ከፍተኛ ሊግ | የ16ኛ ሳምንት የዛሬ ጨዋታዎች ውሎ

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ በተደረጉ 10 ጨዋታዎች በምድብ \’ሀ\’ ድል የቀናቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ቤንች ማጂ ቡና ፉክክር ሲቀጥል በምድብ \’ለ\’ አዲስ አበባ ከተማ በምድብ \’ሐ\’ ደግሞ ገላን ከተማ ወደ መሪነት መምጣት የሚችሉበትን ዕድል አባክነዋል።

በዳንኤል መስፍን ፣ ቴዎድሮስ ታከለ እና ጫላ አቤ

የጠዋት ጨዋታዎች

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ዱራሜ ከተማ – ምድብ ሀ

የምድቡን መሪ የሆነውን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዱራሜ ያገናኘው ጨዋታ በንግድ ባንክ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ገና በጨዋታው የመጀመርያ ደቂቃ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ኳስ እዩብ ማሙሽ አምልጦ በመግባት ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት በቀረው ሙከራ ጎል ለማግኘት ፍለጋ የጀመሩት ንግድ ባንኮች ብዙም ሳይቆዩ የመጀመርያ ጎላቸውን አግኝተዋል። በ4ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተጣለውን ልዑልሰገድ አስፋው ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። ንግድ ባንክ ምንም እንኳን ፈጥነው ወደ እንቅስቃሴ በመግባት ጎል ያስቆጥሩ እንጂ ስኬታማ ባልሆኑ ቅብብሎች የተነሳ ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ተቸግረው ቆይተዋለወ። ዱራሜዎች አጀማመራቸው ቀዝቀዝ ያለ ቢመስልም በሂድን ብልጫ ወስደው አደጋ ለመፍጠር ጥረት ማድረግ ቢጀምሩም ኳስና መረብን ማገናኘት አልቻሉም።

\"\"

በሁለተኛው አጋማሽም ከንግድ ባንክ በተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት ድራሜ ከተማዎች ከቅጣት ምት በግራ እግሩ ካፎ ካስትሮ መቶት የግቡ አግዳሚ ከመለሰባቸው በኋላ በ54ኛው ደቂቃ በኪሩቤል ካሱ አማካኝነት የአቻነት ጎላቸውን ማግኘት ችለዋል። የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመቀልበስ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ክፍተታቸውን በመቅረፍ የተንቀሳቀሱት ንግድ ባንኮች በ79ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በገባው በወንድማገኝ ኬራ ድንቅ አጨራረስ የማሸነፊያ ሁለተኛ ጎላቸውን አግኝተው ጨዋታውን በማሸነፍ የመድቡ መሪ መሆናቸውን አረጋግጠው ወጥተዋል።

ከፋ ቡና ከ ይርጋጨፌ ቡና – ምድብ ለ

ይርጋጨፌ ቡና ወደ መሪዎቹ ተርታ ከፍ የሚልበትን ውጤት ከዕረፍት መልስ በተቆጠሩበት ጎሎች ተነጥቆ በአቻ ውጤት ጨዋታውን ፈፅሟል።

\"\"

ካፋ ቡናዎች በይርጋጨፌ ቡናው ተጫዋች መልኤል ብርሀኑ ላይ የተገቢነት ክስን ካስያዙ በኋላ ጨዋታው ጀምሯል። ኳስን በአግባቡ በመቆጣጠር ገና በጊዜ በተሻለ መንቀሳቀስ የጀመሩት ይርጋጨፌ ቡናዎች 10ኛው ደቂቃ ላይ መነሻዋን ከቅጣት ምት አድርጋ በካፋ ተከላካዮች ስህተት ተጨራርፋ የመጣችን ኳስ ስዩም ደስታ በቀላሉ ከመረብ አገናኝቶ የአሰልጣኝ ደረጀ በላይን ቡድን መሪ አድርጓል። የተጋጣሚያቸውን ስህተት በአግባቡ ለመጠቀም በድግግሞሽ በማጥቃቱ የተዋጣላቸው ይርጋጨፌዎች ሁለተኛ ጎል አግኝተዋል። 32ኛው ደቂቃ ላይ እሸቱ መና በስዩም ደስታ ላይ በሳጥን ውስጥ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ስዩም ለቡድኑ እና ለራሱ ሁለተኛ ጎል አድርጎታል።

