የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከአስረኛ ሳምንት በኋላ አዳማ ይደረጋል?

የኢትዮጵያ ከፍተኛ የሊግ እርከን የሆነው ቤትኪንግ  የኢትዮጵያፕሪምየር ሊግ ለአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከተቋረጠ በኋላ በተያዘለት መርሐ-ግብር መሠረት በአዳማ ከተማ ይቀጥላል ? የሚለውን የብዙሃኑን ጥያቄ ተንተርሰን ተከታዩን ጥንቅር አዘጋጅተናል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የበላይነት ከጥቅምት ሰባት ጀምሮ በሀዋሳ ከተማ እየተደረገ የሚገኘው የ2014 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዛሬው ዕለት የዘጠነኛ ሳምንት መርሐ-ግብሮቹን ያገባድዳል። ለ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት እና ውድድር ለቀናት (ብሔራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫው እንደሚያመጣው ስኬት) እንደሚቋረጥ ይታወቃል። ከሀዋሳ በመቀጠል ውድድሩን ከአስረኛ ሳምንት ጀምሮ እንድታስተናግድ ተመርጣ የነበረችው አዳማም ሽር ጉዷን የቀጠለች ቢሆንም አሁንም ግን ሊጉ ሀዋሳ ይቀጥላል ፣ ድሬዳዋ አልያም ጅማ ሊሄድ ይችላል የሚሉ ሀሳቦች ከብዙሃኑ ዘንድ እየተነሳ ይገኛል። ይህ ሀሳብ እየተሰማ ቢሆንም የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ እና ሥራ አስኪያጁ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ከቀናት በፊት ወደ አዳማ አቅንተው አሁናዊውን የአዳማ ከተማ ዝግጅት ቃኝተው ተመልሰዋል።

አዳማ ከተማም ከዚህ በፊት እንደ ግብዐት የቀረቡለትን የመጫወቻ እና የልምምድ ሜዳዎችን ምቹነት ለማሳደግ ሥራ ሲሰራ እንደነበር ያወቅን ሲሆን የሊጉ የውድድር ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ እና የምስል መብቱ ባለቤት ዲ ኤስ ቲቪ በጋራ ባወጡት መርሐ-ግብር መሰረት የማታ ጨዋታዎችን ለማከናወን የሚያደርግ የስታዲየም ፓውዛ ጉዳይ ደግሞ ወሳኙ ነገር ነበር። የአዳማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ለማታ ስርጭት የሚሆን መብራት ባለመኖሩ በቶሎ የፓውዛ ገጠማ ሥራዎች እንዲሰሩ የከተማ አስተዳደሩ ከዩኒቨርስቲው ጋር በጋራ በመሆን ጨረታ አውጥተው አሸናፊው እንደተለየ አውቀናል። የጨረታ አሸናፊው አካልም በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት በሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ፓውዛውን ገጥሞ እንደሚጨርስም ተመላክቷል።

ከዚህ ውጪ ከላይ እንደተጠቀሰው የመለማመጃ ጉዳይ ላይም ከተማ አስተዳደሩ ስራዎችን ሲሰራ እንደቆየ እና በከተማው ውስጥ ከሚገኙት መለማመጃ ሜዳዎች በተጨማሪ በዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ ውስጥም ሌላ አዲስ የመለማመጃ ሜዳ መዘጋጀቱን ተነግሮናል። በዚህ ረገድ ከተማው ውስጥ ከሚገኙት ሜዳዎች በተጨማሪም በቅርብ ርቀት ከሚገኙ አጎራባች ከተሞችም አማራጮች ሊቀመጡ እንደሚችሉ ተብራርቷል።

