የመጀመርያው ፅሁፋችን ክፍል በሆነው የክለብ ትኩረታችን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ተከታዮቹን ጉዳዮች ታዝበናል።
👉 ሀዲያ ሆሳዕና ተከታታይ ድል አስመዝግቧል
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት መከላከያን በማሸነፍ የመጀመሪያ ድላቸውን ማሳካት የቻሉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ በሁለት አጋጣሚዎች ከመመራት ተነስተው በጨዋታው መጠናቀቅያ ደቂቃዎች ላይ ባስቆጠሯት ግብ የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ድል ማስመዝገብ ችለዋል።
በጨዋታው እርግጥ ሀዲያዎች ያስቆጠሯቸውን ግቦች ስለማጥቃት ጨዋታቸው መሻሻል ምስክር አድርጎ ለመውሰድ ቢከብድም ግብ ለማስቆጠር አለመቻላቸውን ተከትሎ የማሸነፍ ጫና ውስጥ ለቆየ ቡድን ግን በየትኛውም መንገድ የሚቆጠሩ ግቦችም ሆነ የሚመዘገቡ አውንታዊ ውጤቶች የቡድኑን ሥነልቦና በመገንባት ረገድ የሚኖራቸው ድርሻ ከፍ ያለ እንደመሆኑ ብዙ ትርጉም ያለው ድል ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
ሌላው በጨዋታው በሀዲያዎች በኩል የተመለከትነው አውንታዊ ነገር ቢኖር ቡድኑ በሁለት አጋጣሚዎች ቢመራም ተጫዋቾቹ ተስፋ ሳይቆጥሩ ባሳዩት ጥረት ድል ማድረጋቸው ነው።
ከባለፈው የጨዋታ ሳምንት ጀምሮ ዕድሎችን ወደ ግብነት በመቀየር ረገድ መሻሻሎችን እያሳየ የሚገኘው ቡድኑ በድምሩ ለ58 ያህል ደቂቃዎች እየተመራ ቢቆይም በሁለት አጋጣሚዎች አቻ ለመሆን ሲችል በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የማሸነፊያዋን ግብ ለማግኘት የነበራቸውም ጥረት የሚደነቅ ነው። በተለይም የመጀመሪያውን ግብ በሦስተኛው ደቂቃ ቢያስተናግዱም ውጤት መቀልበስ እንደሚችሉ በማመን በተረጋጋ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበረት አኳኋን ቡድኑ በአዕምሮ ደረጃ የተሻለ መነሳሳት ላይ እንደሚገኝ ማሳያ ነው።
ከባለፈው የጨዋታ ሳምንት አስቀድመው በሦስት ነጥቦች በሊጉ መጨረሻ ላይ ከሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር ከፍ ብለው ይገኙ የነበሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በሁለቱ ተከታታይ ድሎቻቸው ታግዘው ነጥባቸውን ወደ ዘጠኝ በማሳደግ ወደ አስራ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችለዋል።
👉 ድሬዳዋ ከተማ እና አወዛጋቢ ፍፁም ቅጣት ምቶች
በመጨረሻዎቹ ሁለት የጨዋታ ሳምንታት ብቻ ድሬዳዋ ከተማዎች አራት የፍፁም ቅጣት ምት ተሰጥቶባቸዋል። ይህም የቡድኑን አሰልጣኝ ጨምሮ የቡድኑን አባላት በጣሙን ቅር ያሰኘ አጋጣሚ ሆኗል።
