ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

Read Time:5 Minute, 10 Second

የ8ኛ ሳምንት ዓበይት አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች በሦስተኛው ፅሁፋችን ተመልክተናል።

👉 የአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው አስተያየቶች ዕውነታን ይገልፃሉ ?

“በመጀመሪያው አጋማሽ ከፍተኛ የማጥቃት ብልጫ ነበረን።…. ዛሬ ኳስ የሚይዝ ቡድን ጋር ነው የተጫወትነው ግን የተመለከታችሁት ነገር ግን የተገላቢጦሽ ነበር። በጣም አጥቅተን ተጫውተናል…..”

“ቡድኖች ያገቡትን ኳስ አስጠብቀው ለመውጣት ነው የሚጫወቱት። ዛሬ ሰው ወጥቶብን እንኳን ኢትዮጵያ ቡና ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት ነው የተጫወተው። እና ስመለከተው አሰልጣኞች ላይ ጭንቀትም አለ። እኔ ነፃ ሆኜ ነው የምሰራው በሌሎች ቡድኖች ላይ ግን የተመለከትኩት ነገር ይህንን ነው። አሰልጣኞች ሲረጋጉ ወደፊት ይህ ነገር ይቀረፋል የሚል ዕምነት አለኝ።” ይህ ሀሳብ አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው በኢትዮጵያ ቡና 1-0 ከተሸነፉበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሰጡት አስተያየት ነው።

አሰልጣኞች ከጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ በሚኖራቸው የድህረ ጨዋታ አስተያየት ሜዳ ላይ ሰፊው የእግርኳስ ተመልካች በገሀድ ከተመለከተው የሜዳ ላይ እውነታ ጋር የሚጣረሱ ሀሳቦችን ሲሰጡ ማድመጥ በእኛ ሀገር እግርኳስ የተመለደ ሂደት ነው።

ለአብነትም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ወልቂጤ ከተማ በኢትዮጵያ ቡና 1-0 ከተረታበት ጨዋታ በኋላ ከላይ ያቀረብነው የአሰልጣኝ ጳውሎስ አስተያየት ማሳያ ነው። በጨዋታው የነበረው እውነታ አሰልጣኙ ካሉት በተቃራኒ ስለመሆኑ ቁጥሮች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።

በጨዋታው ወልቂጤ ከተማዎች በተጋጣሚያቸው ኢትዮጵያ ቡና በኳስ ቁጥጥር 67% ለ33% በሆነ ልዩነት ብልጫ የተወሰደባቸው ሲሆን በግብ ሙከራ ረገድም ኢትዮጵያ ቡና 10 ሲያደርግ ወልቂጤ ግን 5 ብቻ ነበር ያደረገው በተጨማሪም ኢላማቸውን በጠበቁ ሙከራዎችም ኢትዮጵያ ቡና 5 ማድረግ ሲችል ወልቂጤ ከተማዎች ግን 2 ብቻ ነው ማድረግ የቻሉት።

ታድያ በዚህ ደረጃ በሚታይ መልኩ በተጋጣሚ ብልጫ የተወሰደበት ቡድን አሰልጣኝ በጨዋታው የተሻሉ እንደነበሩ የሚገልፅ ሀሳብ ሲሰጥ መመልከት ግራ የሚያጋባ ነው።

በ8 ሳምንት የሊጉ ጉዞ በአማካይ 46% የኳስ ቁጥጥር ያለው ወልቂጤ ከተማ ከሁለት ጨዋታዎች ውጪ በተቀሩት ስድስት ጨዋታዎች በተጋጣሚው በኳስ ቁጥጥር ረገድ ብልጫ የተወሰደበት ሲሆን በተመሳሳይ በአማካይ በጨዋታ ስድስት የግብ ሙከራዎችን የሚያደርገው ቡድኑ በሙከራዎችም ረገድ በተመሳሳይ ከአንድ ጨዋታ ውጪ በተጋጣሚዎቹ ብልጫ ሲወሰድበት ተመልክተናል።

