​የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 1- 0 መከላከያ

የ9ኛ ሳምንቱ ቀዳሚ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ ተጋጣሚ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ 

ስለጨዋታው

የበለጠ ተጠቅጥቀው ስለሚጫወቱ ዓለምብርሀን እና አምሳሉ እነሱን ለመበተን ተጠግተው እንዲጫወቱ ነበር ዕቅዳችን። በመጀመሪያው አጋማሽ በግራም በቀኝም ብዙ ሞክረናል። ያን ትርጉም አልባ ያደረገው አጨራረሳችን ደካማ በመሆኑ ነው።  የእነሱን ቀዳዳ ለማግኘት ተቸግረናል። የቆሞ ኳሶችን አግኝተናል ፤ እነሱን አልተጠቀምንም። እኛ በግብ ስንቀድም ነው እነሱ ለቀው ሊወጡ የሚችሉት ፤ የሆነውም ያ ነው። ከዛ በኋላ በርካታ አጋጣሚዎች አግኝተናል ፤ አልተጠቀምንም። ትልቁ ነገር ግን በዘጠኝ ጨዋታ በሀዋሳ ቆይታችን የአንደኝነት ክብራችንን አስጠብቀን መሄዳችን ነው።  በአጠቃላይ ግን በዘጠኝ ጨዋታ ያሳካነው ነጥብ 66℅ ነው። የሚመራ ቡድን ቢያንስ 80-90 መድረስ አለበት። ስለዚህ ብዙ መስራት አለብን። ለዚህ አንዱ የሜዳው ምቹ አለመሆንም ነው። በቀጣይ ግን በተመቻቹ ሜዳዎች ላይ የተሻለ ነገር እናደርጋለን ብዬ እገምታለሁ።

ስለቡድኑ የመስመር ጥቃት ምጣኔ

ዓለምብርሀን እየገባው ሲሄድ ከአምናው የተሻለ ይጠቅማል ብዬ አስባለሁ። አሁን ወደምንፈልገው ነገር እየተጠጋ ነው። ልምምድ እና ጨዋታ ላይ ይለያያል። ቦታው ሲገባው እና አጠቃቀሙን ሲያውቀው የተሻለ ይሆናል። አምሳሉ ልምድ ያለው ተጫዋች ነው እሱም ቢሆን የሚያሻሽላቸው ነገሮች እንዳሉ ሆነው ማለት ነው።

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ – መከላከያ
ስለወጣት ተጫዋቾች የዕለቱ አፈፃፀም

በእኔ ግምት የሥነልቦና ችግር አይቻለሁ ብዬ ነው የማምነው። በጨዋታ ደረጃ እነሱ ከሞከሩት እኛ የሞከርነው ይበልጣል። መሀል ሜዳ ላይ የተሻለ ኳስ ይዘዋል ፤ ያ ትርጉም የለውም። ወደ ጎል በመሄድ እና በመሞከር የተሻለ ነገር አድርገናል። የሥነ ልቦና ችግር ነው በወጣቶቹ ላይ ያየሁት።

ስለአጨራረስ ችግራቸው

እኛ የነገርናቸው በተቃራኒው ነበር። አንደኛ ከሆነ ቡድን ፣ አምስት ስድስት አፍሪካ ዋንጫ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ካሉበት ቡድን ፣ ያለፈው ዓመት ቻምፒዮን ከሆነ ቡድን ጋር ወጥታችሁ ራሳችሁን አሳዩ ነበር ያልናቸው። የሥነ ልቦና ችግር ነው ያየነው፤ ያ መሻሻል የሚችል ነው። ነገር ግን ከዕረፍት ከእነሱ በፊት ያገኘናቸው ሁለት አጋጣሚዎችን መጠቀም ብንችል የተሻለ ነገር ማድረግ እንችል ነበር። ሦስት ነጥብ ተወስዶብናል ፤ በጨዋታ ደረጃ ስመለከተው ግን የእኛ ወጣት የመሆናቸው ችግር ነው ብዬ ነው የማምነው።

ስለኦኩቱ ኢማኑኤል አለመኖር ተፅዕኖ

ኦኩቱ አንድ ጎል ነው ያገባው። በእኔ ግምት ተጫዋቾች እንዲህ ዓይነት ዕድል ሲያገኙ ደስተኛ መሆን ነው የነበረባቸው ፤ ራሳቸውን ለማሳየት። ዕድሉን አግኝተው ካልተጠቀሙበት ግን በሌላ ነው ማለት ነው። 

በቴክኒክ ቦታ ላይ ደስተኛ ሆነው ስላለመታያታቸው

ኳሳዊ ባልሆኑ አንዳንድ ነገሮች ነው ፤ ዝም ብለህ በጭንቅላትህ መበለጥ። ልምድ ነው ፤ መታረም ይችላል። ከልምድ ጋር ደግሞ ውጤቶች መጥፋት የለባቸውም። ልምድ እሰጣለሁ ብለህ ውጤት ሊጠፋ አይገባም። አሁን ያየሁት በመጫወት መበለጥ አይደለም። ሳትጫወት ባላጋራን አግዝፈህ ማየትን ነው። ሜዳ ላይ ያለኸው ግን አንተ ነህ። ማድረግ የሚገቡህን ነገሮች ትተህ በስሜት እና በሌሉ ነገሮች ተውጠህ መጫወት በሚገባህ መልኩ ሳትጫወት የመዘናጋት ነገር ሲኖር ነው።