በእግርኳስ ዳኝነት የሚወሰኑ ውሳኔዎች ተጋጣሚ ቡድኖች በሁለት ፅንፍ ማከራከራቸው አይቀሬ ነው። በተለይም የጨዋታን ውጤት በቀጥታ የመወሰን አቅም ያላቸው የቆሙ ኳሶች(ፍ/ቅ/ም) ዙርያ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ይበልጡኑ አከራካሪ ሲሆኑ ይታያል።
የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔዎች በራሳቸው አጨቃጫቂ ነገር ሊኖራቸው ቢችልም የድሬዳዋ ከተማ ላይ የተሰጡትን አራት ፍፁም ቅጣት ምቶች ተገቢ ናቸው አይደሉም ከሚለው ክርክር ወጣ ባለ መልኩ ሁነቱን መመልከት በተለይ ለምስራቁ ቡድን አባላት በቀጣይ ጊዜያት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ የሚረዳ ነጥብ ነው። ይህን ከማድረግ አንፃር ሂደቱ ስለቡድኑ የመከላከል እና የጨዋታ ወቅት አስተዳደር (Game Mangment) የሚያመለክትበትን አቅጣጫ መረዳት አንደኛው እርምጃ ይሆናል።
በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ አስራ አምስት ደቂቃዎች ጀምሮ የተሻለ የጨዋታ የበላይነት ወስደው ቢጫወቱም ቀስ በቀስ ግን ወደ ኃላ ሸሸት ብለው ለመጫወት ማሰባቸውን ተከትሎ ሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምቶች አጋጣሚዎች የተፈጠሩ ሲሆን በተመሳሳይ በሀዲያ ሆሳዕናውም ጨዋታ ቡድኑ በሁለት አጋጣሚዎች መሪ መሆን ቢችልም ውጤቱን ለማስጠበቅ የሄደበት መንገድ ውጤታማ አላደረገውም።
የፍፁም ቅጣት ምት አጋጣሚዎቹን ብሎም የተሰጡት ውሳኔዎች ምናልባት ድሬዳዋ ከተማዎች “ዕድለ ቢስ” በመሆናቸው የተገኙ ነበሩ አለፍ ሲልም ተበደሉ ብሎ ከመውሰድ ይልቅ ከጨዋታ ቁጥጥር ጋር አያይዞ መመልከቱ የተሻለ ነው። በዘመናዊ እግርኳስ አሰልጣኞች ቡድናቸው በጨዋታው የተሻለ የጨዋታ ቁጥጥር እንዲኖረው በማድረግ በአጋጣሚ ሊከሰቱ የሚችሉ ሁነቶችን (Coincidence) መቀነስ እንደሚቻል በማመን ጨዋታዎችን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ቦታ ሰጥተው ሲታትሩ ይስተዋላል።
እርግጥ የጨዋታ ቁጥጥር የሚለው ጉዳይ ብዙ መገለጫዎች ቢኖሩትም ከላይ የጠቀስናቸው የጨዋታ ወቅት አስተዳደር ማለትም ኳስ በተቻለ መጠን በተጋጣሚ እግር ስር እንዳይቆይ በማድረግም ሆነ ወደ ራስ የመከላከል ሲሶ የሚመጡ ኳሶችን ከምንጩ ለማስቀረት በሚረዳ አዎንታዊ መከላከል (Proactive Defending) እነዚህን ነገሮች ማስቀረት ይቻላል።
ታድያ ድሬዳዋ ከተማ ላይ የተሰጡት ፍፁም ቅጣት ምቶች ከአወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔዎች ሌላ ቡድኑ ጨዋታውን በሚገባ መቆጣጠር ባለመቻሉ የተገኙ መሆናቸውን በመረዳት ቡድኑ ጨዋታዎችን በመቆጣጠር ረገድ ያለበትን ክፍተት መቅረፍ ይኖርበታል።
👉 ወላይታ ድቻ እውነተኛ ተፎካካሪ ነውን?
