የዋልያዎቹ የሞሮኮ ቆይታ ያለነጥብ ተጠናቋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጊኒ አቻው ሁለተኛ ሽንፈት አስተናግዶ ሦስት ነጥብ ላይ ለመቆም ተገዷል።

\"\"

በዛሬው ጨዋታ አሰልጣኝ ውበቱ ከባለፈው አንፃር ሚሊዮን ሰለሞን ፣ ጋቶች ፓኖም እና ቢንያም በላይን በረመዳን የሱፍ ፣ ታፈሰ ሰለሞን እና ቸርነት ጉግሳ ተክተው ገብተዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ2-0ው ሽንፈት አንፃር ሲታይ የተሻለ እንቅስቃሴ ባሳየበት ጨዋታ ግብ የተቆጠረበት በመጀመርያ ደቂቃዎች ላይ ነበር። በአራተኛው ደቂቃ ላይ ናቢ ኬይታ ከተከላካዮች ጀርባ አፈትልኮ በመውጣት አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

\"\"

ብዙ ሙከራ ባልነበረው ጨዋታ በ24ኛው ደቂቃ ላይ ዋልያዎቹ በሽመልስ በቀለ አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር ፤ አማካዩ አቤል ያለው ያመቻቸለት ኳስ ተጠቅሞ ነበር ወደ ግብ ለማስቆጠር የተቃረበው። ከወርቃማው ዕድል በኋላም በሠላሳ አራተኛው ደቂቃ ቸርነት ጉግሳ እና አቤል ያለው በጥሩ መናበብ ተቀባብለው የፈጠሩት ዕድል ከነዓን ማርክነህ ወደ ግብነት ቀይሮ ዋልያዎቹ አቻ መሆን ችለዋል።

\"\"

ብዙም ሳይቆይ ግን በአርባ ሁለተኛው ደቂቃ ተከላካዮች በፈጠሩት የአቋቋም ስህተት ኢላይሽ ሞሪባ ግብ አስቆጥሮ ጊኒዎች መሪ መሆን ችለዋል።

አቤል ያለው በይሁን እንደሻው ለውጠው ሁለተኛውን አጋማሽ የጀመሩት ዋልያዎቹ ምንም እንኳ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ቢወስዱም በአመዛኙ የኳስ ፍሰቱ በራሳቸው የሜዳ ክፍል ነበር። በዚህ ምክንያትም በርካታ ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም። ሆኖም በረመዳን የሱፍ እና ዑመድ ኡኩሪ አማካኝነት ሙከራ አድርገዋል።

በጨዋታው በብዛት ጥንቃቄ መርጠው በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት የሞከሩት ጊኒዎችም በመሀመድ ባዮ አደገኛ ሙከራ ካደረጉ በኋላ በሰባኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥረው ልዩነቱ ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችለዋል።

\"\"

ዋልያዎቹ ከግቡ መቆጠር በኋላ ሁለት ሙከራዎች ማድረግ ችለው ነበር። በተለይም ከነዓን ማርክነህ ያደረገው ሙከራ ለግብ የቀረበ ነበር። ጨዋታው ከመጠናቀቁ ከጥቂት ሰከንዶች በፊት ግን ጥረታቸው ሰምሮ ኪታካ ጀማ ሱሌማን ሀሚድ ያሻገረለትን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ የግብ ልዩነቱን ወደ አንድ ማጥበብ ችሏል።

ጨዋታው 3-2 በሆነ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ዋልያዎቹ ተከታታይ ሽንፈት አስተናግደው የማጣሪያው ምድብ አራት መጨረሻ ደረጃን ይዘዋል።

\"\"