በነገ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቀዳሚ መርሐ ግብር ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።
ሰበታ ከተማ ከስምንት ሳምንታት ቆይታ በኋላ ያሳካውን የመጀመሪያ ድል ይዞ ከወልቂጤ ከተማ ጋር የሚገናኝበት ጨዋታ ጥሩ ፉክክር እንደሚያስመለክተን ይጠበቃል። ወራጅ ቀጠና ውስጥ ከሚገኘው የነገ ተጋጣሚያቸው በስምንት ደረጃዎች ከፍ ብለው የተቀመጡት ወልቂጤዎች የደረጃ ልውውጥ በበረከተበት ሊግ ተከታታይ ሽንፈት ላለማስተናገድ ከፍ ባለ ትኩረት ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል። ሰበታ ከተማም ውድድሩ ወደ ዕረፍት ከማምራቱ በፊት ሁለተኛ ድሉን ማሳካት ከቻለ ወደ ደረጃው ወገብ የመጠጋት ዕድል ያለው በመሆኑ በቀላሉ የሚመለከተው ጨዋታ አይሆንም።
ሁለቱም ተጋጣሚዎች የኳስ ቁጥጥርን መሰረት ያደረገ አቀራረብን ሲከተሉ ይስተዋለል። ይህም መሀል ሜዳ ላይ የሚኖረው ፍልሚያ ጨዋታውን የመወሰን አቅሙን ከፍ ያደርገዋል። በቅርፅ ደረጃ ሰበታ ከተማ አማካይ ክፍል ላይ የቁጥር ብልጫን ሊይዝ መቻሉ ተጠቃሚ ቢያደርገውም ወልቂጤ ከተማ የተሻለ የማጥቃት ተሳትፎ የሚያደርጉ የመስመር ተከላካዮችን መያዙ እና ጌታነህ ከበደንም ወደ ኋላ የመሳብ ዝንባሌ ስላለው ፍልሚያውን ከፍ እንደሚያደርገው ይታሰባል። ያም ሆኖ ወልቂጤ ከተማ በእስካሁኑ ጉዞው የኳስ ቁጥጥር ላይ ያተኩር እንጂ በሚፈልገው መጠን ዕድሎችን ሲፈጥር አይታይም። በዚህ ረገድ ተመሳሳይ አቀረራረብ ከነበረው ኢትዮጵያ ቡና ጋር ተዳክሞ መታየቱ ኳስ ለመያዝ ፍላጎት ካለው የነገው ተጋጣሚው ጋር ኳሶችን በቶሎ ወደ ፊት በማድረሱ በኩል ተሻሽሎ እንዲመጣ ይጠበቅበታል።
በሰበታ ከተማም በኩል ይኸው ችግር በተደጋጋሚ ይተይ የነበረ ሲሆን በመጨረሻው የጅማ አባ ጅፋር ጨዋታ በተሻለ ሁኔታ የመጨረሻ ዕድሎችን ሲፈጥር ታይቷል። ሆኖም ከሙከራዎቹ አንድ ሦስተኛው ብቻ ኢላማቸውን መጠበቃቸው ለቡድኑ ሌላኛው ችግር ሆኖ ታይቷል። ከዚህ ባለፈም ከደካማ ተጋጣሚ ጋር በኳስ ምስረታው ረገድ ያሳየውን መሻሻል ነገ የመድገሙ ጉዳይ በራሱ ተጠባቂ ነው። ይህ ሀሳብ በተለይም የተጋጣሚው የአማካይ ክፍል የቅርፅ እና የተጨዋች ለውጥ ሳያደርግ ከመቆየቱ አንፃር ሲታይ መሀል ላይ ብዙ ለውጦችን ሲሞክር ለሚታየው ለሰበታ ከተማ ቀላል ፈተና ላይሆን እንደሚችል ይገመታል። ፈተናውን የሚያቀልለት ግን አልፎ አልፎ ከተጋጣሚ ተከላካይ መስመር ጀርባ በቅጥታ ለመግባት የሚሞክርባቸውን አጋጣሚዎች ከተሻሻለ የአጨራረስ ብቃት ጋር ይዞ ወደ ሜዳ ከገባ ይመስላል።
የወልቂጤ ዋነኛ ጠንካራ ጎን ሆኖ የቀጠለው ወጥ የሆነ ቀዳሚ ተሰላፊዎችን የመጠቀም መንገድ ከማጥቃቱ በላይ በመከላከሉ ይገለፃል። የቡድኑ የመከላከል ውህደት ጥንካሬ በሊጉ ከፋሲል እና ጊዮርጊስ ጋር ጥቂት ግብ የተቆጠረበት (4) ቡድን አድርጎታል። እስካሁንም በአምስት ጨዋታዎች ግብ አለማስተናገዱ ለሰበታ አጥቂዎች የሚያስተላልፈው መልዕክት ስለመኖሩ መናገር ይቻላል። ሰበታዎችም በተመሳሳይ በአራት ጨዋታዎች መረባቸው ያልተደፈረ ቢሆንም ከዚህ በተቃረነ መልኩ በሁለት ጨዋታዎች ሰባት ጎሎችን ማስተናገዳቸው ከመከላከል ባሻገር የቡድኑን የሥነ ልቦና ስስነት የሚያሳይ መሆኑ ከድል በኋላ ይህ ችግር ይቀረፍ ይሆን ብለን እንድንጠብቅ ያደርገናል።
በነገው ጨዋታ የሰበታ ከተማዎቹ መሐመድ አበራ ፣ አክሊሉ ዋለልኝ ፣ ታፈሰ ሰርካ እና ጌቱ ወልደአማኑኤል በጉዳት ምክንያት የማይኖሩ ሲሆን አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ ከጉዳት በረከት ሳሙኤል ደግሞ ከቅጣት ተመልሰዋል። ወልቂጤ ከተማ ግዙፉን ግብ ጠባቂው ሲልቪያን ግቦሆን በቅጣት ሲያጣ መጠነኛ ጉዳት ያለበት አማካዩ በኃይሉ ተሻገር መሰለፍም አጠራጣሪ ሆኗል።
ፌደራል ዳኛ ተፈሪ አለባቸው ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ይመሩታል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱን ቡድኖች ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ ባገናኙት የአምናዎቹ ጨዋታዎች ሰበታ ከተማ በሁለቱም ዙሮች በተመሳሳይ የ1-0 ድልን ማሳካት ችሏል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)
ለዓለም ብርሀኑ
ጌቱ ኃይለማሪያም – ቢያድግልኝ ኤሊያስ – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ
ክሪዚስቶም ንታምቢ – አንተነህ ናደው
ሳሙኤል ሳሊሶ – ሀምዛ አብዱልሀሚን – ዱሬሳ ሹቢሳ
ፍፁም ገብረማርያም
ወልቂጤ ከተማ (4-4-2 ዳይመንድ)
ሰዒድ ሀብታሙ
ተስፋዬ ነጋሽ – ዮናስ በርታ – ውሀብ አዳምስ – ረመዳን የሱፍ
ሀብታሙ ሸዋለም
ያሬድ ታደሰ – በኃይሉ ተሻገር
አብዱልከሪም ወርቁ
ጌታነህ ከበደ – እስራኤል እሸቱ