በመጀመሪያው አጋማሽ በተጋጣሚያቸው ለመበለጥ የተገደዱት ካፋ ቡናዎች በሁለተኛው አጋማሽ ፈጣን የተጫዋቾች ቅያሪዎችን በማድረግ በይበልጥ ወደ ጨዋታ ቅኝት ውስጥ ገብተዋል። በፈጠሩት ለውጥም 64ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ይስሀቅ ወደ ጎል ኳስን ሲመታ በተከላካዮች በእጅ በመነካቷ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አስጨናቂ ሉቃስ አስቆጥሮ ጨዋታው ወደ 2ለ1 ተሸጋግሯል። በመስመር በሚነሱ ኳሶች ተጨማሪ ግብ ለማዋሀድ የጣሩት ካፋ ቡናዎች 71ኛ ደቂቃ በተመስገን አማረ የሳጥን ውጪ አስደናቂ ጎል ከመመራት ተነስተው ወደ አቻነት ተሸጋግረዋል። ጨዋታው ሊገባደድ አስር ደቂቃዎች ሲቀሩ ይርጋጨፌ ቡናዎች ተቀይሮ በገባው ኤፍሬም ቶማስ አማካኝነት ሁለት ያለቀላቸውን ዕድል ቢያገኙም ወደ ጎልነት ባለመቀየራቸው ጨዋታው 2ለ2 ተጠናቋል።

ኦሜድላ ከ ገላን ከተማ – ምድብ ሐ

የጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ በገላን ከተማ ጥሩ እንቅስቃሴ እና በአስገራሚ የኳስ ፍሰት የታጀበ ነበር። ሆኖም አጋማሹ ምንም ግብ ሳይቆጠር የተጠናቀቀ ሲሆን በእነ በየነ ባንጃው የሚመራው የገላን የመሀል ሜዳ ክፍል አስደናቂ ኳሶችን ወደ ፊት በማሻገር ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድል ሲፈጥሩ ተስተውሏል። በዚህም አጨዋወት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ገላን ከተማዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ ጫና ለመፍጠር ሲጥሩ የተመለከትን ሲሆን በኦሜድላ በኩልም የሚያገኙትን ኳሶች በመልሶ ማጥቃት በተደጋጋሚ የገላን ከተማን የኋላ መስመር ሲፈትሹ ቆይተዋል። ሆኖም ግን ያገኙትን የግብ ዕድል በቀላሉ ሲያባክኑ ተስተውሏል። በጨዋታውም ምንም ግብ ሳይቆጠር ተጠናቆ ሁለቱ ቡድኖች ነጥብ ተጋርተው መውጣት ችለዋል። ውጤቱንም ተከትሎ ገላን ከተማ የምድቡ መሪ መሆን የሚችልበትን ዕድል ሳይጠቀም ቀርቷል።

የ05:00 ጨዋታ

ባንች ማጂ ቡና ከ ሰንዳፋ በኬ – ምድብ ሀ

ከምድቡ መሪ በቅርብ ርቀት የሚገኘው ቤንች ማጂ ቡና እና በሰንዳፋ በኬ መካከል የተካሄደው ጨዋታ ቤንች ማጂ ቡናን አሸናፊ አድርጓል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ የጎላ የጎል ሙከራ ባይደረግበትም በአንፃራዊነት በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ በመሆን የተቀመጠው ቤንች ማጂ ቡና ኳሱን በተሻለ በማንሸራሸር ክፍተቶችን ለመፍጠር ሲሞክር ሰንዳፋ በኬ በበኩሉ በጥብቅ የመከላከል አጨዋወት በመንቀሳቀስ የሚያገኛቸውን ኳሶች ለአጥቂያቸው መሳይ ሰለሞን አንደኛ እና ሁለተኛ ኳስ በማሸነፍ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢያስቡም ስኬታማ አልነበሩም።

\"\"