በስድስተኛ የጨዋታ ሳምንት በሊጉ ይመሩ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች በትልቅ ደረጃ በተፈተኑባቸው የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ቡድኑ በአጋጣሚ እንጂ ለሰንጠረዡ አናት የታጨ ቡድን አለመሆኑን ለመታዘብ ችለናል።
በስድስተኛ የጨዋታ ሳምንት ከአምና አሸናፊው ፋሲል ከነማ እንዲሁም በተከታታይ በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ከሆኑት ባህር ዳር ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በተመሳሳይ ላለመሸነፍ ቅድሚያ በሰጠ የጨዋታ ዕቅድ ጨዋታቸውን ቢያደርጉም ከሦስቱ ጨዋታዎች ማግኘት የቻሉት አንድ ነጥብ ብቻ ነው።
ባለፉት የጨዋታ ሳምንታት በጥንካሬነት እናነሳ የነበረው የቡድኑ ውጤት ተኮር አቀራረብ በእነዚህ ጨዋታዎች ውጤታማ ሲሆን እየተመለከትን አንገኝም። ቅድሚያ ለመከላከል ሰጥቶ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ለመጫወት የሚፈልገው ቡድን በንፅፅር የጥራት ደረጃቸው ከላቁ ቡድኖች ጋር ሲገጥም ከመከላከል ባለፈ የመልሶ ማጥቃት ፍላጎቱ ደካማ የሆነ ቡድን ሆኖ እየተመለከትነው እንገኛለን።
እንደ የትኛውም አለመሸነፍን ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚገባ ቡድን በተጋጣሚው ቀዳሚ ግብ ሲቆጠርበት ወደ ሁለተኛ የጨዋታ ዕቅድ ለመግባት ሲቸገር የተመለከትነው ድቻ በእነዚህ ጨዋታዎች ከመከላከል ባለፈ ሊያጠቃ የሚችልበት መንገድ ላይ ሀሳቦች ሲያጥረው ፤ በተለይ በጊዮርጊሱ ጨዋታ ስንታየሁ መንግሥቱ አለመኖሩን ተከትሎ በግልፅ የተመለከተንበት አጋጣሚ ተፈጥሯል።
ጥሩ የሚባል የማሸነፍ ግስጋሴ ላይ የነበረው ቡድኑ አሁን ላይ ከዚያ የማሸነፍ ቅኝት የወጣ ይመስላል። የሊጉ ባህሪ ሆነና ከሦስት ጨዋታ አንድ ነጥብ አግኝተውም ቢሆን አሁንም ከመሪዎቹ በቅርብ ርቀት ቢገኙም አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በተደጋጋሚ እንደሚሉት የቡድኑ አወቃቀር ለሊጉ አሸናፊነት ሳይሆን በሊጉ ለመቆየት የተገነባ እንደመሆኑ አሁን ከእውነታው ጋር ታርቀው በሊጉ ጥሩ ደረጃን ይዘው ለማጠናቀቅ አስበው መስራት መጀመር ይኖርባቸዋል።
👉 የኢትዮጵያ ቡና ተከታታይ ድል
ሊጉን ደካማ በሆነ መንገድ የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጨረሻ አራት ጨዋታዎች ተከታታይ ድሎችን በማስመዝገብ ወደ ሰንጠረዡ አናት በመጠጋት ላይ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ቡና የቡድኑን የአዕምሮ ደረጃ ከፍ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን ተከታታይ አራት ድሎችን ቢያስመዘግብም አሳማኝ በሆነ መንገድ እያሸነፈ ይገኛል ብሎ መናገር ግን አይቻልም። ከአራቱ ድሎች ውስጥ ሦስቱ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት የተጠናቀቁ ሲሆን አንዱ ደግሞ በሁለት የፍፁም ቅጣት ምት ግቦች ድሬዳዋ ከተማን የረቱበት ጨዋታ ነው።
