ከፍተኛ ሊግ | የ14ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 14ኛ ሳምንት ዛሬ በሦስቱ አስተናጋጅ ከተሞች በተደረጉ ዘጠኝ ጨዋታዎች ተፈፅሟል።

የ04:00 ጨዋታዎች

ወሎ ኮምቦልቻ ከ ዱራሜ ከተማ – ምድብ \’ሀ\’

ረፋድ በጀመረው የመጀመርያ ጨዋታ ወሎ ኮምቦልቻ ከዱራሜ ከተማ አገናኝቶ ወሎ ኮምቦልቻዎች ከመመራት ተነስተው አሸንፈው ወጥተዋል። የጨዋታውን እንቅስቃሴ ተቆጣጥረው በተጋጣሚያቸው ጫና ያሳደሩት ዱራሜዎች በሁለት አጋጣሚዎች ከሳጥን ውጪ የመቱትን ኳስ የግቡ አግዳሚ የመለሰባቸው የሚያስቆጭ ነበር። ወሎ ኮምቦልቻዎች በተወሰደባቸው ብልጫን ለመቆጣጠር ወደ ኋላ ተስበው መከላከልን በመምረጣቸው ወደ ፊት በመሄድ እምዛብ የጎል ዕድሎችን ሳይፈጥሩ ቀርተዋል።

\"\"

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሬ አንስቶ በሁለቱም በኩል በጨዋታው ነጥብ ይዞ ለመውጣት ብርቱ ፉክክር ሲያደርጉ በ61ኛው ደቂቃ የጨዋታው የመጀመርያ ጎል ተስተናግዷል። ጎሉንም ባልተጠበቀ መንገድ የዱራሜው አንበል ተስፋሁን ተሾመ ከመሐል ሜዳ በቀጥታ የመታው ኳስ ወደ ጎልነት ተቀይሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ብዙም ሳይቆዩ ምላሽ የሰጡት ወሎዎች ከቅጣት ምት ኳስ በ68ኛው ደቂቃ ካሳሁን ሰቦቃ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን አቻ አድርጓል። በዚህች ጎል የተነቃቁት ወሎ ኮምቦልቻዎች ከመሐል ሜዳ የተጣለለትን ከተከላካዮች አምልጦ የገባው ብርሀኑ አዳሙ በግብ ጠባቂው አናት ላይ አሳልፎ ቡድኑን መሪ ያደረገች ጎል በ81ኛው ደቂቃ አስቆጥሮ ጨዋታው 2-1 ተጠናቋል።

ንብ ከ ከምባታ ሺንሺቾ – ምድብ \’ለ\’

የሜዳ ለውጥ ተደርጎ በግብርና ኮሌጅ ሜዳ 4 ሰዓት ሲል ንብ እና ከምባታ ሺንሺቾን ያደረጉት ጨዋታ የምድቡ ቀዳሚ ጨዋታ ነበር። ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ህይወቱ ላለፈው የእንጅባራ ተጫዋች ተስፋፂሆን ፋንቱ ንቦች የ23 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍን ካደረጉ በኋላ ነበር ጨዋታው መጀመር የቻለው። በተሻለ ንቃት ጨዋታውን የጀመሩት እና በመስመር በኩል በተለይ ታምራት ስላስ በተሰለፈበት የቀኝ የሜዳው ክፍል ረጅሙን ደቂቃ ሲጫወቱ የተስተዋሉት ንቦች 19ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አግኝተዋል። ከተጠቀሰው ቦታ ታምራት ስላስ ወደ ሳጥን ውስጥ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ያሻገረውን አምበሉ ንስሀ ታፈሰ ግብ አድርጎታል። ሺንሺቾዎች መሀል ሜዳ ላይ ብቻ ረጅሙን ደቂቃ ያሳለፉ ስለነበር በቀላሉ ወደ ተጋጣሚ ሦስተኛ የሜዳ ክፍል መግባት ተስኗቸው አጋማሹ ተገባዷል።