እጅግ የተደራጀ ስብስብ ያላቸው ቤንች ማጂ ቡናዎች ጎል ለማስቆጠር ረጅም ደቂቃዎች ይውሰድባቸው እንጂ በትዕግስት ክፍተቶችን ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው የመጀመርያ ጎላቸውን በ62ኛው ደቂቃ በወጣቱ ፈጣን አጥቂ ሀሰን ሁሴን አማካኝነት አግኝተዋል። ከዚህች ጎል መቆጠር በኋላ ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ማጥቃታቸውን የቀጠሉት ቤንቺ ማጂ ቡናዎች በተከታታይ ጨዋታዎች ለቡድኑ ጎል እያስቆጠረ በሚገኘው እሱባለው ሙሉጌታ በ73ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ጎል አስቆጥረው ጨዋታውን ሁለት ለዜሮ አሸናፊነት አጠናቀዋል።

የ08:00 ጨዋታዎች

ጋሞ ጨንቻ ከ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ – ምድብ ሀ

የዕለቱ ሦስተኛ ጨዋታ የነበረው የጋሞ ጨንቻ እና የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ ጨዋታ በጋሞዎችን አሸናፊ አድርጓል።

በመጀመርያው አጋማሽ ተመጣጣኝ ፉክክር ባስመለከተን በዚህ ጨዋታ አቃቂ ቃሊቲዎች በመስሩፍ መሐመድ አማካኝነት በግንባር በተመታ ኳስ እጅግ ለጎል የቀረበ ሙከራ ቢያደርጉም በጥሩ ሁኔታ የጋሞዎች ግብ ጠባቂ ንጉሴ ሙሉጌታ አድኖታል። ከዚህች የጨዋታውን የመጀመርያ ሙከራ ከተመለከትን በኋላ እምብዛም ተጨማሪ የጎል ሙከራ በሁለቱም ቡድኖች ባንመለከትም ለእረፍት ወደ መልባሻ በሚያመሩበት 45ኛው ደቂቃ ላይ ጋሞ ጨንቻዎች ማቲዎስ ማደልቾ አማካኝነት ጎል አስቆጥረዋል።

\"\"

በሁለተኛው አጋማሽ ጋሞ ጨንቻዎች ጨዋታውን በሚፈልጉት መንገድ በመቆጣጠር የግብ ክልላቸውን በንቃት በመጠበቅ ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ያደረጉት እንቅስቃሴ ፍሬ አፍርቶ በመስመር አጥቂው በፍቃዱ ሕዝቄል የግል ጥረት ታክሎበት ሁለተኛ ጎላቸውን በ71ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። በቀሪ ደቂቃዎችም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው በጋሞ ጨንቻ አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።

አዲስ አበባ ከተማ ከ ጉለሌ ክ/ከ – ምድብ ለ

ከቀትር መልስ ሁለቱን የመዲናይቱን ክለቦች አዲስ አበባ ከተማን ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ያገናኘው ቀዝቃዛው ጨዋታ ያለ ጎል ፍፃሜውን አግኝቷል።

\"\"

ጨዋታው በሁለቱ አጋማሾች ተመሳሳይ የጨዋታ ቅርፅ የነበረ ነበር። አዲስ አበባ ከተማ ወጥነት ያልተላበሰን ተደጋጋሚ ስህተቶችን አዘውትረው ሲጫወቱ ጉለሌዎች በበኩላቸው የቅብብል አጨዋወትን ሲጫወቱ ከማስተዋል በዘለለ የጠሩ ግልፅ አጋጣሚዎችን ለመመልከት አልታደልንበትም። በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ከቅጣት ምት ሮቤል ግርማ ወደ ጎል መትቶ ግብ ጠባቂው ኩክ ኪዊዝ ሲተፋ ኤርሚያስ ኃይሉ ለአዲስ አበባ ግብ አስቆጥሮ ከጨዋታ ውጪ የተባለችዋ ምናልባትም በጨዋታው ኢላማውን የጠበቀች ሙከራ ነበረች ማለት ይቻላል።

ይሁን እንጂ በሁለተኛው አጋማሽ ጉለሌዎች ልዩነት ለመፍጠር በተደራጀ የማጥቃት መንገድን ይዘው ወደ ሜዳ መግባት ቢችሉም ጨዋታው ከነበረው አሰልቺ ይዘት አንፃር ግብ ሳያስመለክተን 0-0 ሊጠናቀቅ ችሏል።