እንደ ካሣዬ አራጌ ዓይነት ከውጤቶች ባለፈ ውጤቱ ለሚመጣበት መንገድ ለሚጨነቅ አሰልጣኝ ብዙም ምቾት የሚሰጥ አካሄድ ባይሆንም ቡድኑ ከነበረበት ጫና አንፃር ተከታታይ ድሎቹ በጥሩ ጎናቸው የሚነሱ ናቸው።
ኢትዮጵያ ቡና በካሳዬ አራጌ የአሰልጣኝነት ዘመን ከሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ባለፈ የማሸነፍ ግስጋሴ ለማስመዝገብ ተቸግሮ ቢቆይም አሁን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችሏል። ይህም ቡድኑ ከደካማ አጀማመሩ ማግስት መሆኑ የተለየ ያደርገዋል።
👉 ብዙ ጥፋቶችን የሚፈፅመው አርባምንጭ ከተማ
ሊጉ ለዓለም ዋንጫ ማጣርያ ተቋርጦ ከተመለሰ ወዲህ በተወሰነ መልኩ የጨዋታ መንገዳቸውን ለውጠው የመጡት አርባምንጭ ከተማዎች ከፍተኛ ጫና አሳድረው ለመጫወት እየሞከሩ ሲሆን ከዚሁ ጋር ብዙ ጥፋቶችን ሜዳ ላይ እየሰሩ ይገኛል።
ከፍ ያለ ጫናን ተጋጣሚ ላይ አሳድሮ የመጫወት ግቡ ተጋጣሚ ባልተደራጀበት ወቅት ኳስን በሜዳው የላይኛው ክፍል ዳግም በማግኘት ፈጣን ጥቃቶችን ለመሰንዘር የሚያግዝ የመከላከል ዘዴ እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ ሂደት ተቀዳሚው ግብ የሆነው ኳስን በላይኛው የሜዳ ክፍል ማግኘት ሲሆን ሁሉም የጫና ዓይነቶች አተገባበራቸው ይለያይ እንጂ የሚከወኑት ከላይ የተጠቀሰውን ግን ለማሳካት ነው።
በዚህ ሂደት አርባምንጭ ከተማ ኳሱን ለማግኘት ከፍተኛ ፍጥነት እና ጉልበትን በቀላቀለ መንገድ ሲጫወት እንመለከታለን። በዚህ ሂደት ውስጥ ተጫዋቾቹ አላስፈላጊ ንክኪዎች ከተጋጣሚ ተጫዋቾች ጋር እየፈጠሩ በተደጋጋሚ ሂደቱ በጥፋቶች ሲቋረጥም ይስተዋላል።
እርግጥ የጨዋታ መንገዱ ጉልበት እና ፍጥነትን የቀላቀለ እንደመሆኑ ተደጋጋሚ አካላዊ ንክኪዎች እንደሚኖሩት ቢጠበቅም ጫና ለማሳደር ወደ ላይ ከፍተው የሚሄዱት ተጫዋቾች ተቀዳሚው ግባቸው ኳሱን አድርገው መንቀሳቀስ ይኖርባቸው። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ሂደቱ በተደጋጋሚ በጥፋቶች የሚቋረጥ ከሆነ ተጋጣሚዎች በቆመ ኳስ ፣ ከመጀመሪያዎቹ አነስተኛ በሆነ ጫና እና በተለያየ አማራጭ ሊወጡበት የሚችሉበትን መንገድ ሊፈጥር ስለሚችል ጫና መፍጠራቸውን ዋጋ ሊያሳጣው ይችላል።
የጨዋታ መንገዱ በራሱ በጣም መቀናጀት ፣ በህብረት መንቀሳቀስ እና ማመንን የሚጠይቅ ቢሆንም ይህን ሂደት የተሳለጠ ለማድረግ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ይታመናል። በመሆኑም አርባምንጭ ከተማዎች ይህን የጨዋታ መንገድ በሂደት እያሳደጉት ሲሄዱ መሰል ችግሮችን እየተቀረፉ ይመጣሉ ተብሎ ተስፋ ይደረጋል።
👉 ሽግሽጎች የበዙበት ጅማ አባ ጅፋር
