በ9ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማዎች አዲስ አበባ ከተማን 1-0 በሆነ ውጤት በመርታት ደረጃቸውን አሻሽለዋል።
ድሬዳዋ ከተማዎች በሀዲያ ሆሳዕና ከተረታው ስብስብ ላይ አምስት ለውጦችን ሲያደርጉ በዚህም ፍሬው ጌታሁን ፣ ዳንኤል ደምሴ ፣ አቤል ከበደ ፣ አብዱራህማን ሙባረክ እና ማማዱ ሲዲቤን አስወጥተው በምትካቸውም ደረጄ ዓለሙ፣ መጣባቸው ሙሉ፣ ሱራፌል ጌታቸው፣ ጋዲሳ መብራቴ እና ሙኸዲን ሙሳን ተክተው ያስገቡ ሲሆን አዲስአበባ ከተማዎች ደግሞ አማካይ መስመሩ ላይ ሙሉቀን አዲሱን በብሩክ ግርማ ብቻ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።
የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱን በኮቪድ ምክንያት ያጡት አዲስአበባ ከተማዎች ጨዋታውን በግብጠባቂያቸው ዳንኤል ተሾመ እየመተመሩ የማድረጋቸው ጉዳይ ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ ጨዋታው እንዲጠበቅ ያደረገ አጋጣሚ ነበር።
ሁለት ኳስን የመቆጣጠር ፍላጎት ባላቸው ቡድኖች መካከል የነበረው ፉክክር አጀማመሩ ቀዝቀዝ ያለ ነበር። ነገርግን በ13ኛው ደቂቃ ላይ እንዳለ ከበደ እንየው ካሣሁን ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘችውን የፍፁም ቅጣት ምትን ሙኽዲን ሙሳ በማስቆጠር ድሬዳዋ ከተማን ገና በጊዜ ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ በኋላ እስከ መጀመሪያው የውሀ እረፍት ድረስ በነበሩት የጨዋታ ደቂቃዎች አዲስአበባ ከተማዎች የተሻለ እድሎችን መፍጠር ችለዋል። በተለይም አዲስ አበባዎች ከድሬዳዋ ከተማዎች የሚቀሟቸውን ኳሶች በፍጥነት ወደ ማጥቃት እንቅስቃሴ በማስገባት የድሬዳዋን ግብ ፈትሸዋል።
በ20ኛው ደቂቃ ከድሬዳዋ ተጫዋቾች ያቋረጡትን በፍጥነት ወደ ድሬዳዋ ግብ ያደረሱትን ኳስ ፍፁም ጥላሁን የሞከረውን ኳስ ደረጄ ዓለሙ ሲያድንበት በተመሳሳይ በ23ኛው ደቂቃ ቻርልስ ሪባኑ መሀል ሜዳ አካባቢ የቀማውን ኳስ ወደ ቀኝ መስመር ያዞ በመውጣት ያሻገረውን ኳስ ፍፁም ጥላሁን እና ሪችሞንድ አዶንጎ አከታትለው ቢሞክሩም ደረጄ በግሩም ሁኔታ ኳሶቹን አድኗል።
31ኛው ደቂቃ ላይ ግን ሱራፌል ጌታቸው ከተከላካዮች ጀርባ በረጅሙ የላከውን ኳስ ከሙኽዲን ሙሳ ጋር ለመከላከል ይታገል የነበረው የአዲስአበባ ከተማው ተከላካይ ዘሪሁን አንሼቦ ከግብጠባቂው ዋኬኔ አዱኛ ጋር ባለመግባባቶ ወደ ኃላ የገጨውን ኳስ ግብጠባቂው ኳሷን ከሳጥን ውጭ በእጅ በመንካቱ መነሻነት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል ፤ በምትኩም ወጣቱ ግብጠባቂ ኮክ ኮየት የመጀመሪያውን የሊጉን ጨዋታ ኤልያስ አህመድን ተክቶ በመግባት አድርጓል።
በሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ መነቃቃት የጀመሩት አዲስአበባ ከተማዎች በጎዶሎ ተጫዋቾች እንኳን ሆነው ድሬዳዋን ወደ ራሳቸው አጋማሽ በመግፋት የተሻለ ጫና ለማሳደር ጥረት አድርገዋል።
እርግጥ ነው የፈጠሩትን ጫና ወደ ግብ እድሎች በመቀየር ረገድ ደካማ የነበሩት አዲስአበባ ከተማዎች ልመንህ ታደሰ ከቆመ ኳስ ገጭቶ የሞከራት እንዲሁም በፍፁም ጥላሁን አማካኝነት ካደረጓቸው ሙከራዎች ውጭ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።
በተቃራኒው ድሬዳዋ ከተማዎች የነበራቸውን የቁጥር ብልጫ ተጠቅመው ጨዋታውን ለመቆጣጠር ከመሞከር ይልቅ በአዲስአበባ ከተማ በተወሰደባቸው ብልጫ ለመመከት በመከላከሉ ብዙ ጥረት እንዲያደርጉ ተገደው ተመልክተናል።
በ75ኛው ደቂቃ ላይ የድሬዳዋ ከተማው የመስመር አማካይ አብዱለጢፍ መሀመድ ሪችሞንድ አዶንጎ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ መውጣቱን ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች የመጨረሻዎቹን ደቂቃዎች በአስር አስር ተጫዋቾች ለመጨረስ ተገደዋል።
ሁለቱም ቡድኖች በቁጥር መመጣጠናቸውን ተከትሎ በተወሰነ መልኩ የተሻለ ፉክክርን የተመለከትንበት የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክተን ጨዋታው ተጠናቋል።
ጨዋታው በድሬዳዋ ከተማዎች የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ ነጥባቸውን ወደ 11 በማሳደግ ተጋጣሚያቸው የነበሩትን አዲስአበባ ከተማዎችን በግብ ክፍያ በመብለጥ 9ኛ እና 10ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ በቅተዋል።