\"\"

ጨዋታውን ወደ ራሳቸው በማድረግ ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸውን ዕድል ለመፍጠር በመታተር ይጫወቱ የነበሩት ከምባታ ሺንሺቾዎች አሁንም ግልፅ አጋጣሚዎችን በመፍጠሩ የሚታይባቸው ውስንነት በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ጫናዎች እንዲበረታባቸው ሆኗል። በዚህም ንብ ተጨማሪ ግብን ለማከል ከርቀት እንዲሁም በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን ደርሰው የግብ መጠናቸውን የሚያሰፉ አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም ጨዋታው በ1-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ባቱ ላይ በምድብ \’ሐ\’ በተደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ኦሜድላ እና ደሴ ከተማ ተገናኝተዋል። በጨዋታው ደሴ ከተማ አላዛር ተስፋዬ በራሱ ላይ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ ቢሆንም 31ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን መንገሻ ኦሜድላን አቻ አድርጓል። ጨዋታው ከዕረፍት መልስ ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በ1-1 ውጤት ተጠናቋል።

የ08:00 ጨዋታዎች

ሰበታ ከተማ ከ ወልዲያ – ምድብ \’ሀ\’

ከሰዓት ስምንት ሰዓት የቀጠለው የሰበታ ከተማ እና የወልድያ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ተመጣጣኝ ፉክክር ያስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጎል በማስቆጠር ቀዳሜ የሆኑት ወልዲያዎች ነበሩ። በ7ኛው ደቂቃ ከወልዲያ የሜዳ ከፍል በረጅሙ የተላከውን ኳስ ጌታሁን ዳዲ ለግብ ጠባቂው በግንባር በመግጨት ለማቀበል አስቦ የመታው ኳስ በራሱ ላይ ሊቆጠር ችሏል።

\"\"

ፈጥኖ ጎል ቢቆጠርም በቀሩት ደቂቃዎች ተጨማሪ ጎል ሳንመለከት ቆይተን ከዕረፍት መልስ እንደጀመረ ሰበታ ከተማዎች የአቻነት ጎል አግኝተዋል። ጎሉንም በ47ኛው ደቂቃ የወልዲያ ተከላካዮች ከግብ ክልላቸው ማራቅ ባለመቻላቸው የተደረበውን ኳስ ምትኩ ጌታቸው በጥሩ አጨራረስ ወደ ጎልነት ቀይሮታል። ቀሪው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እምብዛብ የጎል ሙከራ ባያስመለክተንም በመጨረሻው ደቂቃ ሰበታዎች አሸናፊ የሚሆኑበትን የጎል ዕድል በምትኩ አማካኝነት ቢፈጥሩም የግቡ አግዳሚ የመለሰባቸው አጋጣሚ የሚያስቆጭ ሆኖ ጨዋታው በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ነቀምት ከተማ ከ ይርጋጨፌ ቡና – ምድብ \’ለ\’

በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ለውጥ ያስከትል የነበረው የነቀምት ከተማ እና ይርጋጨፌ ቡና ጨዋታ ጥሩ ፉክክርን አስመልክቶን ይርጋጨፌ ቡናን አሸናፊ አድርጎ ተጠናቋል። 8 ሰዓት ሲል ጅምሩን ባደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ነቀምት ከተማዎች ረጃጅም ኳስን መሠረት ባደረገ እንቅስቃሴ ከመስመር በሚሻገሩ እና በግንባር ተገጭተው በሚቆጠሩ ኳሶች ግቧችን ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም በመልሶ ማጥቃት ፋታ የለሽ የጨዋታ መንገድን ይከተሉ የነበሩት ይርጋጨፌዎች ተሳክቶላቸው 54ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ የሜዳው ክፍል ከተገኘ የቅጣት ምት ተሻምቶ ስዩም ደስታ በግንባር ገጭቶ ከመረብ በማገናኘት ይርጋጨፌን መሪ አድርጓል።

