የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 0-1 ሀድያ ሆሳዕና

በዝናባማ አየር ምሽት ላይ የተካሄደው የኢትዮጵያ ቡና እና የሀድያ ሆሰዕና ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኃላ አሰልጣኞቹ ለሱፐር ስፖርት ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀድያ ሆሳዕና

የቡድናቸው ዕድገት እንዴት ይገለፃል

ሲጀመር ቡድናችን ከመሸነፍ ወደ አቻ በኃላም ወደ ማሸነፍ መጥቷል። ከዚህ በፊትም ገልጨዋለው የጊዜ ጉዳይ እንጂ እያደገ የሚመጣ ነው። ለምን ልምድ ያላቸው አቅም ያላቸው ሜዳ ውስጥ የማይቸገሩ ልጆች ናቸው። ይህ ነገር እንደሚመጣ የሚገመት ነው። ይህ ቢሆንም ግን በሥስቱ ጨዋታ ላይ ማሸነፍ ብንችልም አለቀ ማለት አይደለም። ከዚህ በኃላ ብዙ የሚጠብቁን ስራዎች አሉ እርሱን እያስተካከልን ከእረፍታችን በኃላ በተሻለ ለመሆን እንሞክራለን።

የተጋጣሚን የመጫወቻ ግማሹን ሜዳ እንደሚፈልጉት ስለማግኘታቸው

በእርግጥ መጀመርያ ላይ እንዳሰብነው መሄድ አልቻልንም። የምንጫወተው በጣም ጠንካራ እና ኳስን መሠረት አድርጎ ከሚጫወት ቡድን ጋር ስለሆነ ትንሽ ተቸግረን ነበር። ከእረፍት በኃላ ቀይረን አራት ሦስት ሦስት ጎሉን ካገባን በኃላ ወደ አራት አምስት አንድ መጥተናል። ይህን ያደረግነው ተጋጣሚያችን ክፍት ቦታ እንዳያገኝ ነው። ልጆቼ ከዚህ በፊት ያደርጉት የነበረ ነው ነገ ከነግወዲያ ደግሞ እንደ ተጋጣሚያችን አጨዋወት ያደርጉታል ብዬ አስባለው።

በተጋጣሚ እንቅስቃሴ ስህተት ስለ መፈለጋቸው

በእርግጥ የምንጫወተው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነው። ብዙ ኳሶችን መስርተው ስለሚወጡ ወደ እኛ የሜዳ ክፈረል ከመጡ እንቸገራለን። ከዛው ጀምሮ አፍኖ ለመጫወት እንጂ እግርኳስ በየትኛውም መንገድ ስህተቶችን ተጠቅመህ ነው የምትጠቀመው። ይህም ብቻ ሳይሆን እንደየክለቦቹ የምንጠቀማቸው ነገሮች አሉ። ኢትዮጵያ ቡና ተጭነን ብንጫወት ዕድል እንፈጥራለን የሚል ነበር ሞክረን የመጣነውከእረፍት በፊት ይህን ልናሳካ አልቻልንም። ከእረፍት በኃላ ግን ወደ አራት ሦስት ሦስት መጥተን ዕድሎችን ለማግኘት ችለናል። ሆኖም ከአጠቃቀም ላይ ክፍተቶች አሉብን። ተጋጣሚያችን በጣም ጠንካራ ስለሆነ ብዙ ዕድሎች ለማግኘት እንቸገራለን። ላዛ ነው በአራት አምስት አንድ ሜዳውን ለቀን የመጣነው ለምን እነርሱ ጋር ክፍተት ካገኙ በጣም ምርጥ አጥቂዎች አቅም ካላቸው ተጫዋቾች እንዲሁም ከምርጥ አሰልጣኝ ጋር ስላሉ ቦታ ካገኙ ሊያገቡብን ስለሞችሉ በአቅማችን ውጤቱን አስጠብቀን አሁን ካለንበት ደረጃ ከፍ ለማለት ስላሰብን ነው ይሄን ያደረግነው።

አሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለ ጨዋታው እንቅስቃሴ

አጠቃላይ የነበረው ነገር ጥሩ ነው። ያው ውጤቱን አጥተናል። ግን እንቅስቃሴው መጥፎ አይደለም። በጣም ማፈን ነበር በዚህም በጫና ውስጥ ሆነው ነው ልጆቹ የተጫወቱት በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሂደቱን የሚያስጠብቁበት መንገድ ጥሩ ነበር። አንዳንዳንድ ስህተቶች ነበሩ ማረም የነበሩብን የተከፈቱ ቦታዎችን በትክክል ያለማየት በተለይ መስመር ላይ ያሉ ልጆች አንዳንድ ጊዜ ስህተት ነበረ። በተረፈ ግን ጥሩ ነበር እንቅስቃሴው።

ተጋጣሚ ቡድን ተጭኖ ስለተጫወተበት መንገድ

በዚህ ጫና ውስጥ ኳሶች ይበላሹ ነበር። አንዳንዴ ደግሞ ሂደቱን የምናስቀጥልበት ዕድል ነበር። ምክንያቱም አንድ ቡድን ዘጠናውን ደቂቃ ሙል ተጭኖ መጫወት አይችልም። ክፍተቶችን በምናገኝበት ወቅት እንዴት መሄድ እንዳለብን ተነጋግረን ነበር። ጫናዎች ነበሩ ግን በዚህ ሂደት ውስጥ ክፍተቱን ለመጠቅም ተሞክሮ ነበር አንዳንድ ጊዜ ስኬታማ ነበር። አንዳንዴ ደግሞ ስህተቶች ይፈጠሩ ነበር።

የተዘጉ ቦታዎችን ለማስከፈት ስለ ተጫዋቾች ትዕግስት

በአጠቃላይ ጥሩ ነው ማለት የሚቻለው። አንዳንድ ጊዜ የተዘበራረቀ ነገር አለ። ወደ አልተመቸ ቦታ ኳሱ የሚሄድበት ሁኔታ አለ። አጠቃለይ ግን እዛ ውስጥ ለመቆየት የሚያደርጉት ጥረት ጥሩ ነበር።

በቆሙ ኳሶች ኢትዮጵያ ቡና ይቸገራል

የቆሙ ኳሶች ላይ ለሚሞክረውም ለሚሞከርበትም በጣም አመቺ ነው ማለት አይቻልም። አንዳንድ ጊዜ የሚዘበራረቅ ነገር ስላለ የሚያገኘውን ሰው አታቀውም። መጀመርያ የያዝከውን ሰው ልታጣው ትችላለህ እርሱን ለማግኘት ስትል በሌሎች ሰዎች ልትጋረድ ትችላለህ። የቆሙ ኳሶች ላይ በግንባር የሚገጩ ምን አልባት ሊኖሩ ይችላሉ። እነዛም ሰዎች ዕድሉን የማያገኙበት ሁኔታ አለ ይሄ ነው ለማለት ትንሽ ያስቸግራል። በሆነ ክፍተት ዕድል የሚገኝበት ስለሆነ የተቻለህን ጥረት ታደርጋለህ።