ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

የጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻው ትኩረታችን ደግሞ የሳምንቱ ሌሎች ትኩረት ይሻሉ ያልናቸው ጉዳዮች ናቸው።

👉 የታላቁ ሰው ዝክር. . . 

ባለታሪኮችን በሚመጥናቸው ልክ መዘከር እንደ ሀገር ያልተሻገርነው ትልቅ ተግዳሮታችን ነው። ባለታሪኮችን በመዘከር የነገዎቹን ታሪክ ሰሪዎች ማብቃት ላይ ባለመስራታችን እንደ ሀገር ትላንታችንን ረስተን በዛሬ ጉዳዮች ላይ ብቻ እንድናተኩር ሆነናል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ውስጥ ከክብር ይድነቃቸው ተሰማ ቀጥሎ በብዙ ከሚነገርላቸው ህያዋን መካከል የሆኑት የሀገር ባለውለታው መንግሥቱ ወርቁ 11ኛ ሙት ዓመት ባሳለፍነው ሳምንት (ታህሳስ 8) መሆኑን ብዙ ታሪክ የሰሩበት የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ደጋፊዎች ከወላይታ ድቻ ጋር በነበራቸው ወቅት እሳቸውን ለመዘከር በተጫዋችነት ዘመናቸው ይለብሱት የነበረው እና በክለቡ ለክብራቸው መታሰቢያ እንዳይለበስ በተደረገው “8” ቁጥር ቅጥር ቅርፅ የተሰራ የፕላስቲክ የአየር ከረጢት በሜዳው ይዘው ተመልክተናል።

ይህን ተከትሎ በድህረ ጨዋታ ቃለ መጠይቆች በመንግሥቱ ወርቁ ስር የመሰልጠን ዕድል ያገኘው ዘሪሁን ሸንገታ እና የኢትዮጵያ ቡናው ካሳዬ አራጌ መንግሥቱ ወርቁን በተመለከተ ሀሳባቸውን እንዲያገሩ ተደርጓል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ በተጫዋችነት ፣ በአሰልጣኝነትም ሆነ በኢንስትራክተርነት ለሀገራችን እግርኳስ ትልቅ ውለታን የዋለው ባለ”8″ ቁጥሩ ባለሟል በእግርኳሳችን ያበረከተው ታላቅ አስተዋጽኦ ከመቃብር በላይ ህያው ነው።

በቀጣይ ግን መንግሥቱ ወርቁንም ሆነ ሌሎች የሀገር ባለውለታዎችን ተገቢ የሆነ እውቅና እና ክብር መስጠት አስፈላጊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አሁንም በዚህ ረገድ የተሻሉ ነገሮችን ለመመልከት እንጓጓለን።

👉 በድንገት የጨለመው የስታዲየም መብራት

በ8ኛ የጨዋታ ሳምንት ሰበታ ከተማ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ባደረጉት ጨዋታ 25ኛ ደቂቃ ላይ በድንገት በስታዲየሙ የግብ እንግዶች መቀመጫ አቅጣጫ ያሉት ሁለት የስታዲየም ፖውዛዎች አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን ተከትሎ ጨዋታ ሊቋረጥ ችሏል።

በወቅቱ በአካባቢው በነበረው ከፍተኛ ንፋስ የቀላቀለ የአየር ንብረት ጋር ተያይዞ ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር መነሻነት ጨዋታው ለ13 ያህል ደቂቃዎች ተቋርጦ ሊቀጥል ችሏል።

መሰል ቴክኒካዊ እክሎች አያጋጥምም ባይባልም በእኛ ሀገር አውድ ግን በዚህ ፍጥነት ምላሽ ለመስጠት የተደረገው ርብርብ ይበል የሚያሰኝ ነው። በቀጣይም መሰል እክሎች ቢያጋጥሙ እንኳን አፋጣኝ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ለመስጠት ከዚህ የበለጠ ዝግጁነት ሊኖር ይገባል።

