የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በሦስቱ አዘጋጅ ከተሞች በተደረጉ ዘጠኝ ጨዋታዎች 15ኛውን ሳምንት አገባዷል።
በዳንኤል መስፍን ፣ ቴዎድሮስ ታከለ እና ጫላ አቤ
ምድብ ሀ
ባቱ ከተማ ከ ሰበታ ከተማ
የዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ ባቱ ከተማን ከሰበታ ከተማ ጋር አገናኝቶ ከጨዋታ ብልጫ ጋር ባቱ ከተማ አሸንፏል።
ገና ከጨዋታው ጅማሬ አንስተው በፈጣን እንቅስቃሴ የሰበታን የግብ ክልል መፈተሽ የጀመሩት ባቱ ከተማዎች የመጀመርያ ጎላቸውን በ20ኛው ደቂቃ የቀድሞ የመከላከያ ተስፈኛ አጥቂ በነበረው ዩሐንስ ደረጄ አማካኝነት አግኝተዋል። ለዚህች ጎል መገኘት የተስፋዬ በቀለ አስተዋፆኦ የጎላ ነበር። በጨዋታው እንቅስቃሴ ውስጥ ያልነበሩት እና ብልጫ የተወሰደባቸው ሰበታ ከተማዎች ከራሳቸው አጨዋወት ይልቅ የባቱ ከተማን እንቅስቃሴ ለማቋረጥ ሲገደዱ ብቻ ተመልክተናል።
በወጣት የተገነባው እና አዝናኝ እግርኳስን የሚጫወተው ባቱ ከተማ በሁለተኛው አጋማሽ 54ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ጎላቸውን አግኝተዋል። ጎሉንም ተስፈኛው ወጣት አጥቂ በሀይሉ ተስፋዬ በፈጣን መልሶ ማጥቃት የተገኘውን ኳስ በጥሩ አጨራረስ ወደ ጎልነት ቀይሮታል። ተጨማሪ ጎሎችን ማስቆጠር የሚችሉበትን ዕድሎች ቢያገኙም ባቱ ከተማዎች ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። ወደ ጨዋታው ፍፃሜ ሰበታ ከተማዎች በኤፍሬም ቀሬ አማካኝነት ለጎል የቀረበ ሙከራ ቢያደርጉም ምንም መፈየድ ሳይችሉ ሽንፈት አስተናግደው ወጥተዋል።
ጅማ አባ ቡና ከ ቤንች ማጂ ቡና
ጅማ አባ ቡናን ከ ቤንች ማጂ ቡና ያገናኘው አዝናኙ ጨዋታ በቤንች ማጂ ቡና አሸናፊነት ተገባዷል። ብዙ ተመልካች በአሰላ አረንጓዴ ስታዲየም በታደመበት በዚህ ተጠባቂ ጨዋታ አባ ቡናዎች የመጀመርያዎችን ሃያ ደቂቃዎች በተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም ግልፅ የጎል ዕድል በመፍጠር እረገድ ጥራት ይጎላቸው የነበሩ በመሆኑ የኋላ የኋላ ለቤንች ማጂ ብናዎች እጅ ለመስጠት ተገደዋል። ቀስ በቀስ ጨዋታውን ተቆጣጥረው ወደ ማጥቃት ሽግሩ የገቡት ቤንች ማጂዎች 42ኛው ደቂቃ እሱባለው ሙልጌታ በጥሩ መንገድ ያሻገረለትን ኤፍሬም ታምሩ ወደ ጎልነት በመቀየር የቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።
በሁለተኛው አጋማሽ በጨዋታው ጅማሬ ለመጀመርያው ጎል መገኘት አስተዋፆ ያደረገው እሱባለው ሙልጌታ በግንባሩ በመግጨት በ48ኛው ደቂቃ ለቤንች ማጂ ቡናዎች ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል። ብልጫ ወስደው መጫወት የቀጠሉት ቤንች ማጂ ቡናዎች መሪነታቸውን ያሰፉበትን ሦስተኛ ጎል በ82ኛው ደቂቃ ለራሱ ሁለተኛ ጎል የሆነውን በእሱባለው ሙልጌታ አማካኝነት አግኝተዋል። ለጎሉ መቆጠር የአንበሉ ጌታሁን ገላዬ ሚና ነበረበት። አስገራ ሚድራማዊ ትዕይንት ያስመለከተን የመጨረሻ አምስት ደቂቃ ጅማ አባቡናዎች በ86 ደቂቃ መርዋን ራያ እና በ90 ደቂቃ ብሩክ ዩሐንስ አማካኝነት ጎል አስቆጥረው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም የዕለቱ ዳኛ የጨዋታውን መጠናቀቅ በማብሰራቸው ተሸንፈው ሊወጡ ችለዋል።
ወልድያ ከ ወሎ ኮምቦልቻ
የአስራ አምስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በወልድያ ከተማና በወሎ ኮንቦልቻ መካከል ተደርጎ በወልድያዎች የበላይነት ተጠናቋል።