የአዳማ ከተማ ሥራ-አስኪያጅ አቶ አንበስ መገርሳ ለሶከር ኢትዮጵያ በገለፁት መሰረት ደግሞ የከተማው ከንቲባን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች እና የዩኒቨርስቲው የአስተዳደር ሰዎች በተገኙበት ከትናንት በስትያ ስብሰባ ተደርጓል። የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ፣ የአዳማ ከተማ የብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ፣ ምክትል ከንቲባው አቶ መሐመድ፣ የከተማው ሥራ-አስኪያጅ አቶ ዘርፉ፣ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ለሚ እና የአዳማ ከተማ ክለብ ፕሬዝዳንት እና ሥራ-አስኪያጅ እንዲሁም የአክሲዮን ማኅበሩ አባል በተገኙበት ስብሰባ ላይም ምክትል ዲን የሆኑን ዶ/ር ሀብታሙ እስካሁን የተሰሩ ሥራዎችን በተመለከተ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን ቀሪ ሥራዎችም ባሉት ቀናት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና ከተማው ውድድሩን ለማስተናገድ ቁርጠኛ እንደሆነ ሀሳብ ተንፀባርቋል።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ክለቦች ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ ውድድሩ እዚሁ ሀዋሳ እንዲቀጥል ሀሳብ እያቀረቡ እንደሆነ ሰምተናል። በተያያዘ ዜናም ከሦስት ቀናት በፊት የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ወደ ባህር ዳር ተጉዘው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደተወያዩ እና ባህር ዳርም ቀድሞ ከተያዘለት ፕሮግራም አስቀድሞ ውድድሩን ለማስተናገድ ፍላጎት እንዳለ እንደተገለፀ አውቀናል። በተለይ ዋናው የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ለማታ ጨዋታዎች የሚሆን ፓውዛ ስለሌለው ደግሞ ጨዋታዎች ወደ ቀን እንዲመጡ አልያም የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ስታዲየም (ፔዳ ካምፓስ) እንደ አማራጭ እንዲወሰድ ሀሳብ እንዳቀረቡም ሰምተናል።

የአክሲዮን ማኅበሩ ሥራ-አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ በበኩላቸው በቅርቡ ወደ አዳማ ሄደው ያለውን አሁናዊ ዝግጅት እንደተመለከቱ አመላክተው የዋናው መጫወቻ ሜዳ እና የስታዲየም ፓውዛ ጉዳይ ላይ ብቻ ክልሉ አፅዕኖት ሰጥቶ እንዲሰራ አቅጣጫ እንደተመለከተ ነግረውናል። ያለ ምንም ጥያቄ የፓውዛው ጉዳይ በቶሎ እንዲፈታ ከመነገሩ በተጨማሪ ደግሞ የእግርኳስ መጫወቻው ሜዳ አሁን ካለበት በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሽሎ መቅረብ እንዳለበት እና ከዚህም በኋላ ተጫዋቾች፣ አሠልጣኞች እና የስፖርት ቤተሰቡ ሜዳውን በተመለከተ ትችት እንዳያነሳ መሰራት እንዳለበት ገልፀው እንደመጡ አስረድተውናል። ሁለቱ አበይት ስራዎችም እስከ ታኅሣሥ 30 ድረስ ተገባደው የአክሲዮን ማኅበሩ ባለሙያዎች ወደ ስፍራው ተጉዘው የመጨረሻ ምልከታ እንደሚያደርጉ እና የመጨረሻ ውሳኔውም በዛው እንደሚሰጥ ጠቁመውልናል።

አዳማ ከተማ ውድድሩን ለማስተናገድ እየሄደችበት ያለችው ርቀት ጥሩ ቢሆንም ታኅሣሥ 30 የተቀመጡት ነጥቦች ታይተው መሻሻሎች ከሌሉ (የመጫወቻ ሜዳው ምቹነት እና የፓውዛው ለቀረፃ አመቺነት) ውድድሩ በቀጥታ ወደ ድሬዳዋ እንደሚያቀናም ታውቋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ እስካሁኑ ሰዓት ድረስ ውድድሩ ሀዋሳ ይቀጥላል የሚለው ጉዳይ በአክሲዮን ማኅበሩ ሀሳብ ውስጥ እንደሌለም አውቀናል።