በሊጉ በአንድ ነጥብ በሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር ደካማ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል። ከስብስብ ጥልቀት አንፃር ብዙ ችግሮች የሚነሱበት ቡድኑ ይህን ለመቅረፍ ተጫዋቾችን በማሸጋሸግ እየተጠቀመ ይገኛል።
በላይ አባይነህ ከአጥቂ መስመር ተሰላፊነት ወደ መሀል ተከላካይነት ተቀይሮ የመጫወቱ ጉዳይ ብዙ ያነጋገረ ቢሆንም በየጨዋታው እየተመለከትን የምንገኘው የተጫዋቾች ተደጋጋሚ የሚና ለውጥ እየተለመደ መጥቷል። እንደውም በቀላል አገላለፅ ከግብ ጠባቂው ውጪ ያሉት የሜዳ ላይ ተጫዋቾች ከዚህ ቀደም ከለመዱት ሚና ውጪ እየተጠቀሙባቸው ይገኛል ቢባል ማጋነን አይሆንም። በተጨማሪም ተጫዋቾቹ ጨዋታው ሲጀመር ይዘውት ወደ ሜዳ ከሚገቡት ሚና ሌላ በጨዋታው ሂደት የሚደረጉ ተደጋጋሚ ፍሬያማ የሆኑ ለውጦችን እየተመለከትን አለመገኘታችን አሰልጣኝ አሸናፊ ቡድኑን መልክ ለማስያዝ ምንኛ እየተቸገሩ እንደሚገኝ ማሳያ ነው።
ለአብነትም በሰበታ ከተማ 1-0 በተሸነፉበት የዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በርከት ያሉ ተጫዋቾች ያለ ተፈጥሮአዊ የመጫወቻ ስፍራቸው ሲጫወቱ ተመልክተናል።
ከበላይ አባይነህ ተከላካይነት ሌላ ከኃላ ክፍሉ ፊት ከነበሩት አምስት አማካዮች ውስጥ እዮብ አለማየሁ ከመስመር አማካይነት ወደ ወደ መስመር ተመላላሽት ፣ ሚኪያስ ግርማ ከመስመር ተከላካይነት ወደ መሀል አማካይነት ፣ ዱላ ሙላቱ ከመስመር አማካይነት ወደ መሀል አማካይነት ፣ መስዑድ መሀመድ ጭምር ከጥልቀት ከመነሳት ይልቅ ወደ ፊት ተገፍቶ ሲጫወት አይተናል።
በዚህ መልኩ ጨዋታውን የጀመረው ቡድኑ በጨዋታ ወቅት ተደጋጋሚ የሚና መሸጋሸጎች ሲደረግም አስተውሏል። ከእነዚህ መሸጋሸጎች ጀርባ ያለው ያለው ስልታዊ ጉዳዮች በውል ባይታወቁም ሜዳ ላይ ግን ቡድኑ በእነዚህ መሸጋሸጎች ውስጥ ይህ ነው የሚባል የሚታይ ለውጥ ማሳየት ተቸግሯል።
ተቀይረው ወደ ሜዳ ከገቡ ተጫዋቾች ውስጥም አስናቀ ሞገስ ከመስመር ተከላካይነት ይልቅ በመሀል አማካይነት ፣ ኢዳላሚን ናስር ከመሀል ተከላካይነት ይልቅ በፊት አጥቂነት ከጠቀማቸው ችግሩ ምን ያህል ስር የሰደደ እንደሆነ መረዳት ይቻላል።
በጨዋታ ወቅት ከተመለከትናቸው የሚና ለውጦች መካከል በላይ አባይነህ በመሀል ተከላካይነት ጨዋታውን ቢጀምርም በእንቅስቃሴ ደስተኛ ያልነበሩት አሰልጣኝ አሸናፊ በመጀመሪያው አጋማሽ ተቀይሮ ከመውጣቱ በፊት ወደ መስመር ተመላላሽነት ሚናውን ለውጦ እንዲጫወት ያደረጉት ሲሆን በምትኩም ዱላ ሙላቱ ሦስተኛው የመሀል ተከላካይ ሆኖ እንዲጫወት ተደርጎ ተመልከትናል። በመቀጠልም ዱላ በሁለተኛው አጋማሽ በመስመር ተመላላሽነትም እንዲሁ እንዲጫወት ሲደረግ ተመልክተናል።
ይህን ጨዋታ ለአብነት አነሳን እንጂ ሂደቱን በቀደሙት የጨዋታ ሳምንታትም በተለያየ መጠን ሜዳ ላይ ስንመለከት ቆይተናል።
ከዚህ አንፃር በአማራጮች እና በተጫዋቾች ጥራት ችግር እየተፈተነ የሚገኘው ቡድኑ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እስከ ውድድሩ አጋማሽ ድረስ በምን መልኩ ይደርሳል የሚለው ነገር በቀጣይ ይጠበቃል።