ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ጅማ አባጅፋር

ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባጅፋር በአስራ ሦስት ነጥቦች እንዲሁም አስራ ሦስት ደረጃዎች ተበላልጠው የሚያደርጉትን የነገ ጨዋታ እንደሚከተለው ቃኝተነዋል።

ነገ አስራ ሁለት ሰዓት ላይ የሚደረገው ጨዋታ በሁለት የተለያየ መንገድ ላይ የሚገኙ ክለቦችን የሚያፋልም መርሐ-ግብር ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ የስምንት ሳምንት ጉዞ አንድም ጨዋታ ያልተሸነፈ ብቸኛው ክለብ ሲሆን ጅማ አባጅፋር ደግሞ በሊጉ በርካታ ጨዋታዎችን የተረታ (7) ክለብ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ጊዮርጊስ ከሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ እና ወልቂጤ ከተማ ጋር በጣምራ በሊጉ ዝቅተኛ ግብ ያስተናገደ ክለብ መሆኑ ሲታወቅ ጅማ አባጅፋር ደግሞ በተቃራኒ 14 ግቦችን ተቆጥረውበታል። ታዲያ ጊዮርጊስ በዚህ አዎንታዊ ሪከርዱ ለመቀጠል ጅማ ደግሞ የዓመቱን የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ ለማግኘት የሚያደርጉት ፍልሚያ ትልቅ ትኩረትን እንደሚስብ ይታሰባል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወላይታ ድቻ ጋር በነበረው ጨዋታ የወትሮ ቀጥተኛነቱ አልነበረም። ምክንያቱም ወላይታ ድቻ እጅግ አፈግፍጎ ሲጫወት ስለነበረ። ነገ ግን በአንፃራዊነት ኳስን ለመቆጣጠር ከሚጥር ቡድን ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ደግሞ ያለው ፍላጎት የሚጠበቅ ይሆናል። በተለይ ደግሞ ጅማ አባጅፋር ውጤት ስለሚያስፈልገው ተከላክሎ ላይጫወት ይችላል። ከዚህም መነሻነት ቡድኑ ወደ ቀጥተኛ አጨዋወቱ የሚመለስበት ዕድል ሊኖር ይችላል። የአሠልጣኝ ዘሪሁን ተጫዋቾች ከድቻ ጋር በነበረው ጨዋታ ግን ኳስ ለመያዝ በጣም ሞክረው ነበር። እስማኤል አውሮ-አጎሮ እና አማኑኤል ገብረሚካኤልም የተከላካዮችን ትኩረት ለመሳብ ወደ መሐል ሜዳ የሚሳቡባቸው አጋጣሚዎችም ነበሩ። ድቻ ግጥግጥ ብሎ ከመጫወቱ መነሻነትም እንደ ወትሮው ባይሆንም በመስመሮች በኩል ለማጥቃት ሲጥሩ ነበር። በተለይ ደግሞ አቤል ያለው ወደ ሀፍ ስፔስ እየገባ የግብ ዕድሎችን እየፈጠረ ነበር። በቅርብ ጊዜያትም ተጫዋቹ የግብ ምንጭ እየሆነ ይገኛል። በተለይ የተጋጣሚ አጨዋወት አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ የእሱ የግል ብቃቶች ያስፈልጋሉ። ነገም በዚሁ ሁኔታ የቡድኑ የመስመር አጨዋወት ለግብ ማስቆጠሪያነት ይጠበቃል።

ጅማ አባጅፋር በእንቅስቃሴ ደረጃ መሻሻል እያሳየ የነበረ ቢሆንም በሰበታው ጨዋታ ግን መውረድ አሳይቷል። በተለይ በማጥቃቱ ረገድ ከሰበታው ጨዋታ በፊት በተደረጉት ሁለት ጨዋታዎች ያሳየውን መሻሻል ማሳደግ ባለመቻሉ እና ቡድናዊ ቅርፁን ማስጠበቅ ባለመቻሉ ቀስ በቀስ ወደ ቀድሞ ችግሩ የገባ አስመስሎታል። ጅማ ኳስን ለመመስረት የሚያሳየው ጥድፊያም በተወሰነ መልኩ ዋጋ እያስከፈለው ነበር። ከዚህ ውጪ አልፎ አልፎም ቢሆን የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን ሲፈጥር ነገርግን ከውጤት ማጣቱ በመነጨ በሚመስል መልኩ ዕድሎቹን የመጠቀም ችግር ታይቶበታል። በተጨማሪም ለውጤት ፍለጋ በሙሉ ኃይል በማጥቃት እና በመጠንቀቅ መሐል ሲዋልል ለአደገኛ መልሶ ማጥቃቶች የተጋለጠበት ቅፅበትም አስመልክቷል። በነገው ጨዋታ ግን ውጤቱ እጅግ ስለሚያስፈልገው በሙሉ ትኩረት ግብ ለማስቆጠር እደሚጫወት ይታመናል። ከሰባት ጨዋታዎች ቅጣት በኋላ የሚሰለፈው ዳዊት እስቲፋኖስ ደግሞ በመሐል ሜዳው የሚሰጠው እርጋታ እና ለፊት መስመር ተጫዋቾቹ የሚያመቻቻቸው ኳሶች ለቡድኑ ውጤት አምጪ ሊሆኑ ይችላሉ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ አማካዩን በረከት ወልዴን ብቻ ነገ ያጣል። ጅማ አባጅፋር በሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ተጫውቶ አንድ ለምንም ሲሸነፍ ከሜዳ ተቀይሮ ከወጣ በኋላ በ87ኛው ደቂቃ ያልተገባ ድርጊት ፈፅሟል በሚል ቀይ ካርድ ተሰጥቶት በአወዳዳሪው አካል ደግሞ የሰባት ጨዋታዎች ቅጣት ተላልፎበት የነበረው ዳዊት እስቲፋኖስ ቅጣቱን በመጨረሱ ነገ ለጨዋታው ዝግጁ ነው። አልሳህሪ አልማህዲ ብቻ ግን በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆኗል።

ይህንን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በአልቢትርነት የሚመሩት ይሆናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ቡድኖቹ ለስድስት ጊዜ ከተገናኙባቸው አጋጣሚዎች ውስጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሦስት በማሸነፍ የበላይ ሲሆን ጅማ አባ ጅፋር ሁለቴ ድል አድርጎ ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። በስድስቱ ግንኙነቶች ቅዱስ ጊዮርጊስ 10 ጎሎችን ሲያስቆጥር ፤ ጅማ 5 ጎሎችን አስመዝግቧል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ቻርለስ ሉክዋጎ

ሱሌይማን ሀሚድ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሔኖክ አዱኛ

ያብስራ ተስፋዬ – ጋቶች ፓኖም – ከነዓን ማርክነህ

አቤል ያለው – እስማኤል አውሮ-አጎሮ – አማኑኤል ገብረሚካኤል

ጅማ አባ ጅፋር (3-5-2)

አላዛር ማርቆስ

ተስፋዬ መላኩ – የአብስራ ሙሉጌታ – ወንድምአገኝ ማርቆስ

በላይ አባይነህ – ዳዊት እስቲፋኖስ – መስዑድ መሀመድ – ምስጋናው መላኩ – ዱላ ሙላቱ

መሐመድኑር ናስር – ዳዊት ፍቃዱ

ያጋሩ