ከፍተኛ ሊግ | የምድብ ለ 3ኛ ሳምንት ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ 3ኛ ሳምንት ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ በሰበታ ከተማ ሜዳ ተካሂዶ ካምባታ ሺንሺቾ እና ሰንዳፋ በኬ ተጋጣሚያቸውን ረተዋል።

ጠዋት በጀመረው የከፋ ቡና እና የካምባታ ሺንሺቾ ጨዋታ በካምባታ ሺንሺቾ ሁለት ለዜሮ አሸናፊነት ተጠናቋል። ከፋ ቡና ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን አሸንፎ በመምጣት ጥንካሬውን በማሳየት ቢዘልቅም በዛሬው ዕለት ዋና አሰልጣኙ አዲሴ ካሴ በሀዘን ምክንያት ከቡድኑ ጋር አለመኖራቸው በቡድኑ ውጤት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ አድርጓል። በተመሳሳይ ለጊዜው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የካምባታ ሺንሺቾ ዋና አሰልጣኝ ኤፍሬም ቡድናቸውን እየመሩ ባይገኙም ቡድኑ በዛሬው ጨዋታ ብልጫ ወስዶ በመጀመርያው አጋማሽ በ26ኛው ደቂቃ ኤፍሬም ታምራት ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ መሆን ችለዋል። በሁለተኛው አጋመሽ እንደጀመረ የካምባታ ሺንሺቾ ሁለተኛ ጎላቸውን በአጥቂው ጃፋር ከበደ በማስቆጠር መሪነታቸውን አስፍተዋል። ጨዋታውም በዚሁ ውጤት ሲጠናቀቅ ውጤቱን ተከትሎ ካምባታ ሺንሺቾ ምድቡን እንዲመራ አስችሎታል።

ዘጠኝ ሰዓት በጀመረው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ቤንች ማጂ ቡና ከሰንዳፋ በኬ ያገናኘው ጨዋታ በሰንደፋ በኬ አሸናፊነት ተጠናቋል። የመጀመርያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ወደ ጎል በመድረስ ቤንቺ ማጂ ቡናዎች የተሻሉ ነበሩ። ለዚህም ማሳያ አጥቂው አብይ ቡልቲ አምስት ከሀምሳ ውስጥ መሬት ለመሬት የመታውን ለጥቂት በአንግሉ ጠርዝ የወጣበት እንዲሁም ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን አጥቂው ወንዴ ኬር ኳሱ አየር ላይ እያለ የመታው እና ለጥቂት በግቡ አናት የወጣው ለቤንች ማጂ ቡና ወደ ጎል ለመቅረባቸው ማሳያዎች ነበሩ።

ሆኖም ግን ከ15 ደቂቃ በኃላ ሰንዳፋ በኬዎች በመጀመርያው ወደ ጎል በቀረቡበት አጋጣሚ ያገኙትን የማዕዘን ምት አንበሉ ዳኛቸው ብርሀኑ በግንባር በመግጨት ጎል በማስቆጠሩ ሰንዳፋዎችን እንዲነቃቁ አስችሏቸዋል። ጎል ቢስተናገድባቸውም በፍጥነት ወደ ፊት በመሄድ ጨዋታው ለመመለስ የሞከሩት ቤንች ማጂዎች በቶሰልች ሳይመን አማካኝነት የፈጠሩት ግብ የማግባት ዕድልን ግብጠባቂው አድኖባቸዋል። ከ30 ደቂቃ በኃላ መጀመርያዎቹ ደቂቃዎች እንደነበረው የማጥቃት እንቅስቃሴዎች እየተቀዛቀዙ የመጡት ቤንች ማጂ ሁለተኛ ጎል ሊያስተናግዱ የሚችሉበት አጋጣሚ ሰንዳፋ በኬዎች ቀድሞ በኢትዮጵያ ቡና ተስፋ ቡድን ሲጫወት የምናቀው ቅዱስ ተስፋዬ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

የጨዋታው ሚዛን ወደ ሰንዳፋ በኬ ተቀይሮ አንድ ግልፅ የጎል አጋጣሚ አቤል ታምራት በግብጠባቂው ከመከነበት ከጥቂት ደቂቃ በኃላ ዳግመኛ ወደ ፊት የሄዱት ሰንዳፋ በኬዎች ተቀይረው በገባው ታምሩ ባልቻ አማካኝነት ሁለተኛ ጎል አስቆጥረው መሪነታቸውን ማስፋት ችለዋል። ለዚህች ጎል መቆጠር የግብጠባቂው ከፍያለው ሀይሉ ስህተት የጎላ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ በቀጠለው ይህ ጨዋታ ቤንች ማጂዎች ግልፅ ባልሆነ መንገድ ክፍት ቦታ ፈልገው ጎል ለማስቆጠር ሲቸገሩ በአንፃሩ ሰንዳፋዎች በከፍተኛ ሊግ የመጀመርያ ተሳትፏቸው ሦስት ነጥብ ለማሳካት በጥንቃቄ እየተከላከሉ በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ጎል ባያስቆጥሩም ጯና ፈጥረው ጨዋታውን ተቆጣጥረው አሸንፈው ሊወጡ ችለዋል።