ዳሞት ከተማ ከ ስልጤ ወራቤ – ምድብ ሐ

የመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ የተመለከትን ሲሆን በኳስ ቁጥጥሩ ስልጤ ወራቤዎች ተሽለው የተገኙበት እና በማጥቃቱ ረገድ ከመስመር በሚነሱ ኳሶች የግብ ዕድል ለመፍጠር የሞከሩበት ነበር። በዚህም አጨዋወት ብዛት ያላቸው የግብ ዕድሎችን የፈጠሩ ቢሆንም መጠቀም ተስኗቸው ሲያባክኑ ታይቷል። ዳሞት ከተማም ጥንቃቄን ያበዛ አጨዋወት በመከተል ግቡን ሳያስደፍር አጋማሹ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽ ዳሞት ከተማዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ ተሽለው የተመለሱ ሲሆን በአንፃሩ ስልጤ ወራቤ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ አጨዋወቱን ሳይቀይር በመግባቱ ዳሞት ከተማዎች ወደ ኋላ በማፈግፈግ ስልጤ ወራቤዎች ትተው የሚመጡትን ክፍተት በመልሶ ማጥቃት ለመጠቀም ጥረዋል። ይህንንም ተከትሎ በ74ኛ ደቂቃ ላይ ዳሞት ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን ዕድል ወደ ማዕዘን ምት በመቀየሩ የተገኘችውን የመዕዘን ምት በሱልጣን አብዩ አማካኝነት ወደ ግብነት በመቀየር ዳሞት ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ስልጤ ወራቤዎች ከሽንፈት ለማምለጥ ባደረጉት ጥረት በ85ኛው ደቂቃ በፈጠሩት ጫና የዳሞት ከተማው ተጫዋች ትንሳኤ ያበጌታ በራሱ ግብ ላይ በማስቆጠር ስልጤዎችን ከሽንፈት መታደግ ችለዋል። በዚህም መሠረት ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቆ ሁለቱም ክለቦች ነጥብ መጋራት ችለዋል።

\"\"

የ10:00 ጨዋታዎች

ሰበታ ከተማ ከ ጅማ አባ ቡና – ምድብ ሀ

ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ወርደው በከፍተኛ ሊግ የተገናኙት ሰበታ ከተማ እና በጅማ አባ ቡና ያደረጉት ጨዋታ አባ ቡናዎችን አሸናፊ አድርጓል።

ጨዋታው አጀማመሩ ቀዝቀዝ ቢልም ቀስ እያለ እየተጋጋለ በመምጣት በተለይ የአባ ቡናዎችን የኳስ ቁጥጥር የበላይነት አስመልክቶናል። በዚህም ሂደት በ27ኛው የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ባለ ብዙ ልምዱ አጥቂ ቡዛየሁ እንደሻው ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ያልቻሉት ሰበታ ከተማዎች በመጀመርያው አጋማሽ ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

\"\"

በሁለተኛው አጋማሽ በአንፃራዊነት ተሽለው የቀረቡት ሰበታዎች በተለይ ተቀይሮ የገባው ዮናስ አቡሌ የቡድኑን የማጥቃት አቅም በመጨመር ከሳጥን ውጭ የተገኘውን ቅጣት ምት በቀጥታ መቶት ግብ ጠባቂው እንደምንም ያወጣበት ለሰበታ በጨዋታው የተገኘ የመጀመርያው ሙከራ ሆኗል። ብዙም ሳይቆይ ሰበታዎች ዮናስ አቡሌ በጥሩ መንገድ ያቀበለውን አጥቂው ኤፍሬም ቀሬ ኳሱን ገፍቶ በመግባት መሬት ለመሬት የመታው ኳስ ወደ ጎልነት ተቀየረ ሲባል የአባ ቡናው ግዙፉ የግብ ዘብ ሌሊሳ ታዬ አድኖበታል። በመልሶ ማጥቃት ወደ ፊት የሄዱት አባ ቡናዎች አስራ ስድስት ከሃምሳ ውስጥ እስጢፋኖስ ተማም ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ቡዛየሁ እንደሻው በድጋሚ በመምታት ሁለተኛ ጎል 73ኛው ደቂቃ አስቆጥሮ ጨዋታው በአባ ቡናዎች አሸናፊነት ተገባዷል።

