አዲስ አበባ ከተማ በግብ ዘቡ እየተመራ የነገውን ጨዋታ ሊያደርግ?

በነገው ዕለት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር የሚጫወተው አዲስ አበባ ከተማ ዋና እና ምክትል አሠልጣኞቹን እንዲሁም የቴክኒክ ዳይሬክተሩን በነገው ጨዋታ እንደማያገኝ ታውቋል።

አዲሱ የሊጉ ክለብ አዲስ አበባ ከተማ ነገ 12 ሰዓት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር የዘጠነኛ ሳምንት መርሐ-ግብሩን የሚያከናውን ይሆናል። ከሁለተኛ ሳምንት ጀምሮ ቡድኑን በዋና አሠልጣኝነት ሲመሩ የነበሩት አሠልጣኝ ደምሰው ፍቃዱም ነገ ቡድናቸውን እየመሩ ጨዋታውን ይቀርባሉ ተብሎ ቢጠበቅም ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ መሠረት አሠልጣኙ በነገው ጨዋታ ሀላፊነታቸውን በሜዳ ተገኝተው እንደማይወጡ አውቀናል።

ዋና አሠልጣኙ ቡድናቸውን የማይመሩበት ምክንያት ደግሞ ዛሬ በደረሰው የኮቪድ-19 ውጤት መሠረት እንደሆነ አውቀናል። ከዋና አሠልጣኙ በተጨማሪ ደግሞ የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ የሆኑት አሠልጣኝ መሠረት ወ/ማርያምም በተመሳሳይ ምክንያት አይኖሩም። ምናልባት የቡድኑ አዲሱ ቴክኒክ ዳይሬክተር ፍሰሐ አገኘሁ በቦታው ሊሰየሙ ይችላሉ ብለን ጠይቀንም እሳቸውም በተመሳሳይ የኮቪድ-19 ውጤት እንደማይገኙ አውቀናል።

ይህንን ተከትሎ አዲስ ነገር እስካልተፈጠረ ድረስ የቡድኑ ግብ ጠባቂ የሆነው ዳንኤል ተሾመ በነገው ዕለት የተጫዋችነት እና የአሠልጣኝነትም ጥምር የሥራ ሀላፊነት ይዞ እንደሚገባ ሰምተናል።

በጉዳዩ ዙርያ ያሉ አዳዲስ ነገሮች ካሉ ይዘን የምንቀርብ ይሆናል።