👉 ገብረክርስቶስ ቢራራ በተንታኝነት ብቅ ብለዋል

በታችኞቹ የሊግ እርከኖች ዲላ ከተማን ዘለግ ላለ ጊዜ ያሰለጠኑት እና በፕሪሚየር ሊጉም ደቡብ ፖሊስ እና ወላይታ ድቻን በማሰልጠን የምናውቃቸው አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከቆይታ በኋላ በተንታኝነት ተመልክተናቸዋል።

ለአሰልጣኝነት ከገንዘብ ይልቅ የተሻለ የስራ ከባቢ ያስፈልጋል በሚለው ዕምነታቸው የሚታወቁት አሰልጣኙ ከወላይታ ድቻ ጋር ከተለያዩ ጊዜ አንስቶ በሥልጠናው ወደ ሁለት ዓመት ለተጠጋ ጊዜ ሳንመለከታቸው መቆየታችን አይዘነጋም። ታድያ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በሱፐር ስፖርት የጨዋታ ተንታኝነት መልካም የሚባል ቆይታን አድርገዋል።

በነበራቸው የስምንት ጨዋታ ቆይታ ሀሳባቸውን በመግለፅ ረገድ ችግር እንደሌለባቸው ያስመሰከሩት አሰልጣኙ የጨዋታ አረዳዳቸውም ሆነ ታክቲካዊ ግንዛቤያቸው እንዲሁም በሀገራችን እግርኳስ ብዙም ትኩረት ባለገኙት ሳይንሳዊ በሆኑ አዕምሯዊ እና ከአካላዊ ዝግጁነት ዙሪያ ያነሷቸው የነበሯቸው ጉዳዮች ጥሩ የሚባሉ ነበሩ።

👉 የመጀመሪያው የደጋፊዎች ቅጣት

በ2012 የውድድር ዘመን በኮቪድ ወረርሽን ሊጉ ከተቋረጠ ወዲህ በአምና የውድድር ዘመን እጅግ ውስን ያላቸው ደጋፊዎች ወደ ሜዳ እንዲገቡ መደረጋቸውን ተከትሎ በስታዲየሞች ይታይ የነበረው ሥርአት አልበኝነት የቀነሰ ቢያስመስለውም ዘንድሮ ወደ ሜዳ የሚገቡ ደጋፊዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ የማገርሸት አዝማሚያ እየተመለከትን ነው።

ደጋፊዎች በቁጥር በርከት ብለው ሜዳ ላይ መመልከታችን ለእግርኳሱ ከፉክክር ሆነ ከውበት አንፃር የሚጨምርለት ነገር እንዳለ ባይካድም እንደ እኛ ሀገር ደግሞ የደጋፊዎች የሜዳ ላይ ሥርአት አልበኝነት እዚህም እዚያም በሚታይበት ሁኔታ ይህን ሁኔታ በአግባቡ መያዝ ይሻል።

በእስካሁኑ የሊጉ የ8 ሳምንት ጉዞ በተለያዩ ጨዋታዎች መሰል ያልተገቡ ድርጊቶችን ፍንጮችን እየተመለከትን እንገኛለን ፤ ለማሳያነትም በመሰል ድርጊቶች መነሻነት ሲዳማ ቡና የመጀመሪያው ሰለባ ሆኖ ተመልክተናል።

ሲዳማ ቡና በፋሲል ከነማ 4-0 በተረታበት ጨዋታ በተፈጠሩ ሁነት መነሻነት በተላለፈበት ቅጣት መካከል በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከመከላከያ ጋር ከሜዳው ውጪ ባደረገው ጨዋታ ያለ ደጋፊዎቹ ጨዋታ እንዲያደርግ ተገዷል። ይህንን ተከትሎ የቡድኑ ደጋፊዎች ከስታዲየሙ ቅጥር ግቢ ውጪ በዛፍ ላይ ተንጠልጥለው ጨዋታውን ለመታደም ሲሞክሩ ታይተዋል።

