ልዩ ዘገባ ከሞሮኮ | ዋልያዎቹ ምሽት ላይ ልምምድ ይሰራሉ

ከነገ በስትያ ከጊኒ ጋር ጨዋታ ያለባቸው ዋልያዎቹ በኦማን የሚጫወተውን አጥቂ በመያዝ በተሟላ ሁኔታ ዛሬ ወደ ልምምድ ይመለሳሉ።

በ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ከጊኒ፣ ግብፅ እና ማላዊ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድብ ወሳኝ 3ኛ እና 4ኛ ጨዋታዎቹን በገለልተኛ ሜዳ ለመከወን ትናንት አመሻሽ ሞሮኮ ገብቷል።

\"\"

ትናንት ባቀረብነው ዘገባ ቡድኑ በበረራ መስተጓጎሎች ቀድሞ በታቀደው መሰረት ሞሮኮ መግባት ያልቻለ መሆኑን አስነብበን የነበረ ሲሆን ሞሮኮ መሐመድ 5ኛ ዐየር ማረፊያ ከደረሰ በኋላም ለሦስት ሰዓታት ገደማ በቪዛ ፕሮሰስ ጉዳይ በስፍራው ለመቆየት ተገዷል። በመቀጠልም ቡድኑ ወደተዘጋጀለት ኤዶ አንፋ ሆቴል አምርቷል።

የቡድኑ አባላት ሆቴል ከደረሱ በኋላ የእራት መዐድ የተቃመሱ ሲሆን የበረራ እና የቪዛ ችግር ከማጋጠሙ በፊት ምሽት ላይ ልምምድ ይሰራሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም በተጠቀሱት ምክንያቶች መዳከሞች ስለተከሰቱ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ለተጫዋቾቻቸው እረፍት ሰጥተዋል።

\"\"

ዛሬ ረፋድ ላይ የቡድኑ አባላት 2:30 (በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር 5:30) ቁርስ የተመገቡ ሲሆን ምሽት ላይ ወደ መደበኛ ልምምድ እንደሚመለሱ ታውቋል። በዚህም በራጃ የመለማመጃ ሜዳ ቡድኑ ከእሁዱ የሩዋንዳ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ በኋላ የመጀመሪያ የመስክ ላይ ልምምድ የሚያደርግ ይሆናል።

ለጊኒው ጨዋታ ከተጠሩ ተጫዋቾች መካከል በኦማኑ አል-ሱዋይቅ ክለብ የሚጫወተው ዑመድ ኡክሪ ትናንት ምሽት ከኦማን በቀጥታ ሞሮኮ ገብቶ ስብስቡን ተቀላቅሏል። ተጫዋቹም በዛሬው ልምምድ ላይ ከአጋሮቹ ጋር የመጀመሪያ ልምምድ የሚሰራ ይሆናል።