👉 “ይህ ለእኛ ስድብ ነው ፣ ልክም አይደለም”
👉 “ኢትዮጵያ የመቶ ሚሊየን ህዝብ ሀገር ነች”
👉 “የሚያስመሰግን ስራ ብንሰራ ነው የተሻለ የሚሆነው”
የካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫን አስመልክቶ በሚካሄደው የፓናል ውይይት ላይ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በትውልደ ኢትዮጵያዊ ተጫዋቾች ዙርያ ግልፅ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በርከት ያሉ ግብአቶች በተሰጡበት የኢሊሊ ሆቴል መድረክ ላይ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በብሔራዊ ቡድን ስብስባቸው ላይ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ተጫዋቾች አለማካተታቸው ለምን እንደሆነ ለተነሳባቸው ጥያቄ ተከታዩን ማብራሪያ ስጥተዋል።
“ዴቪድ በሻህ አራት ዓመት ሆኖታል ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር አብሮ ለመስራት ጥያቄ ካቀረበ። ሆኖም ግን ጥያቄውን የሚሰማው እና ያስገባውን ፕሮፖዛል የሚያይለት ጠፍቶ ተስፋ ቆርጦ ትቶት ነበር። እኔ ወደ ቦታው ከመጣው ወዲህ ግን ተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርቦ በስተመጨረሻ ከፌዴሬሽኑ ጋር አብሮ እንዲሰራ እና ከውጭ ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አይቶ እኔ በማቀርብለት ፕሮፋይል መሠረት የሚሆኑ ተጫዋቾችን እንዲያቀርብ ፌዴሬሽኑ እውቅና ሰጥቶታል። ከዚህ ዓመት ከመስከረም አስር ጀምሮ ወደ ስራ ገብቷል። ከመስከረም በኋላ ተንቀሳቅሶ የተወሰኑ ቪዲዮችን ለእኔ ልኮልኛል። ከዚህ በተጨማሪ የዙም ውይይት አድርገናል።
በመጀመርያ ራሴ በኋላ ከአሰልጣኝ አባላቶቼ ጋር ለመመልከት ሞክረናል። አሁን ባለው ሁኔታ መሠረት ያለው ጊዜ አጭር በመሆኑ እርሱ ያለቸውን ተጫዋቾች አምጥተን መስራቱ ከግብአቱ ይልቅ ክፍተቱ ስለሚበዛ ወደፊት ማየት እንችላለን ብለናል። በጀርመን ሦስተኛ ዲቪዚዮን የሚጫወት ኬቨን ሪዶንዶ የሚባል ኖርዌይ ሊግ የሚጫወት ግብጠባቂ ዳንኤልን ተጨማሪ ቪዲዩዎች ላክልኝ ብዬው ነበር። ሌላ ዝርዝር ነገር ውስጥ አልገባም። የእርሱ ፍላጎት የላካቸው ተጫዋቾች በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ እንዲገቡ ነው የፈለገው። እዚህ ጋር ነው የተላለፍነው። የተላኩት ቪዲዮዎች የአራት የአምስት ደቂቃዎች ይሆናሉ። ኢትዮጵያ የመቶ ሚሊየን ህዝብ ሀገር ነች። በዚህች ከሁለት ደቂቃ በማያልፍ ምስል ግብጠባቂ አምጥቼ እንዳሰልፍ ከነበረ ፍላጎቱ ይህ ለእኛ ስድብ ነው ፣ ልክም አይደለም። ተጨማሪ ምስል እንዲልክ ይህም የላከው ራሱ ጥራት የለውም። ባየሁትም የተወሰ ነገር ጥሩ ነገር አይቻለው። ግብጠባቂው ኖርዌይ ነው የሚጫወተው። ተጠባባቂ ነው። ተጫዋች በዚህ መልኩ መምረጥ ተገቢ አይደለም። ይህን ተከትሎ ብሔራዊ ቡድኑ ላይ እኔ ላይ የተሞከረው ነገር ብዙም አስደሳች አይደለም። እርሱም የሚለፋው እንደ ሀገር ነው። ለሀገር ከሆነ ደግሞ ሁላችንም የሚያስመሰግን ስራ ብንሰራ ነው የተሻለ የሚሆነው። በአጠቃላይ በዚህ አጭር ቀን ቢመጡ እንኳን የተጫዋቾቹን ስም ለማወቅ ይቸግራል።” ብለዋል።