ከአቻ እና ከሽንፈት መልስ እርስ በእርስ ሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻን የሚያገናኘው ጨዋታ ላይ ተከታዮቹ ነጥቦች ተነስተዋል።
ድል ካደረጉ ስድስት የጨዋታ ሳምንታት ያለፋቸው ሲዳማ ቡናዎች ከገቡበት የውጤት ማጣት ቀውስ ለመውጣት እና በደረጃ ሰንጠረዡ መሻሻልን በማግኘት ወደ እረፍት ለመሄድ ነገ ጠንክረው እንደሚጫወቱ ይታመናል።
ሲዳማ ቡና ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከመከላከያ ጋር ተጫውቶ ያለ ግብ አቻ ሲለያይ ዳይመንድ የሚመስል የአማካይ የተጫዋቾች አደራደር ቅርፅ ይዞ ነበር ወደ ሜዳ የገባው። ይህ የአደራደር ቅርፅ በመሐል ሜዳው ላይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንዲኖረው ቢያደርግም ግን የዳይመንዱ ግራ እና ቀኝ ያሉት ተጫዋቾች በማጥቃቱ ረገድ የነበራቸው ተሳትፎ እጅግ ውስን ነበር። ከሁለት አንዱ በተለይ ደግሞ ዳዊት ተፈራ ወደ ፊት እየሄደ የተጋጣሚ የመከላከል ወረዳ ላይ ቡድኑ የቁጥር ብልጫ እንዳይወሰድበት ይጥራል ቢባልም ወደ ኋላ ይቀር ነበር። በዚህም ምክንያት ሲያጠቁ ፊት ላይ ያላቸው የተጫዋቾች ቁጥር ይመናመን እና ለተጋጣሚ ተከላካዮች ምቹ ይሆን ነበር። ይህ ጉዳይ ደግሞ ቡድኑ በነገው ጨዋታ የግድ ሦስት ነጥብ ማግኘት ካሰበ ሊያስተካክለው የሚገባ ቀዳሚው ጉዳይ ነው።
ቡድኑ ያለበት የውጤት ማጣት አጠቃላይ ቡድኑን ፈሪ ያደረገው ይመስላል። ሀላፊነት (ሪስክ) ወስዶም ለማጥቃት ሲያመነታ ይታያል። በመጀመሪያዎቹ የሊጉ ጨዋታዎች ላይ በተደጋጋሚ ሲያደርጋቸው የነበሩ የመስመር ላይ ጥቃቶችም ከጨዋታ ጨዋታ እየወረዱ መጥተዋል። ምባልባት የቡድኑ ዋነኛ የማጥቂያ አማራጭ እንደሆነ የሚታሰበው የመስመር አጨዋወቱ ከተስተካከለ እና የመስመር ተከላካዮቹም በድፍረት እንዲያጠቁ ከተደረገ ቡድኑ አዎንታዊ ውጤት ሊያገኝ ይችላል። ከዚህ ውጪ በሊጉ ባደረገው የመጀመሪያ ሁለት እና የመጨረሻ አንድ ጨዋታዎቹ ላይ ብቻ ግቡን ያላስደፈረው ቡድኑም ከወላይታ ድቻ የሚጠበቀውን ፈጣን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት እንዴት ይመክታል የሚለው የሚጠበቅ ነው።
ሳይጠበቅ ራሱን የዋንጫ ተፎካካራ አድርጎ የነበረው ወላይታ ድቻ ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ዳግም ሦስት ነጥብን በማሳካት በፉክክሩ ለመዝለቅ እና ከወቅታዊ መጥፎ ብቃቱ ለመውጣት ሌላኛውን በመጥፎ የውጤት ጉዞ ላይ የሚገኘውን ሲዳማ ለማሸነፍ ብሩቱ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ ይታሰባል።
