ሪፖርት | አዳማ ከተማ ከአምስት ተከታታይ አቻዎች በኋላ ድል አድርጓል

የዳዋ ሆቴሳ ፍፁም ቅጣት ምት ጎል አዳማ ከተማ በባህር ዳር ላይ የሊጉን የመጀመሪያ የእርስ በእርስ ድል እንዲያስመዘግብ አድርጋለች።

አዳማ ከተማ አርባምንጭን ሲገጥም ከተጠቀመበት አሰላለፍ ውስጥ አሚን ነስሩ ፣ ኤልያስ ማሞ ፣ አብዲሳ ጀማል እና ጂብሪል አህመድን በማሳረፍ ጀሚል ያዕቆብ ፣ ዮናስ ገረመው ፣ አቡበከር ወንድሙ እና ዳዋ ሆቴሳን ወደ ሜዳ አስገብቷል። በባህር ዳር በኩልም ሦስት ለውጦች ሲኖሩ ቅጣት እና ጉዳት የገጠማቸው አህመድ ረሺድ እና ኦሴይ ማውሊ እንዲሁም አለልኝ አዘነ በመሳይ አገኘሁ ፣ ፉዓድ ፈረጃ እና ሣለአምላክ ተገኘ ተተክተዋል።

አዳማ ከተማዎች ተጋጣሚያቸው ኳስ መስርቶ እንዳይወጣ በማድረግ ጫን ብለው በጀመሩት ጨዋታ የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። በዚህም 2ኛው ደቂቃ ላይ መናፍ ዐወል ኳስ አቀብላለሁ ብሎ በመሳሳቱ አዳማዎች አግኝተውት በዮሴፍ አማካኝነት ሞክረው ነበር። የባህር ዳር ወደ ፊት በቶሎ ለመድረስ የሚደረገውን ጥረት ማቋረጥ ያልከበዳቸው አዳማዎች ወደ ቀኝ ባደላ ጥቃት ወደ ሳጥን ለመድረስ ሲሞክሩ ተስተውለዋል። ሆኖም የመጨረሻ ቅብብላቸው ደካማ ሆኖ ከአደገኛ ሙከራ አርቋቸው ቆይቷል። ቡድኑ ቀዳሚውን ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ 26ኛው ደቂቃ ላይ ሚሊዮን ሠለሞን የዮናስ ገረመውን ወደ ቀኝ ያደላ ቅጣት ምት በግንባሩ ሲገጭ ያደረጉ ቢሆንም ፋሲል ገብረሚካኤል ለማዳን ብዙም አልተቸገረም።

ከወሃ ዕረፍት መልስ የባህር ዳሮች እንቅስቃሴ አገግሟል። ቅብብሎቻቸው ከሜዳቸው በመውጣት ወደ አዳማ ሳጥን ፈጠን ባሉ ጥቃቶች ደርሰዋል። ሆኖም 36ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ኒኪማ ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ ወደ ላይ ከመነሳቱ በቀር ሌላ አደገኛ ሙከራ አላደረጉም። ይልቁኑም 45ኛው ደቂቃ ላይ አዳማዎች ከመሀል በተሰነጠቀ ኳስ በግራ በኩል የሰነዘሩት መልሶ ማጥቃት አደጋ ሊፈጥር ቢቃረብም የአሜ መሀመድ ሙከራ አቅም ሳይኖረው ቀርቷል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ቡድኖቹ የተመጣጠነ እንቅስቃሴ ማሳየት ጀምረዋል። ጨዋታው ጥሩ የማጥቃት ምልልስ እየታየበት ቢቆይም ሙከራ ግን ርቆት ነበር። 68ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ ቀዳሚው ሲሆን በፋሲል ከተመለሰ በኋላ አዳማዎች መልሰው ለማስቆጠር ባደረጉት ጥረት ውስጥ ተመስገን ደረሰ በቢኒያም አይተን ላይ ጥፋት በመስራቱ አዳማዎች ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። ዳዋ ሆቴሳም 71ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አድርጎታል። ከግቡ በኋላ ጨዋታው ለውሃ ዕረፍት ሲቋረጥ ግርማ የፍፁም ቅጣት ምቱን ውሳኔ በመቃወም ግርማ ዲሳሳ ከዕለቱ አርቢትር ጋር በፈጠረው የቃላት ልውውጥ የቀጥታ ቀይ ካርድ ሰለባ ሆኗል።

ጨዋታው ወደ እንቅስቃሴ ሲመለስ ባህር ዳሮች በፍፁም ዓለሙ የርቀት ሙከራ እንዲሁም ዳዋ ሆቴሳ ከማዕዘን በመጣ የግንባር ሙከራ ወደ ግብ ደርሰዋል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች እየተመሩ የነበሩት ባህር ዳሮች ተጫዋች ቢጎድልባቸውም በጨዋታ እና በቆሙ ኳሶች የግብ ዕድል ለመፍጠር ጥረዋል። ሆኖም ጠንቀቅ ብለው ጥቃቶችን በመከላከል የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር የጣሩት አዳማዎች ወደ ፊት ሄደው ተጨማሪ ግብ ባያሳኩም ውጤታቸውን አስጠብቀው ወጥተዋል።

በውጤቱ ባህር ዳር ከተማ ወደ ሁለተኛ ደረጃ መመለስ የሚችልበትን ዕድል ሲያመክን ነጥቡን 12 ያደረሰው አዳማ ከተማ ከ14 ወደ 7ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።