ቅድመ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ አዲስ አበባ ከተማ

የዘጠነኛውን ሳምንት ሁለተኛ መርሐ ግብር በተከታዩ መልክ ቃኝተነዋል።

የነገ ምሽቱ ጨዋታ ተጋጣሚዎች ሰሞንኛ ውጤት በፈለጉት መንገድ የሄደ አልነበረም። የጅማው ጨዋታ ድንቅ ብቃት እና ውጤት ትዝታ ብቻ የተረፋቸው ድሬዳዋዎች ከዚያ በሁዋላ በአራት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ አሳክተው ወደ ሰንጠረዡ ግርጌ አካባቢ ተንሸራተዋል። የነገው ጨዋታ ውጤት ካልሰመረላቸውም በወራጅ ቀጠና ውስጥ ሆነው ሀዋሳን ለመልቀቅ ይገደዳሉ። ከተጋጣሚው በሦስት ነጥብ ከፍ ብሎ በሰንጠረዡ ወገብ አካባቢ የሚገኘው አዲስ አበባም በተመሳሳይ ከላይ ወደ ታች መገፋት የግድ ሆኖበታል። በእርግጥ ከተጋጣሚው በተለየ ሁኔታ በመጨረሻ አራት ጨዋታዎቹ አምስት ነጥቦችን ይሰብስብ እንጂ ዳግም ደረጃውን ከፍ አድርጎ ከጫና ለመራቅ የ9ኛ ሳምንት ውጤቱን ማሳመር ይኖርበታል።

በሊጉ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን የማግኘት ግብ ይዘው ከሚንቀሳቀሱ ቡድኖች መካከል የሚመደበው ድሬዳዋ በዚህ መንገድ ጨዋታን ተቆጣጥሮ በቂ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ ረገድ ብዙ እንደሚቀረው ያለፉት ጨዋታዎች አሳይተውናል። የኳስ ፍሰቱ መቋጫ የሆኑት ሁለቱ መስመሮች ከተጋጣሚ ሳጥን ዙሪያ ወደ ውስጥ ለመግባት ዋና ምርጫዎቹ መሆናቸውም ለተጋጣሚዎች ተገማች እያደረገው ያለ ይመስላል። ይህ ችግር በቀኝ በኩል የጋዲሳ መብራቴ መመለስ ተስፋ ይሁነው እንጂ ወደ ፊት ሲሄድ በኮሪደሩ ጉልበት የሚሆነው እንየው ካሳሁንን ከማጣቱ ጋር ተዳምሮ ግራውን የሚዘውረው አብዱለጢፍ መሀመድን በነገው ጨዋታ ዋናው የድሬ የማጥቃት ሂደቶች መቋጫ ሊያደርገው ይችላል። አሁንም ሁነኛ ሰው ያገኘ የማይመስለው የቡድኑ የአስር ቁጥር ሚና በአግባቡ ካልተሸፈነም ተጨማሪ ቀዳዶችን ለማግኘት እንዳይቸገር ያሰጋዋል።

በሌላ ጎኑ ስንመለከተው አዲስ አበባ ከተማ በሀዋሳው ጨዋታ ያሳየው የመከላከል ድክመት ድሬዳዋ ከተማ ከነማጥቃት ሂደት ችግሩ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁመናል። በጀመሩበት የመከላከል ትኩረት የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበረው ተጋጣሚያቸው ሀዋሳን ከግብ ክልላቸው በማራቁ እየተዳከሙ የመጡት አዲስ አበባዎች ግብ ሲያስተናግዱ አራቱ የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎቻቸው መሀል ላይ በጠበበ አቋቃም ላይ ተገኝተው ታይተዋል። መሰል ቅፅበቶች ለድሬዎች ተገማች ቢሆንም በንፅፅር ጠንካራ ለሆነው የኮሪደር ጥቃት ሊያጋልጣቸው ይችላል።

ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የአዲስ አበባዎች ቀጥተኛ ኳሶች ለድሬዳዋ ፈተና የሚሆኑበት ዕድል ሊፈጠር ይችላል። ኳስ መስርቶ ከሜዳው ሲወጣ የተከላካይ መስመሩን ወደ መሀል የሚያስጠጋው ድሬዳዋ በተንጠልጣይ ኳሶች በቀላሉ እንደሚጠቃ የሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ በጉልህ አሳይቷል። ለመሰል ሁነቶች የተመቸው ሪችሞንድ ኦዶንጎን የያዘው የመዲናዋ ክለብም የማጥቃት ሽግግሩን በሚያሳልጡት የመስመር አጥቂዎቹ ታግዞ ግብ አፋፍ የመድረስ አቅሙ እንዳለው የቅርብ ጨዋታዎቹ ያሳያሉ።

ሌላው ትኩረት የሚስበው እና የቅርብ ጨዋታዎች መልካቸው ሆኖ የሚታየው ነጥብ የቆሙ ኳሶች አጠቃቀም ነው። በመጨረሻው ጨዋታ ከቆመ ኳስ መነሻ ግብ ያስተናገደው ድሬዳዋ በሌሎች አጋጣሚዎችም በአግባቡ ተጫዋቾችን በበቂ ሁኔታ ሳይሸፍን ሲቀር ተስተውሏል። የነገ ተጋጣሚው አዲስ አበባም ተደጋጋሚ የቆሙ ኳስ ዕድሎችን ቢፈጥርም እንደብዛታቸው ውጤታማ ሲሆን አልታየም። ሁለቱም ላይ ይህ ድክመት ይታይ እንጂ ነገ በዚህ ረገድ ተሻሽሎ የሚመጣ ቡድን በጨዋታው ለሚያስመዘግበው ውጤት መነሻ ሊሆነው እንደሚችል ግን መናገር ይቻላል።

ለድሬዳዋ ከተማ መልካሙ ዜና የጋዲሳ መብራቴ ለጨዋታው ዝግጁ መሆን ነው። በሌላ በኩል ዳንኤል ኃይሉ አሁንም ከቡድኑ ጋር የሌለ ሲሆን ያሲን ጀማል ፣ ዳንኤል ደምሴ እና እንየው ካሳሁንም በጉዳት ምክንያት ጨዋታው ያልፋቸዋል። በአዲስ አበባ በኩል ትልቁ ዜና የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱን በኮቪድ ምክንያት በነገው ጨዋታ የማንመለከታቸው መሆኑ ነው። በዚህም ምክንያት ጉዳት ላይ ከሚገኙት ሮቤል ግርማ ፣ ፋይሰል ሙዘሚል ፣ ነብዩ ዱላ እና ቴዎድሮስ ሀሞ በተጨማሪ ቡድኑን በአሰልጣኝነት እንደሚመራ የሚጠበቀው ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመም በአሰላለፉ ውስጥ አያካተትም።

ፌደራል ዳኛ ዮናስ ማርቆስ ይህንን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመሩታል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በ2009 ሁለት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን አንዱን ድሬዳዋ ከተማ 1-0 አሸንፎ ሌላኛውን አንድ አቻ ተለያይተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ፍሬው ጌታሁን

ዐወት ገብረሚካኤል – መሳይ ጳውሎስ – አውዱ ናፊዩ – ሄኖክ ኢሳይያስ

ብሩክ ቃልቦሬ – መጣባቸው ሙሉ

ጋዲስ መብራቴ – አቤል ከበደ – አብዱለጢፍ መሀመድ

ማማዱ ሲዲቤ

አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)

ዋኬኔ አዱኛ

አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ልመንህ ታደሰ – ዘሪሁን አንሼቦ – ያሬድ ሀሰን

ኤልያስ አህመድ – ቻርለስ ሪባኑ – ሙሉቀን አዲሱ

እንዳለ ከበደ – ሪችሞንድ አዶንጎ – ፍፁም ጥላሁን