የዘጠነኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታን በሚከተለው መልኩ ቃኝተነዋል።
በዘጠኝ ሳምንታት የሊጉ ጉዞ በርካታ ጨዋታዎችን አቻ በመውጣት አንደኛ የሆነው አዳማ ከተማ በሁለተኛ ሳምንት ያገኘውን ሦስት ነጥብ ዳግም በማሳካት በደረጃ ሰንጠረዡ እስከ 7ኛ ድረስ ዕድገት አሳይቶ ወደ ዕረፍት ለማምራት ነገ ብርቱ ፉክክር ማድረጉ የማይቀር ነው።
የአዳማ ከተማ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ለከፋ ትችት የሚዳርገው ባይሆንም በውጤት ደረጃ ግን ቀስ በቀስ እየተንሸራተተ ከጨዋታው በፊት የወራጅ ቀጠናው ውስጥ እንዲገኝ አድርጎታል። በአንፃራዊነት የወረደ ስብስብ የሌለው ቡድኑ ጨዋታዎችን በጥሩ ሁኔታ ሲጀምር ቢታይም አዎንታዊ ውጤቶችን በማግኘት የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሱ ሲያደርግ አይታይም። ከዚህም መነሻነት አብዛኛውን ጊዜ ቀድሞ ግብ እያስተናገደ ጥረቱ ለገባበት ግብ ምላሽ ለመስጠት እየሆነ ይታያል። ባሳለፍነው ሳምንትም ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ሲጫወት በተመሳሳይ ቀድሞ ግብ ተቆጥሮበት ባለቀ ሰዓት ባስቆጠረው ጎል ነው አንድ ነጥብ ይዞ የወጣው። ይህ ጉዳይ የአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝን ስብስብ እጅግ እየጎዳ እንደሆነ የታየ ሲሆን የጨዋታውን ክፍለ ጊዜም በዕኩል የትኩረት ማከናወን እንዳለበት መመስከር ይቻላል። በነገውም ጨዋታ ይህ ጉዳይ ተስተካክሎ መቅረብ ካልቻለ ከተጋጣሚው ጥንካሬ አንፃር ውጤት እንዳይከዳው ያሰጋዋል።
ሁለት ተከታታይ ድሎችን ካስመዘገበ በኋላ ከሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ ጋር ያለግብ የተለያየው ባህር ዳር ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሆኖ ወደ ዕረፍት ለማምራት ያልማል። በፍጥነት ወደ ድል አድራጊነት መመለስ በራሱ ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ መሆኑን የሚየመላክት መሆኑ የነገው ጨዋታ ለቡድኑ ወሳኝ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ተጠባቂ በነበረው የፋሲል ከነማው ጨዋታ ላይ ባህር ዳር ለተጋጣሚው አጨዋወት ምላሽ መስጠትን መርጦ ነበር። ለዛም ይመስላል የአደራደር ለውጥ በማድረግ ጭምር የፋሲልን የመስመር ጥቃት በማክሰም በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወደ ግብ ሊደርስ ይሞክር የነበረው። ነገ ግን የአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ቡድኑ ከዚህ የተለየ መልክ ይዞ እንደሚቀርብ ይጠበቃል። እርግጥ ነው ቡድኑ ለመልሶ ማጥቃት የቀረበ የጨዋታ ዕቅድ ይዞ ሲገባ ይበልጥ አደገኛ ሆኖ ይታያል። ያም ሆኖ የኳስ ቁጥጥርን ማዕከል ያደረገ አጨዋወት ዋናው መገለጫው ነው ቢባል መሳሳት አይሆንም። አዳማ ከተማ ውጤቱን አጥብቆ መፈለጉ ከሜዳው ከፍ ብሎ በተመሳሳይ የኳስ ቁጥጥሩን በእጁ ለማድረግ መንቀሳቀሱ ሲታሰብ ግን የመከላከል ሽግግሩ ጊዜውን የጠበቀ ካልሆነ ባህር ዳሮች ፈጣን አጥቂዎቻቸውን ያማከሉ ድንገተኛ ጥቃቶችን ሲሰነዝሩ ልንመለከት እንችላለን።
በጨዋታው አዳማ ከተማ ያለጉዳት እና ቅጣት ዜና ወደ ሜዳ እንደሚገባ ሲጠበቅ በባህር ዳር በኩል ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ኦሴይ ማዉሊ በጉዳት አህመድ ረሺድ ደግሞ በቅጣት አይሰለፉም።
ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ለመምራት ተመድበዋል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን ከተገናኙባቸው አራት ጨዋታዎች ሦስቱ በባህር ዳር ከተማ አሸናፊነት ሲጠናቀቁ በአንዱ ያለግብ ተለያይተዋል። በግንኙነታቸው አዳማ ከተማ እስካሁን ግብ ያልቀናው ሲሆን ባህር ዳር ከተማ ስድስት ግቦች አሉት።
ግምታዊ አሰላለፍ
አዳማ ከተማ (4-3-3)
ጀማል ጣሰው
ሚሊዮን ሰለሞን – አሚኑ ነስሩ – ቶማስ ስምረቱ – ደስታ ዮሐንስ
አማኑኤል ጎበና – ዮሴፍ ዮሐንስ – ዮናስ ገረመው
አቡበከር ወንድሙ – ዳዋ ሆቴሳ – አሜ መሐመድ
ባህር ዳር ከተማ (4-4-2 ዳይመንድ)
ፋሲል ገብረሚካኤል
መሳይ አገኘሁ – ፈቱዲን ጀማል – መናፍ ዐወል – ግርማ ዲሳሳ
በረከት ጥጋቡ
አብዱልከሪም ንኪማ – አለልኝ አዘነ
ፍፁም ዓለሙ
ዓሊ ሱሌይማን – ተመስገን ደረሰ