ቦዲቲ ከተማ ከ ንብ – ምድብ ለ

የሳምንቱ የማሳረጊያ ጨዋታ የነበረው የንብ እና ቦዲቲ ከተማ ጨዋታ ጥሩ ፉክክርን እና ተመጣጣኝ እንቅስቃሴን ፣ በሒደት ግን የንብን በሳል የመስመር ላይ አጨዋወትን ያስመለከተን ጨዋታ ነበር። ታምራት ስላስ በፈጣን የአንድ ሁለት ቅብብል ጨዋታው በተጀመረ በአራተኛው ደቂቃ ላይ ከግብ ጋር ተገናኝቶ ንብን መሪ አደረገ ተብሎ ሲጠበቅ የግቡ ቋሚ ብረት የመለሰባት ፈጣኗ የጨዋታው ሙከራ ሆናለች። ከእንቅስቃሴ ውጪ የጎል ዕድሎችን ያላስመለከተን ቀዳሚው አርባ አምስት ተጠናቆ ጨዋታው በሁለተኛ አጋማሽ ሲቀጥል ቦዲቲ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት አጥቂው ቢኒያም ታከለን የትኩረት ማዕከል በማድረግ ሲጫወቱ ብንመለከትም በአንድ ሁለት የጨዋታ ፍሰት ወደ ቀኝ መስመር አዘንብለው ሲጫወቱ የነበሩት ንቦች ግን ያገኙትን ዕድሎች በአግባቡ ተጠቅመው ጎል ማስቆጠር ቸለዋል።

\"\"

62ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት አምበሉ ንስሀ ታፈሰ ሲያሻማ ተጨራርፋ የደረሰችውን ኳስ ኤርሚያስ ደጀኔ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ግሩም ጎል አድርጎታል። የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎች በይበልጥ የቦዲቲ የግብ ክልል ማነፍነፋቸውን የቀጠሉት ንቦች 86ኛ ደቂቃ ላይ በጨዋታው ድንቅ የነበረው ታምራት ስላስ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ከቀኝ መስመር በኩል መሬት ለመሬት ያሳለፈለትን ኳስ ናትናኤል ሰለሞን ከቦዲቲ ተከላካዮች አምልጦ በመውጣት ሁለተኛ ጎል በማከል ጨዋታው 2ለ0 የንብ ድል አድራጊነት ተደምድሟል።

ጅማ አባ ጅፋር ከ ደሴ ከተማ – ምድብ ሐ

የመጀመሪያው አጋማሽ ጅማ አባ ጅፋሮች ኳስን መሰረት አርገው በኳስ ቁጥጥርም ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረስም ተሽለው የተገኙበት አጋማሽ ነበር። በአንፃሩ ደሴ ከተማ ኳስን በረጅም እና በመስመር መጫወትን መርጠው በመግባት ጨዋታቸውን ያከተናወኑ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ የደሴ ከተማ የመሀል ሜዳ ተጫዋቾቹ ተስሏች ሳይመን እና ማትያስ መኮንን ኳሶችን ቶሎ ቶሎ ወደ መስመር በመጣል የማጥቃት አማራጮችን ሲፈጥሩ ተስተውሏል። ጅማ አባ ጅፋሮች በፊት መስመራቸው በሱራፌል ፍቃዱ አማካኝነት ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎች ሲፈጥሩ ተስተውሏል። በዚሁ አጨዋወት የመጀመሪያው አጋማሽ ምንም ግብ ሳይቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የመጀመሪያ አጋማሽ ጉድለታቸውን ለማስተካከል የጣሩ ሲሆን ደሴ ከተማዎች የመልሶ ማጥቃትን አማራጭ አድርጎ በመውሰድ በነማናዬ ፋንቱ አማካኝነት የግብ እድል ሲፈጥሩ በጅማ አባጅፋሮች በኩል በአሚር አብዱ አማካኝነት ጥሩ ጥሩ እና ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎች ሲፈጥሩ ተስተውሏል። በ78ኛው ደቂቃ ጅማ አባ ጅፋሮች ያገኙትን ኳስ ሱራፌል ፈቃዱ ከአሚር አብዱ የተሻገረለትን ኳስ በድንቅ አጨራረስ በማስቆጠር ጅማ አባ ጅፋርን አሸናፊ ማድረግ ችሏል።

\"\"