የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 1-0 አዲስ አበባ ከተማ

እንደቀኑ ሁሉ በ1-0 ውጤት ከተጠናቀቀው የምሽቱ ጨዋታ በኋላ ተከታዩ የአሰልጣኞች ሀሳብ ተደምጧል።

አሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ – ድሬዳዋ ከተማ

ስለጨዋታው

ትንሽ ጫና ነበረው። ውጤቱ አስፈላጊ ነበር ፤ እንጂ ሜዳ ላይ በደንብ ተንቀሳቅሰናል ማለት አይቻልም። የቁጥር ብልጫም አግኝተን መጠቀም አልቻልንም። ነገር ግን እንደአጠቃላይ ውጤት ያስፈልገን ነበር። ተጫዋቾቹ ያላቸው አቅም እና አሁን ያለንበት ሁኔታ አንድ አልነበረም። እና በማንኛውም መንገድ አሸንፈን ወደ መሪዎቹ መጠጋት አለብን የሚል ሀሳብ ነበር። ያ ተሳክቶልናል ብዬ አስባለሁ።

ስለእንቅስቃሴያቸው

በውጤቱ ደስተኛ ነኝ እንቅስቃሴው ግን መስተካከል አለበት። መሀል ሜዳ ላይ በጉዳት የወጡ ተጫዋቾች አሉ ፣ ሲዲቤም አልነበረም። ከዛ ከዛ አንፃር ውጤቱ ጥሩ ነው እላለሁ። እንቅስቃሴው ግን መሻሻል አለበት።

የቁጥር ብልጫውን ስላለመጠቀማቸው

የቁጥር ብልጫውን አልተጠቀምንም። አሁን በነጥብ ከእነሱ ዕኩል ሆነናል። ተጨማሪ ጎሎች ብናገኝ በደረጃም አንድ ወደ ላይ ከፍ ማለት እንችል ነበር። ያንን መጠቀም አልቻልንም።

በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ስለመቆየታቸው

እስካሁን የነበሩ ቁጥሮች የሚያሳዩት ተጋጣሚ ሜዳ ላይ እንደምንቆይ ነበር። ዛሬ ግን ያንን አሳክተናል ብዬ አላስብም። ግን ጥሩ በነበርንባቸው ጊዜያት ውጤት ይዘን መውጣት አልቻልንም። ዛሬ ጥሩ አልነበርንም ባልንበት ሰዓት ደግሞ ውጤት ይዘን ወጥተናል። በተለይ ለደጋፊዎቻችን ይሄ ነጥብ ያስፈልጋቸው ነበር እና ይህች ስጦታ ለደጋፊዎቻችን እንድትሆን እፈልጋለሁ።

ዳንኤል ተሾመ – አዲስ አበባ ከተማ

ጨዋታውን ስለቀየረው ቅፅበት

ጨዋታውን የቀየረው የግብ ጠባቂያችን በቀይ ካርድ መውጣት ነው። ስንጀምር ቀዝቀዝ ብለን ነበር ፤ ቀይ ካርዱ ደግሞ የበለጠ አወረደን። በሁለተኛው አጋማሽ እንደነበረን እንቅስቃሴ ግን ምንም ጥያቄ የለውም ውጤት ይዘን መውጣት ነበረብን። ተጫዋቾች ቀያይረን ብልጫ ወስደን ነበር። ጥሩ እንቅስቃሴ አድርገናል።

በቁጥር ቢጎድልም ቡድኑ ስላሳየው መነሳሳት

ብዙ ጊዜ እንደምናገረው የእኛ ቡድን ሜዳ ውስጥ ሲገባ 11 ብቻ ሆኖ አይደለም። ስብስቡ ውስጥ ያለው 32ቱም ሜዳ ላይ የገባ ነው የሚመስለው። ሁሉም ይተጋገዛል ፤ አንዱ ለአንዱ ፍቅር አለው። አሰልጣኛችንም ቡድኑን ሲይዘው የቡድኑ ህብረት ላይ ነው የሳራው ፤ ለዛ ነው። ጎዶሎ አንመስልም ነበር ፤ የተሻለ ተንቀሳቅሰናል።

ከአሰልጣኝ ደምሰው ጋር በስልክ ስለነበራቸው ቆይታ

ትኩረቴ ጨዋታው ላይ ነበር ፤ አንድ ሰባቴ ሳናወራ አንቀርም። ከእኔ የተሻለ የአሰልጣኙ እይታ ነው። ክፍተቶችን እና ቅያሪዎችን ሲነግረኝ ነበር። መጨረሻ ላይም በሦስት ተከላካይ እንድንጫወት ፣ አጥቅተን እንድንጫወት ሲነግረኝ ነበር።

ከተጫዋችነት እና ከአሰልጣኝነት…

ከመቶ መቶ አንድ ተጫዋችነት ይሻላል። አሰልጣኝነት በጣም ከባድ ነው። ኳስ ሳቆም አሰልጣኝነትን እንዳላስብ ነው ያደረገኝ። ከዳኛ ጋር ያለውንም ነገር ስታይ አሰልጣኝነት ከባድ ነው። ብዙ ጊዜ 25 ተጫዋች ይዘህ ሜዳ ውስጥ የሚገባው ደግሞ 11 ነው። ተቃውሞ የሚያነሳም አለ ፤ አሰልጣኝነት በጣም ከባድ ነው።