በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ የነበሩት የትግራይ ክልል ክለቦች በወሳኝ ጉዳዮች ዙርያ ለመወያየት ቀጠሮ ይዘዋል።
የትግራይ እግርኳስ ፌደሬሽን በስሩ ካሉ ክለቦች ለመነጋገር ቀጠሮ መያዙ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። በነገው ዕለት ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው እና ሦስቱ በፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ የነበሩት ክለቦች መቐለ ሰባ እንደርታ ፣ ወልዋሎ ዓ/ዩ እና ስሑል ሽረን የሚያሳትፈው ይህ ስብሰባ በዋነኛነት ክለቦቹ ከጦርነቱ በኋላ ያሉበትን ሁኔታ ለመገምገም ያለመ ሲሆን ወደ ቀድሞው እንቅስቃሴያቸው ለመመለስ ስለምያስፈልጓቸው ዐበይት ነገሮች ዙርያም ሰፊ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ በመቐለ የሚካሄደው ስብሰባ ከሦስቱ ክለብ ተወካዮች በተጨማሪም ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንደሚሳትፍ ሲሰማ ክለቦቹ ላለፉት ሳምንታት ካደረጉት የውስጥ ስብሰባ በኋላ \’በቀጣይ እንደ ክለብ ይቀጥላሉ ወይስ አይቀጥሉም ?\’ የሚለው ነገር በመድረኩ ቁርጡ ይለይለታል። ፌደሬሽኑ በነገው ዕለት ከሦስቱ ክለቦች ጋር ከተወያየ በኋላም ከተቀሩት የከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ ክለቦች ጋር ለመነጋገር ከወዲሁ መዘጋጀቱም ሰምተናል።