በቀጣይም ከወላይታ ድቻ እና ባህርዳር ከተማ ጋር በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች እንዲሁ ያለደጋፊዎቹ አጀብ ይጫወታል። መሰል ሁነቶች ቡድኖች ላይ በፋይናንስ ረገድ ከሚፈጥሩት ጫና ባለፈ ቡድኑ ከደጋፊዎቹ ሊያገኘው የሚችለውን ተጠቃሚነት ሊያሳጣ እንደመቻሉ ደጋፊዎች ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ድጋፋቸውን ሆነ ተቃውሟቸውን መግለፅ ይኖርባቸዋል።

👉 ቅሬታ የበረከትበት የሊጉ ዳኝነት

ውሳኔ የሚለው እሳቤ በራሱ ህጎችን መነሻ ቢያደርግም ግላዊ ዕይታዎች የተካለበት እንደመሆኑ በተወሰነ መልኩ አከራካሪ ነገሮች እንደሚኖሩት ይገመታል። ከግላዊ ዕይታዎች ባለፈ ግን ውሳኔዎቹን ትክክለኝነት ለመመዘን ከስሜት ወጥቶ ሁነታውን ከህግም ሆነ ከሌሎች መመዘኛዎች አንፃር በትኩረት ማጤንን ይጠይቃል።

በሀገራችን ያለው የእግርኳስ ዳኝነት ሁኔታ ግን በተለይ ውድድሩ የቴሌቪዥን ስርጭት ማግኘቱን ተከትሎ አጋጣሚዎችን በምልሰት ከተለያዩ የዕይታ አቅጣጫዎች መመልከት መቻላችን በተወሰነ መልኩ አደባባይ ላይ እንዲሰጡ አደረገ እንጂ ይህ ሂደት በቀደሙት ጊዜያትም የነበረ ምናልባትም ወደ ፊትም ሊኖር የሚችል የጨዋታው አካል ነው።

የእግርኳስ ዳኝነት ከስህተቶች የፀዳ ማድረግ ባይቻልም በመጠኑም ቢሆን ለመቀነስ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ሆነ ሌሎች አማራጮች ተግባራዊ እየተደረጉ ቢገኝም አሁንም ቢሆን ግን በዳኝነት ውሳኔዎች ላይ እዚህም እዚያም ቅሬታዎች መቅረባቸው አልቀረም። በእኛ ሀገር ደግሞ በተወሰነ መልኩ በዳኞች መካከል ያለውን ተግባቦት ለማሳደግ የሚረዳ መሳሪያ አገልግሎት ላይ እየዋለ ይገኛል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን አሁን ድረስ በሊጉ እያጫወቱ የሚገኙ አንዳንድ ዳኞች ላይ መሰረታዊ የዳኝነት ስህተቶች አሁንም እየተመለከትን እንገኛለን። በተለይም የጨዋታ ህግጋትን በአግባቡ ተረድቶ ተግባራዊ ከማድረግ እና ለእንቅስቃሴዎች ቀረብ ብሎ ውሳኔዎችን ከመስጠት አንፃር ጥያቄ የሚያስነሱ ውሳኔዎች መታየታቸውን ቀጥለዋል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከድሬዳዋ ከተማ ያገናኘው እና በሆሳዕናዎች 3-2 አሸናፊነት የተጠናቀቀው አልቢትር ዓለማየሁ ለገሰ የተመራው ጨዋታ ብዙ አነጋጋሪ ጉዳዮች ያስመለከተን የሳምንቱ ጨዋታ ነበር። ሦስት ፍፁም ቅጣት ምቶችን ያስመለከተን ጨዋታው በተለይ ሁለቱ ፍፁም ቅጣት የተሰጡበት መንገድ በጣም አወዛጋቢ ሂደቶች ነበሯቸው።

