎቹ 3 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። አርባምንጭ 10 አዳማ 9 ግቦችንም በ12ቱ ግንኙነቶች አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሠላለፍ
አርባምንጭ ከተማ (4-4-2)
ይስሀቅ ተገኝ
ፀጋዬ አበራ – በርናንድ ኦቺንግ – ማሪቲን ኦኮሮ – ሙና በቀለ
ሀቢብ ከማል – እንዳልካቸው መስፍን – አንዱዓለም አስናቀ – ሱራፌል ዳንኤል
በላይ ገዛኸኝ – ኤሪክ ካፓይቶ
አዳማ ከተማ (4-3-3)
ጀማል ጣሰው
ሚሊዮን ሰለሞን – አሚኑ ነስሩ – ቶማስ ስምረቱ – ደስታ ደሙ
አማኑኤል ጎበና – ዮሴፍ ዮሐንስ – ዮናስ ገረመው
አቡበከር ወንድሙ – ዳዋ ሁቴሳ – አሜ መሐመድ