ከግብ ዕድሎች ጥራት አንፃር ስነመለከተው ቡድኑ በአማካይ በጨዋታ 2.25 ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን የሚያደርግ ሲሆን ከሁለት ጨዋታዎች ውጪ ባሉት ስድስት ተጫዋች በተጋጣሚው ተበልጧል አልያም ተመሳሳይ መጠን ያለው የግብ ሙከራዎችን ስለማድረጉ ቁጥሮች በግልፅ ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ቡናውን ለአብነት አነሳን እንጂ አሰልጣኙ በቀደሙት ጨዋታዎችም ተመሳሳይ አይነት ይዘት ያላቸው ከሜዳ ላይ እውነታው የተጣረሱ ሀሳቦችን ሲያነሱ አድምጠናል።

ቡድናችን እንደሚታየው አጥቅቶ የሚጫወት ቡድን ነው…ብዙም የምንፈራው ነገር የለም።

አስደሳች ጨዋታ ነው የምንጫወተው… ወደፊት በሄድክ ቁጥር ደጋፊው ተመልካቹ ደስተኛ ነው የሚሆነው።

ከወልቂጤ ከተማ ዘንድሮ ብዙ ነገር ጠብቁ ብዙ ነገር ታያላቹሁ…

…ምንም ችግር የለውም እኛ ብዙ ፍፁም ቅጣት ምት እንደምናገኝ ጨዋታችን በግልፅ ይናገራል።

ኳስ ተቆጣጥረው እንዳይጫወቱ ብዙ ዱላ በዝቶባቸው ነበር። በዚህ ምክንያት እንዳሰብነው አልሆነም።

ከላይ በወፍ በረር የቃኘናቸው ሀሳቦች አሰልጣኙ በተለያዩ አጋጣሚ በነበራቸው ድህረ ጨዋታ ቃለመጠይቆች ካነሷቸው ሀሳቦች በጥቂቱ የተቀነጨቡ ናቸው።

በአሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው አምሳያ የተገነባው ቡድኑ ለማጥቃት ሆነ ለኳስ ቁጥጥር የተሰራ ቡድን እንደነበረ መረዳት ይቻላል። አሰልጣኝ ጳውሎስም እርግጥ በቀደሙት ቡድኖቻቸው ከጨዋታ መንገድ ይልቅ ለውጤት ቅድሚያ የሰጠ ቡድኑን ገንብተው እንደመመልከታችን የተረከቡትን ቡድን ኳስን ተቆጣጥሮ ማጥቃት በሚለው ሀሳብ ውስጥ እንዲቀጥል እያደረጉ መሆኑን እየተመለከትን ብንገኝም በስምንት ጨዋታ አምስት ብቻ ግቦችን ያስቆጠረውን ቡድናቸውን አሰልጣኙ በሚሉት ልክ ነው ብሎ ለመውሰድ ይቸግራል።

👉 ከአሸናፊ ጋር መቀጠል ወይንስ መለያየት?

የ2010 የሊጉ አሸናፊ ጅማ አባ ጅፋር አሁን ላይ ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ በሊጉ ግርጌ በአንድ ነጥብ ተቀምጠዋል። ታድያ ይህን ሂደት ለመቀልበስ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ ነው።

ከቀናት በፊት ለአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እና ረዳቶቻቸው የቡድኑን ውጤት በፍጥነት እንዲያስተካክሉ ደብዳቤ እንደተሰጣቸው መዘገባችን ይታወሳል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ቡድኑ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ሽንፈት ማስተናገዱን ተከትሎ ጫናዎቹ ይበልጥ እየበረቱ ይገኛል።

በየተኛውም ቡድን ውጤት ሲጠፋ እንደሚሆነው አሰልጣኞች ላይ ጫና የመበርታቱ ነገር የሚጠበቅ ቢሆን የዘንድሮውን የጅማ አባ ጅፋር አካሄድ የተለየ እንደመሆኑ የአሰልጣኙም ጉዳይ በተወሰነ መልኩ ትኩረት የሚሻ ነው።

