ቅድመ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ መከላከያ

ሊጉ ለእረፍት ከመቋረጡ በፊት በሀዋሳ ከተማ የሚደረገው የዘጠነኛ ሳምንት የመክፈቻ መርሐ-ግብርን እንደሚከተለው ቃኝተነዋል።

በአሁኑ ሰዓት የሊጉ መሪ የሆነው ፋሲል ከነማ ሊጉ ለሳምንታት ከመቋረጡ በፊት ዳግም ሦስት ነጥብ አግኝቶ መሪነቱን ለማስጠበቅ ጠንካራ ብቃቱን ነገ ያሳያል ተብሎ ይጠበቃል።

በሦስተኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ጅማ አባጅፋርን ካሸነፈ በኋላ ለተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች አዎንታዊ ውጤት ማስመዝገብ ከብዶት የነበረው ፋሲል አሁን ወደ ጠንካራ አቋሙ የመጣ ይመስላል። ምንም እንኳን ባለፉት ሁለት ጨዋታዎችም ሁለት ነጥቦችን ቢጥልም በእቅስቃሴ ደረጃ ለውጤት ረሀብተኛውን ፋሲል ተመልክተናል። በተለይ ደግሞ በሲዳማው ጨዋታ ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ ያሳዩት እንቅስቃሴ ትልቅ ዋጋ ከፍሏቸዋል። በባህር ዳሩም ጨዋታ ሦስት ነጥብ አያግኙ እንጂ በኳስ ቁጥጥር እና የተጋጣሚን የግብ ክልል በመጎብኘቱ ረገድ ብልጫ ነበራቸው። ነገም ይህ ብልጫ እንደሚኖር ሲጠበቅ በማጥቃቱ ረገድ ግን ከመቼውም የተሻለ ብርታት የሚጠበቅባቸው ይመስላል። ምክንያቱም የሚገጥሙት ጠጣር የኋላ መስመር ያለው መከላከያን በመሆኑ።

በጥሩ ወቅታዊ ብቃቱ ላይ የሚገኘው በረከት ደስታ ነገም ለመከላከያ ተከላካዮች የራስ ምታት እንደሚሆን ሲታሰብ ግዙፉ አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢም ከመስመር የሚሻገሩለትን ኳሶች ለመጠቀም የሚያደርገው ጥረት ይጠበቃል። ይህ ከወገብ በላይ ያለ እንቅስቃሴ ደግ ቢሆንም ግን በአንዳንድ የጨዋታ ሂደቶች የሚያደርጓቸው ከማጥቃት ወደ መከላከል የሚደረጉ ሽግግሮች አደጋ አምጪ ናቸው። በተወሰነ መልኩ ይህ ክፍተት በባህር ዳሩ ጨዋታ ታይቶ ባይቀጡበትም ግን መከላከያ ካለው ፈጣን የማጥቃት የሽግግር አጨዋወት አንፃር ዳግም እንዳይቸገሩ ያሰጋል።

ዐፄዎቹ በነገው ጨዋታ ሁለት ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን የማያገኙ ይሆናል። አንደኛው ሲዳማ ቡናን ሲረቱ በጉዳት በ67ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የወጣው እና በባህር ዳሩም ጨዋታ ያልነበረው አስቻለው ታመነ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ዘለግ ላሉ ቀናት ጉዳት አጋጥሞት በባህር ዳሩ ጨዋታ በ63ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ገብቶ የነበረው ሱራፌል ዳኛቸው ነው።

ዘንድሮ ሊጉን የተቀላቀለው መከላከያ በሁለት ተከታታይ ድሎች ዓመቱን ቢጀምርም ከዛ በኋላ እያሳየ ካለው ወጥ ያልሆነ ብቃቱ ለማገገም እና ከአምስተኛ ሳምንት በኋላ አግኝቶት የማያውቀውን ሦስት ነጥን አግኝቶ ደረጃውን ለማሻሻል ነገ ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርግ እሙን ነው።

