የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከጨዋታ በኋላ ተከታዩን አስተያየት በስፍራው ለተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ሰጥተዋል።
ስለጨዋታው…
በጨዋታው ጥሩ ቅርፅ ላይ አልነበርንም። ተጋጣሚያችን በብዙ ነገር የበላይነቱን ወስዶብን ነበር። ቡድናችን ከዚህ ቀደም እንደነበረው አልነበረም። በተለይ በመከላከሉ ረገድ የተቀናጀን አልነበርንም ፤ በተጨማሪም ከተጋጣሚ የሚመጣውን ጫና መቋቋም አልቻልንም። በመጀመሪያው አጋማሽ ደግሞ ጥሩ ሳንሆን አንድ ጎል አስተናግደናል። በአጠቃላይ በጨዋታው ጥሩ አልነበርንም ፤ ጊኒዎች ማሸነፍ ይገባቸው ነበር።
በጨዋታው ጥሩ ስላልተንቀሳቀሱበት ምክንያት…
አንዳንድ ጊዜ እንደዛሬው መጥፎ ቀናት አሉ። እንዳልኩት ከግብ ዘቡ ውጪ በሁሉም ነገሮች በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ አልነበርንም። በጣም በኃይለኛው ነበር ጫና ሲያሳድሩብን የነበረው። ይህንን ጫና መቋቋም አልቻልንም። በቀላሉ ኳሶችን እያጣን ለእነሱ እየሰጠንም ነበር። በአጠቃላይ በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድናችን ጥሩ አልተንቀሳቀሰም። በአንፃሩ በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ኳሱን ለመቆጣጠር ሞክረን ነበር። ግን ደግሞ በራሳችን የቅጣት ምት በሽግግር ሁለተኛውን ጎል አስተናግደናል። እንዳልኩት የዛሬው ቀን እንደ ሌላው ቀናችን አልነበረም። በእግርኳስ እንደዚህ አይነት ቀናት አሉ ፤ አንዳንድ ቀናት መጥፎ ናቸው። ዛሬ ሁሉም ነገሮች ለጊኒዎች ነበር። ማለት የምችለው የዛሬው ቀን ጥሩ ቀናችን አልነበረም።
ስለግብ ዘቡ ሰዒድ ብቃት…
ሰዒድ ልምምድ የሌለው ግብ ጠባቂ ነው። ግን በጥሩ ብቃት ወደፊቱን አሳይቶናል። በእርሱ የዛሬ ብቃትም ደስተኛ ነኝ።
ስለመጀመሪያው አጋማሽ እንቅስቃሴ መዳከም…
አንዳንድ ቀኖች በሁሉም ነገር ትበለጣለህ። ቡድናችን ደከም ያለው ከተጋጣሚያችን አንፃር ነው ብሎ መናገር ይከብደኛል ፤ ምክንያቱም ጊኒ ጠንካራ ቡድን እንደሆነ ብናውቅም ከጊኒ የበለጠ ከብዙ ጠንካራ ቡድኖች ጋርም ተጫውተን ጥሩ ብቃት ነበረን። ዛሬ ምናልባት ከስነ-ልቦና ጋር ተያይዞ ክፍተት ካለ እናያለን። ከዚህ በተረፈ ግን ከጨዋታ አቀራረብ ጋር ተያይዞ ሌላ ለውጥ አላደረግንም። የዛሬውን ቀን እንደ አንድ ብልሹ ወይም መጥፎ ቀን ነው አርጌ የምወስደው።
የማጥቃት አጨዋወቱ ስለመዳከሙ…
ስለአጥቂዎቹ ከማውራታችን በፊት ጨዋታው ከመሰረቱ ተበላሽቶ ነበር። እርግጥ ነው የተወሰኑ ዕድሎችን አግኝተናል ፤ ግን ጥራታቸው በቂ ነው ብሎ መናገር ግን ያስቸግረኛል። ስለዚህ ከመሰረቱ ነው የተበላሸው። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ከተጫዋቾች ቅያሪ በኋላ በተወሰነ መልኩ ወደምንፈልገው መንገድ ለመመለስ ሞክረናል። በሂደት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሞክረናል። ከፊትም ያሉንን ተጫዋቾች ነው ለዚህ ጨዋታ ይሆናሉ ብለን ያሰብናቸውን ያስገባነው። ጎል እስካላገባም ድረስ ተቀርፏል ማለት ባልችልም ጎል ለማግባት መንገዳችን መስተካከል ነበረበት። ሌላ ጊዜ በተደራጀ ሁኔታ መጥተን ነበር የምንስተው ዛሬ ግን በዚህ ደረጃ ጥሩ አልነበርንም። ስለዚህ አጥቂዎቹን መውቀስ አልፈልግም።
ስለተጫዋች ቅያሪ…
ጋቶች ቢጫ አይቶ ነበር። ከእረፍት በፊት ሶስት ቢጫ አይተናል። ይህንን ተከትሎ ከሚጫወትበት ቦታ አንፃር ለተጨማሪ ቢጫ የሚዳረግበት ዕድል ስለሚኖር አንዳቸውን መጠበቅ ነበረብን። በተጨማሪም ኳሱን ከመቆጣጠር ጋር ተያይዞ ሁለት የተከላካይ አማካይ ኖሮ ጫናውን መቀነስ ካልቻልን ቢያንስ ኳሱን የመያዝ አቅሙን የጨመረ ሰው እዛ ጋር በማስገባት የተሻለ ለመቆጣጠር በማሰብ ነው። ይህም ስኬታማ ነበር።
ስለቀጣዩ ጨዋታ…
የምድቡ 3ኛ እና 4ኛ ጨዋታዎች ወሳኝ ጨዋታዎች ናቸው። ዛሬ ተሸንፈናል ግን ነገ ሌላ ቀን ነው። ቀጣዩን ጨዋታ ለማሸነፍ ዕኩል ዕድል ነው ያለን። ለጨዋታውም በተሻለ ለመዘጋጀት ሞክረን ዛሬ የነበሩንን ክፍተቶች ለማየት እንጥራለን። ከጨዋታውም የተሻለ ነጥብ ለማግኘት እንሞክራለን።