በጨዋታ እንቅስቃሴ የተሻሉ የነበሩት ወሎ ኮቦልቻዎች የወሰዱትን ብልጫ በጎል ያልታጀበ በመሆኑ እንደ አጀማመራቸው ሳይሆኑ ቀርተዋል። ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች የተሞላው ወልድያ ከተማ በ19ኛው ደቂቃ ከአስራ ስድስት ከሃምሳ ውጭ የተሰጠውን ቅጣት ምት በግሩም ሆኔታ በቀጥታ በመምታት ሙሉቀን ደሳለኝ የቡድኑን ቀዳሚ ጎል አስገኝቷል።
ወደ መልበሻ ክፍል ለዕረፍት ሊያመሩ በ45ኛው ደቂቃ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት አንቅስቃሴ ከግራ መስመር የተሻገረውን ቢንያም ጥዑመልሳን ከሳጥን ውጭ በድንቅ ሁኔታ መቶ ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። ወሎ ኮምቦልቻዎች ጥሩ እንቅስቃሴያቸው አሁንም በጎል ያልታጀበ በመሆኑ በ75ኛው ደቂቃ በወልድያ በኩል ተቀይሮ የገባው በደረጄ ፍሬው የግንባር ኳስ ሦስተኛ ጎል አስተናግደው ጨዋታው ተጠናቋል።
ምድብ ለ
ቅድሚያውን በወሰደው የምድቡ መርሀግብር ቦዲቲ ከተማ ነቀምት ከተማ ላይ ጣፋጭ ድልን ተጎናፅፎ ጨዋታውን አጠናቋል። 4 ሰዓት ሲል በጀመረው እና የቦዲቲ ከተማዎች ተሻጋሪ ኳሶች ልዩነት በፈጠሩበት የመጀመሪያው አጋማሽ በተቃራኒው ነቀምቶች ኳስን በሚይዙበት ወቅት ከመስመር መነሻቸውን አድርገው በሚጣሉ ኳሶች ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም የኋላ መስመር ላይ ተሰልፈው የሚገኙ ተጫዋቾች በሚሰሩት ስህተት ግብ ተቆጥሮባቸዋል። 17ኛው ደቂቃ ላይ የነቀምቱ ግብ ጠባቂ ኤልያስ ዘአማኑኤል ኳስ ለመያዝ ሲሞክር ያመለጠችውን ኳስ ቢኒያም ታከለ በአግባቡ ተጠቅሞ ጎብ አድርጎታል።
ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ነቀምቶች የተጫዋች ለውጥን አድርገው ክፍተቶቻቸውን ለመድፈን ቢጥሩም የመከላከል ድክመታቸው አብሯቸው ዘልቆ በፈጣን ሽግግር ቦዲቲዎች ተጨማሪ ግብ አክለዋል። 51ኛው ደቂቃ ላይም ለተከላካይ መስመሩ ራስ ምታት ሆኖ የዋለው ቢኒያም ታከለ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል ከመረብ አገናኝቷል። የየመጨረሻውን አስር ደቂቃ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ብርቱ ትግል ውስጥ የገቡት ነቀምቶች 85ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ዱባ በራሱ ላይ በሳጥን ውስጥ ጥፋት ተሰርቶበቶት የተገኘችውን የፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሮ የነረበ ቢሆንም ቡድኑን ከሽንፈት መታደግ ሳይችል በቦዲቲ የ2ለ1 ድል አድራጊነት ተቋጭቷል።
የሁለተኛ ቀን የምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ ከቀትር በኋላ 8 ሰዓት ላይ አምቦ ከተማን ከሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ያገናኘ ነበር። በበርካታ ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች የተዋቀረው ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን በአምቦ ከተማ የፈጣን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት በተጋጋሚ ተፈትነው ሽንፈት አስተናግደው ወጥተዋል። በ25ኛው ደቂቃ ላይ ነብዩ ንጉሱ ያስቆጠራት ብቸኛ ግብ አምቦን ሦስት ነጥብ አስገኝታ ጨዋታው መጠናቀቅ ችሏል።