ወላይታ ድቻ ከሦስት ተከታታይ ከባድ ተጋጣሚዎች በኋላ በወቅታዊ ብቃት አንፃራዊ አሉታዊ ውጤት ላይ የሚገኝ ቡድን ነገ ያገኛል። ቡድኑ የውድድር ዓመቱ ሦስተኛ ተከታታይ ደግሞ ሁለተኛ ሽንፈቱን ባሳለፍነው ሳምንት ሲያስተናግድ ወደ አራት የተከላካዮች ጥምረት ተመልሶ ነበር። ይህ ቢሆንም ግን ቡድኑ በተከታታይ ጨዋታዎች በሦሰት የመሐል ተከላካዮች ጥምረት ሲጫወት ስለነበር በአራት የኋላ የተጫዋች አደራደር ቅርፅ እየተጫወተም ከሦስት ተከላካካይ መንፈስ የተላቀቀ አይመስልም ነበር። በእንቅስቃሴም አራቱ ተከላካዮች ሲያጠቡ እና መስመሩን ሲከፍቱ ሲታይ ነበር። ነገ ቡድኑ የሚመርጠው አጨዋወት ባይታወቅም ግን በአራት ተከላካዮች ከገባ ይህንን ለተጋጣሚ የመስመር አጥቂዎች ምቹ ሁነት የሚፈጥረውን ክፍተት አርሞ መቅረብ የግድ ይለዋል። አለበለዚያ ሊቀጣ ይችላል።
በጨዋታ የመነሻ ሀሳብ ለመከላከል ቅድሚያ የሚሰጠው ወላይታ ድቻ በቅዱስ ጊዮርጊስ ብልጫ ተወስዶበት ሲረታ በማጥቃቱ ረገድ የነበረው ተነሳሽነት እጅግ የወረደ ነበር። የመስመር ተጫዋቾቹም ሆነ ሁለቱ የአማካይ መስመር ተጫዋቾች (ከእድሪስ ውጪ) ወደ ፊት እምብዛም ሲሄዱ ስላልነበር ቡድኑ ለማጥቃት ሲሞክር በመጨረሻው ሲሶ ሦስት ወይም አራት ብቻ ተጫዋቾችን እንዲያገኝ ይሆናል። ይህ ደግሞ እንደ ሲዳማ ቡና ፊት ላይ መሳሳትን አምጥቶበት ነበር። ይህንን ተከትሎም በጨዋታው አንድም ዒላማውም የጠበቀ ሙከራ ሳያደርግ ከሜዳ ወጥቷል። የስንታየሁ አለመኖር ደግሞ በመልሶ ማጥቃት እና በረጃጅም ኳሶች ደካማ እንዲሆን አድርጎታል። ነገ ግን ይህ አጥቂ ከጉዳቱ አገግሞ መምጣቱ የሳሳውን የፊት መስመር ያሰላል ተብሎ ይጠበቃል።
ሲዳማ ቡና አንድ ተጫዋች ብቻ በነገው ጨዋታ አያገኝም። እርሱም የመስመር ተከላካዩ አማኑኤል እንዳለ ነው። ወላይታ ድቻ ደግሞ በነገው ጨዋታ ቁመታሙን አጥቂ ስንታየሁ መንግስቱን ማግኘቱ ትልቁ ዜና ሲሆን የሌላኛው አጥቂ ምንይሉ ወንድሙ መሰለፍ ግን አጠራጣሪ ነው ተብሏል። ከዚህ ውጪ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ፣ አንተነህ ጉግሳ እና ዘካሪያስ ቱጂ ግን ጉዳት ላይ በመሆናቸው ከነገው ፍልሚያ ሙሉ ለሙጉ ውጪ መሆናቸው ተመላክቷል።
ይህንን ጨዋታ ፌዴራል ዋና ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ በአልቢትርነት የሚመሩት ይሆናል።
እርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 14 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ ሁለት ጨዋታ ሲያሸንፍ በአምስት ጨዋታ አቻ ተለያይተው ሲዳማ ቡና ሰባት ጊዜ አሸንፏል። በሁለቱ ግንኙነት እስካሁን 22 ጎሎች ሲቆጠሩ ወላይታ ድቻ 8 ፣ ሲዳማ ቡና 14 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።
ግምታዊ አሠላለፍ
ሲዳማ ቡና (4-3-1-2)
ተክለማርያም ሻንቆ
ምንተስኖት ከበደ – ጊት ጋትኩት – ያኩቡ መሐመድ – መሐሪ መና
ቴዎድሮስ ታፈሰ – ሙሉዓለም መስፍን – ዳዊት ተፈራ
ፍሬው ሰለሞን
ብሩክ ሙሉጌታ – ይገዙ ቦጋለ
ወላይታ ድቻ (4-3-3)
ፅዮን መርዕድ
ያሬድ ዳዊት – ደጉ ደበበ – በረከት ወልደዮሐንስ – አናጋው ባደግ
እድሪስ ሰዒድ – ንጋቱ ገብረሥላሴ – ሐብታሙ ንጉሤ
ቃልኪዳን ዘላለም – ስንታየሁ መንግስቱ – ቢኒያም ፍቅሬ