ደካማ የምልመላ ሂደትን አሳልፎ የውድድር ዘመኑን የጀመረው ቡድኑ በምልመላ ሂደት የተሰሩ የአካሄድ ስህተቶች እየጎዱት እንደሚገኝ እየተመለከትን እንገኛለን። ለተበላሸው የምልመላ ሂደት አሰልጣኙም ሆነ ሌሎች የክለቡ አስተዳደር ሰዎች እንደየ ድርሻቸው ተጠያቂ መሆን ግን ይገባቸዋል።

የበቁ ተጫዋቾችን ከክለብ ክለብ በማዘዋወር ቡድን መገንባት ያልተፃፈ ህግ በሆነበት ሊጋችን በአሰልጣኝ አሸናፊ ደረጃ ያለን አሰልጣኝ ያለበቂ ሰራዊት ለፍልሚያ እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ ባለው ውስን አቅርቦት የሚፈለገውን ውጤት በፍጥነት ካለመጣህ ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው። አሰልጣኞች ስኬታቸው መለካት ያለበት የያዙትን ግብአት አሳድገው (Maximize) አድርገው በቡድኑ አውድ ስኬታማ ናቸው አይደሉም በሚለው መመዘኛ እንጂ ፍላጎታቸው ሳይሟላ የቡድኑ አስተዳደር ስኬት ነው ብሎ ባስቀመጠው መመዘኛ ሊሆን አይገባም።

እርግጥ ቡድኑ አሁን ላይ የሚገኝበት ደረጃ እጅግ አስቸጋሪ መሆኑ ባያጠያይቅም ወደ ውጤታማነት ለመመለስ አሰልጣኙ አቅም እንዳላቸው የቀደመው የሥራ ማህደራቸው ያሳያል። በዚህ ወቅት ግን አሰልጣኝ መቀየሩ በእርግጠኝነት ነገሮችን አይቀይርም ብሎ መናገር ባይቻልም ተጨማሪ ስጋት (Risk) ያለው ውሳኔ ከመወሰን ይልቅ በአሰልጣን አሸናፊ ላይ ዕምነት አሳድሮ መቀጠሉ የተሻለው አማራጭ ይመስላል።

አሰልጣኙ እስከ ውድድሩ አጋማሽ በቡድኑ የሚቆዩ ከሆነ እና በተወሰነ መልኩ ከበላዮቻቸው ከሚገኙ ቡድኖች ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት በጣሙን የሚሰፋ ካልሆነ በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ጥቂት ቡድኑን ማሻሻል የሚችሉ ተጫዋቾችን ማዘዋወር የሚችሉ ከሆነ ካላቸው ልምድ አንፃር ቡድኑን በሊጉ ለማቆየት በሚደረገው ትግል እንዲያሰራራ ሊያግዙት ይችላል።

👉 ወጣት ግብ ጠባቂዎች ጉዳይ

በሊጋችን በአንድ ወቅት ቁጥራቸው በጣሙን አይሎ የነበረው የውጪ ግብ ጠባቂዎች አሁን ላይ በተወሰነ መልኩ ተፅዕኗቸው እየቀነሰ በምትኩ ወጣት ኢትዮጵያዊያን ግብ ጠባቂዎችን በስፋት እየተመለከትን እንገኛለን።

Abrham, [12/20/2021 9:19 AM]
በአሁኑ ወቅት በሊጉ ተካፋይ ከሆኑ አስራ ስድስት ቡድኖች ውስጥ ስድስቱ (37.5%) በቋሚነት የውጪ ሀገራት ዜግነት ያላቸው ግብጠባቂዎችን ሲጠቀሙ አመዛኙ ማለትም አስር (62.5%) ቡድኖች ኢትዮጵያዊያን ግብ ጠባቂዎችን እየተጠቀሙ ይገኛል።