ይርጋጨፌ ቡና በመሪነት ተርታ የሚዘልቅበትን ዕድል አምክኗል። ንብን ያስተናገደው ቡድኑ ያለ ጎል ጨዋታውን አጠናቋል።
ምድብ ሐ
ኮልፌ ክ/ከ ከ ጅማ አባ ጅፋር
የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እንቅሰቃሴ የታየበት እና በሉክ ፓውል የሚመራው ኮልፌ ክ/ከተማ እና በዋቆ የሚመራው ጅማ አባ ጅፋር ጥሩ የሚባል እና ፈጣን ጨዋታዎችን ሲያስመለክቱን ቆይተዋል። በአንፃሩ ኮልፌ ክ/ከተማዎች ወደ ግብ ቶሎ ቶሎ በመድረስ የጅማ አባ ጅፋር ግብ ጠባቂ የሆነውን ዮሐንስ ቤዛን ሲፈትኑ ተስተውሏል። የመጀመሪያ አጋማሽም በኣቻ ውጤት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽም እንደ መጀመሪያ አጋማሽ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ የታየበትና ብዙም ባይሆን የኮልፌ ክ/ከተማ የበላይነት የታየበት ሲሆን ሆኖም በሁለቱም ክለቦች በኩል ግብ ሳይቆጠር በአቻ ውጤት ተጠናቆ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።
ስልጤ ወራቤ ከ ሶዶ ከተማ
የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታው ከተጀመረ የስልጤ ወራቤ የበላይነት የታየበት ሲሆን በ16ኛው ደቂቃ ሶዶ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት የግብ እድል ለመፍጠር ሲሞክሩ በተሰራባቸው ጥፋት የተገኘውን ቅጣት ምት በአማኑኤል ተስፋዬ አማካኝነት በድንቅ አጨራረስ በማስቆጠር ሶዶ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ስልጤዎች ሙሉ በሙሉ የበላይነት በመውሰድ ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ተስተውሏል። ሆኖም ግን የሶዶ ከተማዎች ግብ ጠባቂ አቡሽ አበበ ጥሩ ጥሩ ኳሶ ሲያድን ተመልክተናል። የመጀመሪያው አጋማሽም በሶዶ ከተማ መሪነት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ሁኔታ በማቲያስ ኤልያስ እና በብሩክ ሰማ የሚመራው የስሌጤወራቤ የፊት መስመር ድንቅ ድንቅ ኳሶችን ወደ ግብ ለመቀየር ቢሞክሩም ወደ ግብ መቀየር ተስኗቸው ምንም ግብ ሳያስቆጥሩ ሽንፈት ማስተናገድ ችለዋል። ሶዶ ከተማም ጣፋጭ ሶስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።
ቡራዩ ከተማ ከ ደሴ ከተማ
የመጀመሪያው አጋማሽ ቡራዩ ከተማዎች ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን በግብ ሙከራም ተሽለው በተደጋጋሚ የደሴ ከተማን ግብ ክልል ሲፈትሹ ተስተውሏል።
ይህንንም ተከትሎ በ13ኛው ደቂቃ ያገኙትን የመዕዘን ምት በአብዲ ሁሴን አማካኝነት ወደ ግብ በመቀየር ቡራዩ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ደሴዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉ ቢሆንም ወደ ግብ መቀየር ተስኗቸው በቡራዩ ከተማ ተከላካይ ሲከሽፍ ተመልክተናል። ይህንንም ተከትሎ የመጀመሪያ አጋማሽ በቡራዩ ከተማ መሪነት ተተናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ደሴ ከተማዎች ኃይልን ቀላቅለው በመጫወት ቡራዩ ከተማ ላይ ጫና ለማሳደር ሲጥሩ የተመለከትን ሲሆን ቡራዩ ከተማዎች ኳስን በመያዝ ጥሩ እግርኳስ ለመጫወት ሲሞክሩ ተመልክተናል ። ጨዋታውም በዚው ሁኔታ በመጠናቀቅ ቡራዩ ከተማን ባለድል አርጎ የሦስት ነጥብ ባለቤት መሆን ችለዋል።