በሁለት የአራት ተጫዋቾች አጥር (Double block of four) የሚጫወቱት መከላከያዎች በቡድናዊ መዋቅር ግባቸውን የማያስደፍሩበት መንገድ በስምንቱ የጨዋታ ሳምንታት የታየ የጎላ አዎንታዊ ጎናቸው ነው። እንደ ተጋጣሚያቸው ፋሲል ከነማ ሁሉም በሊጉ በርካታ ጨዋታዎችን (5) ግብ ሳያስተናግዱ የወጡበት ሚስጢር ይህ ለመከላከል ቅድሚያ ተሰጥቶ ግብ ባለማስተናገድ የአጨዋወት ስልት ተቃኝቶ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው። ነገም በተመሳሳይ ኳሱን ለፋሲሎች በመተው ከኳስ ጀርባ በመሆን ዘለግ ያለውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እንደሚያሳልፉ እና የጨዋታ መነሻ ሀሳባቸው ግብ አለማስተናገድ ብሎ እንደሚጀምር ይታሰባል። ይህ መነሻ ሀሳብ ቢሆንም ግን ፈጣን የሽግግር አጨዋወት ደግሞ በተቃራኒው የፍፁም ቅጣት ምት እንዲገኙ የሚያስችላቸው ስልትም ሊሆን ይችላል።

ፈጣን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ከመከተላቸው በተጨማሪ ደግሞ ተሻጋሪ እና ረጃጅም ኳሶችም በመከላከያ በኩል የሚዘወተር ግብ የማግኛ መንገድ እንደሚሆን ይታሰባል። ከዚህ ውጪ ደግሞ በሜዳ ላይ ብዙ ነገሮችን ሲያደርግ እና ከምንም ቡድኑ የግብ ዕድሎችን እንዲያገኝ የሚጥረው ቢኒያም በላይ ነገም በጦሩ በኩል ትኩረት የሚስብ ውጤት ቀያሪ ተጫዋች እንደሚሆን ይታመናል። በተለይም ተጫዋቹ በመስመሮች መሐከል እና ከተከላካዮች ጀርባ እየተገኘ የሚፈጥራቸው አጋጣሚዎች ለፋሲሎች ከባድ ይሆናል። መከላከያ እንደ ስሙ መከላከሉ ጠጣር ቢሆንም ግን ከላይ እንደጠቀስነው ፈጣን፣ ቦታ ተለዋዋጭ እና በቁጥር በዝተው የመጨረሻው የማጥቂያ ሲሶ ላይ የሚገኙትን የፋሲል ተጫዋቾች ሊቆጣጠር ያሰበበት መንገድ ከመቼውም በላይ የጠበቀ መሆን የግድ ይለዋል።

በሊጉ ደረጃ ሰንጠረዥ አስረኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው መከላከያ የመስመር ተከላካዩ ዳዊት ማሞ ከቅጣት ቢመለስለት የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ቦታ እንዳላቸው የሚታሰበው ኦኩቱ ኢማኑኤል፣ ሰመረ ሀፍታይ፣ ገናናው ረጋሳ እና አዲሱ አቱላ ግን አሁንም ከያለባቸው ጉዳት ስላላገገሙ በነገው ጨዋታ አያገኛቸውም።

ዘጠኝ ሰዓት ሲል የሚጀምረውን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በመሐል አልቢትርነት የምትመራው ይሆናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ፋሲል ከነማ እና መከላካያ በአጠቃላይ 7 ጊዜ ተገናኝተዋል። ፋሲል ሦስት በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መከላከያ ሁለቱን አሸንፎ በቀሪዎቹ ሁለቱ አቻ ተለያይተዋል። ዐፄዎቹ 12፣ ጦረኞቹ 6 ጎሎች አስቆጥረዋል።

– በ2011 አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ በነበረው የመጨረሻ ግንኙነታቸው ፋሲል 4-0 አሸንፎ ነበር።

ግምታዊ አሠላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-1-4-1)

ሚኬል ሳማኬ

ዓለምብርሃን ይግዛው – ያሬድ ባየህ – ከድር ኩሊባሊ – አምሳሉ ጥላሁን

ይሁን እንዳሻው

ሽመክት ጉግሳ – በዛብህ መለዮ – ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ – በረከት ደስታ

ኦኪኪ አፎላቢ

መከላከያ (4-2-3-1)

ክሌመንት ቦዬ

ቢኒያም ላንቃሞ – ኢብራሂም ሁሴን – አሌክስ ተሰማ – ዳዊት ማሞ

ኢማኑኤል ላርዬ – ደሳለኝ ደባሽ

ብሩክ ሰሙ – ቢኒያም በላይ – ግሩም ሀጎስ

አቤል ነጋሽ