​ሪፖርት | በሀዋሳ አሸናፊነት የተጀመረው ሊጉ በሀዋሳ ድል ወደ ረጅሙ ዕረፍት አምርቷል

በዘጠነኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ አርባምንጭ ከተማን በብሩክ በየነ ብቸኛ ግብ ማሸነፍ ችሏል።

ሀዋሳ ከተማ ከአዲስ አበባው ጨዋታ ዳዊት ታደሰ እና የአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ያለበት መድኃኔ ብርሀኔን በወንድምአገኝ ማዕረግ እና ዮሐንስ ሱጌቦ ሲተኩ አርባምንጮች ከአዳማ ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ አንፃር ተካልኝ ደጀኔ እና ቅጣቱን የጨረሰው አሸናፊ ፊዳን በአንድነት አዳነ እና ወርቅይታደስ አበበ ምትክ አስጀምረዋል።

ጨዋታው ከጅምሩ ፈጠን ያለ እና በተለያዩ የሜዳው ክፍሎች ላይ ጥሩ ፍልሚያዎችን ያሳየን ነበር። ጫና በመፍጠር ተጋጣሚያቸው እንደልብ እንዳይንቀሳቀስ በማድረግ የተሻሉ የነበሩት አርባምንጮች ሀዋሳ ረዘም ያሉ ኳስችን ወደ ፊት እንዲጥል ሲያስገድዱ ይታይ ነበር። በሁለቱም በኩል ሁለቱ መስመሮች ላይ ትኩረቱን ያደረገው የማጥቃት ሂደታቸው አልፎ አልፎ ወደ ሳጥን ሲደርስ ቢታይም ግልፅ የማግባት ዕድል መፍጠር ግን አልሆነላቸውም።

ከውሃ ዕረፍቱ መልስ ሀዋሳ ከተማዎች የተጋጣሚያቸውን ተከላካይ መስመር የመበተን ምልክት አሳይተው ነበር። 32ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አሻሞ ከመስፍን ታፈሰ በደረሰው ኳስ በቀኝ በኩል ሳጥን ውስጥ የተገኘበት አጋጣሚ ለእዚህ ማሳያ ቢሆንም ሙከራው በግቡ አናት ወጥቷል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች የጨዋታው ሂደት ቀስ በቀስ ወደነበረበት ሲመለስ ቡድኖቹ ጥሩ ምልልስ ያለው የማጥቃት ጥረትን እያደረጉ ቢቀጥሉም አንዳቸው የሌላኛቸውን ጥረት እያከሰሙ ጨዋታው ተጋምሷል።

ከዕረፍ መልስ 48ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን ከባድ ሙከራ አይተናል። በረጅሙ የተላከን ኳስ ሀዋሳዎች በአግባቡ ሳያርቁት ፀጋዬ አበራ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ሲመታ መሀመድ ሙንታሪ በቅልጥፍና አድኖታል። ጨዋታው ሲቀጥል ፀጋዬ እና ሀቢብ ተከታታይ ኳሶችን ከሳጥን ውስጥ ወደ ግብ ቢልኩም መንታሪ በእርጋታ ይዞባቸዋል። ሀዋሳዎች በድንገት የተፈጠረባቸውን ጫና በማብረድ በመልሶ ማጥቃት እና በረጅም ኳሶች ወደ አርባምንጭ ሳጥን መቅረብ ጀምረዋል። በተለይም 62ኛው ደቂቃ ላይ ከኋላ በረጅሙ የተላከን ኳስ ሲጨረርፍ ወንድምአገኝ ኃይሉ አመቻችቶለት ብሩክ በግራ ገብቶ ግልፅ ዕድል ቢያገኝም ግብጠባቂው ይስሀቅ ተገኝ አድኖበታል።

ቀጣዩ የሀዋሳ ጥቃት ፍሬ ሲያፈራ 66ኛው ደቂቃ ላይ ወንድምአገኝ በቀኝ በኩል ሰብሮ በመግባት ወደ ውስጥ የላከውን ኳስ መስፍን ታፈሰ ለመጥቀም ያደረገው ጥረት አልሳካ ቢልም ብሩክ በየነ አግኝቶግብ አግኝቶታል። አርባምንጮች ቀጥተኛነታቸውን ጨምረው ረዘም ያሉ ኳሶችን ወደ ፊት በመላክ የግብ ዕድሎችን ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። ከእነዚህ ውስጥ 86ኛው ላይ ሙና በቀለ ከቀኝ አሻግሮት ኤሪክ ካፓይቶ በግንባሩ የጨረፈው እና ወደ ውጪ የወጣው ኳስ ይጠቀሳል። ሆኖም እስከፍፃሜው የቀጠለው የአዞዎቹ ጥረት ሳይሰምር ጨዋታው በ 1-0 ውጤት ተጠናቋል።

በውጤቱ ነጥቡን 14 ያደረሰው ሀዋሳ ከተማ ደረጃውን ከስምንት ወደ አምስት ከፍ አድርጓል።