ይህ ቁጥር በተለይ ባለፉት ሦስት የውድድር ዘመናት የሀገራችን ግብ ጠባቂዎች ቁጥር ጭማሬን እያሳየ እንደሚገኝ ይጠቁማል። በተለይም ደግሞ አሁን ላይ እየተለመከትን የምንገኘው አዝማሚያ ደግሞ በሊጉ የመጫወት ልምድ የሌላቸው አዳዲስ ግብ ጠባቂዎችን ኃላፊነት የመስጠትን ጉዳይ ነው።

ዳንኤል ተሾመ ፣ አላዛር ማርቆስ ፣ ይስሀቅ ተገኝ ፣ ያሬድ በቀለ ፣ ዋኬኔ አዱኛ ፣ አቡበከር ኑሪ የመሳሰሉ ወጣት የግብ ጠባቂዎች ዕምነት ተጥሎባቸው መሰለፍ መቻላቸው በመልካምነቱ የሚጠቅስ ጉዳይ ነው። ይህም ሂደት ከጥቂት ዓመታት በፊት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በየክለቦቻቸው በተጠባባቂነት አመዛኙን የውድድር ዘመን ያሳለፉ ግብ ጠባቂዎችን ለመምረጥ አሰልጣኞች ይገደዱ ከነበረበት ጊዜ አንፃር ሲነፃፃፀር አሁን ላይ በሊጉ በርከት ያሉ ኢትዮጵያዊያን ግብ ጠባቂዎችን መመልከት መቻላችን ትሩፋቱ በቀላል የሚታይ አይደለም።

አሰልጣኞች ከቀደመው የውጪ ሀገራት ዜግነት ያላቸው ግብ ጠባቂዎች ላይ ከልክ ያለፈ ዕምነት ማሳደራቸውን ትተው እግርኳሳዊ መርህን እና ወቅታዊ ብቃትን መሰረት ባደረገ አካሄድ ይበልጥ ኢትዮጵያዊያን ግብጠባቂዎችን ተመራጭ ማድረግ መጀመራቸው መልካም የሚባል ሂደት ነው።

👉 የዘላለም ሽፈራው እና ሰለሞን ደምሴ ደስታ አገላለፅ

ሰበታ ከተማ የመጀመሪያውን ድል ባስመዘገበበት የ8ኛ ሳምንት ጨዋታ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሰበታ ከተማው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው እና ተጠባባቂ ግብ ጠባቂያቸው ሰለሞን ደምሴ ያሳዩት የደስታ አገላለፅ አስገራሚ ነበር።

የጨዋታውን መጠናቀቅ የሚያበስረው ፊሽካ መናፈቱን ተከትሎ ግብ ጠባቂው በፍጥነት እየሮጠ በመሄድ አሰልጣኙ ላይ ተንጠልጥሎ ደስታውን የገለፀበት መንገድ የተለየ ነበር።

በሀገራችን እግርኳስ በአሰልጣኞች እና በተጫዋቾች መካከል በተለይ በቀደመው ጊዜ የነበረው ግንኙነት “የአለቃ እና ምንዝር” ዓይነት መፈራራት ላይ ያተኮረ ነው በሚል ተደጋጋሚ ወቀሳዎች ሲቀርቡ ይደመጣል። ነገር ግን አሁን ላይ መሻሻሎችን እየተመለከትን እንገኛለን።

በተጫዋቾች እና በአሰልጣኞቻቸው መካከል ያለው ግንኙነት በመርህ እና መከባበር ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ይጠበቃል። ይህም የቤተሰባዊነት ስሜትን በመፍጠር ለአንድ አላማ በጋራ ለመቆም የሚረዳ ነው።

ጠንካራ ህብረት ደግሞ ለጠንካራ ቡድን መሰረት በመሆኑ በተጫዋቾች እና አሰልጣኞች መካከል ያለው ግንኙነት መከባበርን መሰረት ባደረገ መልኩ ለቀቅ ያለ ይዘት ሊኖረው ይገባል።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
ያጋሩ
error: Content is protected !!