የመጀመሪያ አነጋጋሪ ውሳኔ የነበረው ፍሬዘር ካሳ አብዱለጢፍ መሀመድ ላይ የሰራው ጥፋት ከሳጥን ውጪ በነበረበት ሁኔታ አልቢትሩ በሳጥን ውስጥ ነው በማለት ለድሬዳዋ ከተማ የሰጡት እና አብዱረህማን ሙባረክ ወደ ግብነት የቀየረው የፍፁም ቅጣት ምት አጋጣሚ ነው።

በደቂቃዎች ልዩነት ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን ላይ በድሬዳዋው በአብዱለጢፍ መሀመድ ጥፋት ተሰርቶበታል በማለት ለሀዲያ ሆሳዕና የፍፁም ቅጣት ምት ቢሰጡም አምበሉ ሄኖክ አርፌጮ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በተመሳሳይ በሁለተኛው አጋማሽ የኤሊያስ አታሮ በረጅም ወደ ድሬዳዋ ሳጥን የላከውን ኳስ የቡድን አጋሩ ባዬ ገዛኸኝ ለመጠቀም ጥረት ባደረገበት ወቅት አውዱ ናፊዩ ጥፋት ሰርቶበታል በሚል በጨዋታው ሦስተኛ የፍፁም ቅጣት የሰጡበት ሂደት ብዙ ያነጋገረ ነበር።

አርቢቴር ቢኒያም ወርቅአገኘሁ በመሩት ባህርዳር ከተማ እና ፋሲል ከነማ ያገናኘው የ8ኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታ በ69ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ቢጫ ካርዱን የተመለከተው በረከት ደስታ በ89ኛው ደቂቃ ደግሞ ሣላአምላክ ተገኘ የሰራበትን ጥፋት ተከትሎ በተፈጠረ ጉሽሚያ ወቅት የዕለቱ ዳኛ ሁለተኛ ቢጫ ካርድ ሲሰጡት ቢታይም በአካላዊ እንቅስቃሴያቸው እንጂ በመዝገባቸው ላይ ባለማስፈራቸው ተጫዋቹ ከሜዳ ሳይወጣ ጨዋታውን እንዲያጠናቅቅ መደረጉ በጨዋታ ሳምንቱ ከተመለከትናቸው አነጋጋሪ የዳኝነት ውሳኔዎች ተጠቃሹ ነበር።

👉 ማራኪው የመከላከያ መለያ

የገበያ አድማሱን እያሰፋ የሚገኘው ሀገር በቀሉ ጎፈሬ የስፖርት ትጥቆች አቅራቢ ድርጅት ከቀናት በፊት ደግሞ ከአንጋፋው የመከላከያ ስፖርት ክለብ ጋር ለዋናው የእግርኳስ ቡድን የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል።

ታድያ ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ለነበራቸው የሊግ ጨዋታ ይደርሳል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የክለቡ አዲሱ መለያ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት ላይ ውሏል።

የንድፍ መነሻውን የቀደሙትን የመከላከያ መለያዎችን ያደረገው አዲሱ ጎፈሬ ያመረተው የመከላከያ መለያ ደረቱ ላይ በቀደመው መለያ ላይ በአግደመት አረንጓዴ እና ቀይ ቀለሞችን በሚያካፍለው ቦታ ላይ መጠነኛ ቢጫ መስመር የታከለበት አዲሱ መለያ ለዓይን በጣሙን የሚማርክ እንዲሆን አድርጎታል።

ይህ አዲሱ የመከላከያ መለያ በሊጉ በዘንድሮ የውድድር ዘመን ከተመለከትናቸው መለያዎች በተመልካቹ ዘንድ የተወደደ እንደሆነ በማህበራዊ ሚድያዎቻችን በምናጋራቸው መረጃዎች ላይ የሚሰጡ አስተያየቶች ጠቋሚ ናቸው።