አዳማ ከተማ ባህር ዳርን በዳዋ ሆቲሳ ብቸኛ ግብ ከረቱበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።
ፋሲል ተካልኝ – አዳማ ከተማ
ሰለጨዋታው
“ጨዋታው አስጨናቂ ነበር ፤ በተለይ ከዕረፍት በኋላ ግቧን ካገኘን በኃላ አስጨናቂ ነበር ያው ሦስት ነጥብ የሚፈልግ ቡድን መጨነቁ አይቀርም። የቁጥር ብልጫ ኖሮን እንኳን የተሻለ ተንቀሳቅሰን ዕድሎችን መፍጠር አልቻልንም በዚህ ጊዜ ሦስት ነጥብ ማግኘታችን በዕረፍት ጊዜ ለመስራት ላቀድነው ነገር ስንቅ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።”
በባህር ዳር ሜዳ የሚነጥቋቸውን ኳሶች በመጠቀም ረገድ
“ከሜዳቸው መስርተው እንዳይወጡ እና ፊት ላይ ያሏቸውን ባለክህሎት ተጫዋቾችን እንዳያገኙ ከመነሻው በመከልከል እነሱ በሚለቁት ቦታ ለመጠቀም ነበር ያሰብነው ዛሬ ከሌላው ጊዜ በተለየ እርስ በእርስ የነበረን የኳስ ግንኙነት ደካሜ ነበር ነገርግን መጨረሻ ላይ ውጤት አምጥተንበታል እንደ ጨዋታ ግን አስደሳች አልነበረም።”
አብርሃም መብራቱ – ባህርዳር ከተማ
ስለጨዋታው
“ለሁለታችን ጥሩ ጨዋታ ነበር ነገር ግን በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ በእኛ በኩል መሀል ክፍል ላይ ትንሽ መሳሳት ነበር በሁለተኛው አጋማሽ ግን ሁለት ተጫዋቾችን ቀይረን በተወሰነ መልኩ ጨዋታውንም ለመቆጣጠር ሞክረናል ዕድሎችን ፈጥረናል ነገር ግን ምናልባት ምስሉን ሳይ የምናገረው ቢሆንም አጨቃጫቂ በነበረ የፍፁም ቅጣት ምት ተሸንፈናል ውጤቱን በፀጋ እንቀበላለን።”
በተከታታይ ጨዋታ ተጫዋቾችን በቀይ ስለማጣታቸው
“ተጫዋቾች የዳኛን ውሳኔ መቀበል አለባቸው ይህ በፍፁም መለመድ የሌለበት ነው። ነገርግን ግርማን ያስወጣበት መንገድ ለእኔ ትክክል አይደለም ዳኞች አንዳንዴ ተጫዋቾችን መታገስ ይኖርባቸዋል እኔ ተጫዋቾች እየመከርኳቸው ነበር። ዳኞችም ‘እባችሁ ፍትሀዊ ሆናችሁ አጫውቱን’ ነው ይህም ልመና ነው ምንም ከስድብ ጋር አያገናኘውም። አጠገቤ ሆኖ ያለው ይህንን ነው። እኔም የምለው ነገር ነው ስለዚህ ውሳኔዎች ላይ ዳኞች ትንሽ ትዕግስተኛ ቢሆኑ ጥሩ ነው። ዳኞች የጨዋታ ህይወት ናቸው። ነገርግን የጨዋታን ውጤት ሆነ ቅርፅ የሚቀይሩ ነገሮችን ግን ላይ የሚሰጧቸው ውሳኔዎች ብዙ ደስታ አይሰጥም።”