\"\"

ከዕረፍት ጨዋታው ተመልሶ በስዩም ደስታ ላይ ባነጣጠረ የሽግግር አጨዋወትን በመከተል ሌላ ግብን ለማግኘት ይርጋጨፌዎች ያሳዩ የነበረው ትጋት ከተጋጣሚያቸው የተሻለ ሆኖ ታይቷል። በዚህም 70ኛው ደቂቃ ላይ ተካልኝ መስፍን በጥሩ አጨራረስ ሁለተኛ ጎል አክሎ የቡድኑን የግብ መጠን ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል። የተጫዋች ለውጥን ካደረጉ በኋላ በይበልጥ ወደ ጨዋታ ቅኝት የተመለሱት እና ጫናን ወደ መገባደጃው ሲፈጥሩ የታዩት ነቀምቶች በተለይ ደግሞ ቴዎድሮስ መንገሻን ለውጠው ካስገቡ በኋላ በድግግሞሽ ወደ ይርጋጨፌ ቡና የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ ይደርሱ ነበር። በዚህም 78ኛው ደቂቃ የቀድሞው ክለቡን በቅርቡ የተቀላቀለው ገዛኸኝ ባልጉዳ ከሽንፈት ያልታደጋቸውን ብቸኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በይርጋጨፌ ቡና 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ቡድኑም በድሉ ደረጃውን በማሻሻል ወደ መሪዎቹ ተርታ አስጠግቷል።

በምድብ \’ሐ\’ የተደረገው የቡራዩ ከተማ እና ኮልፌ ክ/ከ ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል።

የ10:00 ጨዋታዎች

ጅማ አባ ቡና ከ ባቱ ከተማ – ምድብ \’ሀ\’

በቀዳሚው ምድብ የአስራ አራተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ የነበረው ጅማ አባ ቡና እና የባቱ ከተማ አገናኝቶ ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ ጉሽሚያ የበዛበት ጨዋታ አስመልክቶን ያለ ጎል ተጠናቋል።

\"\"

አምቦ ከተማ ከ ቦዲቲ ከተማ – ምድብ \’ለ\’

የሳምንቱ የምድቡ የማሳረጊያ ጨዋታ በአምቦ ከተማ እና ቦዲቲ ከተማ መካከል ተካሂዷል። ተመጣጣኝ ፉክክርን ባስተዋልንብት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 17ኛው ደቂቃ ላይ አምቦ ከተማዎች ከቅጣት ምት መነሻዋን ካደረገች ኳስ በለማ ኃይሌ የግንባር ኳስ መሪ ሆነዋል። ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ በይበልጥ ቶሎ ቶሎ ተሻጋሪ ኳስን በመጠቀም ወደ አቻነት ለመምጣት ለአምቦ ተከላካዮች ራስ ምታት ሲሆኑ የተመለከትናቸው ቦዲቲ ከተማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ የጭማሪ ደቂቃ ላይ በጥሩ የጨዋታ ፍሰት በጌታሁን ሽርኮ ጎል አቻ ሆነዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ በተጋጣሚያቸው ላይ ልዩነት በመፍጠር ለመጫወት ሲጥሩ የታዩት ቦዲቲ ከተማዎች 65ኛው ደቂቃ ላይ በአጥቂው ቢኒያም ታከለ ጎል ሁለተኛ ጎል አክለው ከመመራት ተነስተው 2-1 በማሸነፍ ወሳኝ ድልን አሳክተዋል።

\"\"

የምድብ\’ሐ\’ የ14ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በጅማ አባ ጅፋር  እና ሶዶ ከተማ መካከል ተከናውኗል። አምስተኛው ደቂቃ ላይ አሸናፊ ሽብሩ ለሶዶ ያስቆጠረው የፍፁም ቅጣት ምት ጎልም ሁለቱን ቡድኖች የለየ ብቸኛ ግብ ሆኗል።