የ2014 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በሁለት ሜዳዎች በሚደረጉ ስድስት ጨዋታዎች በነገው ዕለት በሀዋሳ በይፋ ይጀመራል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስር ከሚደረጉ ውድድሮች መካከል በእንስቶች ደረጃ ቀዳሚው የሆነው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ2014 የውድድር ዘመን ከነገ ታኅሣሥ 16 ጀምሮ በሀዋሳ ግብርና ኮሌጅ ሜዳ እና በአርቴፊሻል ሜዳ ላይ በድምሩ በሚደረጉ ስድስት ጨዋታዎች በይፋ ጅማሯቸውን ያደርጋሉ፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ከሊጉ ወርደው የነበሩትን አርባምንጭ ከተማን እና አቃቂ ቃሊቲን በማካተት እንዲሁም ያደጉትን ባህርዳር ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስን አካቶ በአስራ ሶስት ክለቦች መካከል የዘንድሮው ውድድር ይደረጋል፡፡
የዘንድሮው ውድድር ከመጀመሩ በፊት ክለቦች ውድድሩ የሚጀመርበትን ቀን ፌዴሬሽኑ በጊዜ ይፋ ባለማድረጉ የተነሳ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ለማከናወን እክል እንደፈጠረባቸው አስቀድመው ክለቦች አቤቱታ ሲያሰሙ የነበረ ቢሆንም የኃላ ኃላ ውድድሩ ታኅሣሥ 16 እንጂመር ቀደም ተብሎ ከተያዘለት አንድ ቀን ወደ ኃላ በመሳብ እንዲጀመር በወሰነው ውሳኔ መሠረት ውድድሩ ነገ ዕለተ ቅዳሜ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎቻቸውን በማድረግ ይጀመራሉ፡፡
አምስት የመጀመሪያው ዙር ጨዋታዎች በሀዋሳ ከተደረጉ በኋላ ለኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የማጣሪያ ጨዋታዎች ለሀያ ቀናት እንደሚቋረጥ የሚጠበቀው የዘንድሮው የፕሪምየር ሊግ ውድድር ጨዋታዎቹ በአራት ቀናት የዕረፍት ልዩነት በሁለት ሜዳዎች ላይ ስድስት ጨዋታዎች እንዲደረጉ ምድቡ የሚያዝ ቢሆንም ለሚዲያ አዘጋገብ ምቹ አለመሆኑ እንደ እክል ለሚታይ ጉዳይ ይመስላል፡፡ ይሁን እንጂ ሶከር ኢትዮጵያ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ በመርሃግብሩ ላይ ማሻሻያ ሊደረግ እንደሚችል ቢያመላክትም እስከ አሁን ድረስ ግን ቀድሞ በወጣው ፕሮግራም የሚቀጥል እንደሆነ ሰምተናል፡፡ ጠንካራ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ የሚጠበቀው እና ከኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ወደ ኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ወደ ሚል የቀደመ ስሙ የተመለሰው ይህ ውድድር የዓምናው ሻምፒዮን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ፣ መከላከያ ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ አዳማ ከተማ አይነት ክለቦች በክረምቱ ከሰበሰቡት ስብስብ አንፃር ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ መገመት ይቻላል፡፡
በአንፃሩ በተጠናቀቀው ዓመት ብርቱ የሜዳ ላይ ተፎካካሪ የነበረው ድሬዳዋ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ በርከት ያሉ ተጫዋቾቻቸውን እንዳማጣታቸው ዘንድሮ የሚያሳዩት አቋም ከአምናው የቀዘቀዘ እንደሚሆን ቢጠበቅሞ ወጣቶችን ቀላቅለው መምጣታቸው ምናልባትም ያልተጠበቁ ውጤቶችን ያሳዩናል ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ በ2013 ከፕሪምየር ሊጉ ወርደው የተሳትፎ ዕድልኖ ዳግመኛ ማግኘት የቻሉት አርባምንጭ ከተማም ሆነ አቃቂ ቃሊቲ አዳዲስ አሰልጣኞችን ቀጥረው መምጣታቸው ምን አልባት የተወሰነ የቅርፅ ለውጥ መፍጠር የሚያስችላቸው መሆኑ ዕውን ቢሆንም ከስብስብ አንፃር ግን የተወሰነ ክፍተት እንዳለባቸው በክረምቱ ያስፈረሟቸውን ተጫዋቾች መመልከት በቂ ነው፡፡ ምናልባት ግን አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ ከሀዋሳ ከተማ በኋላ በአርባምንጭ ከተማ ዳግም መመልከታችን በሰማያዊ ለባሾቹ ቤት የሰራቸውን ጠንካራ የፉክክር መንፈስ በአርባምንጭ ከተማ እናያለን የሚለውም ጉዳይ ተጠባቂ ሆኗል፡፡
ውድድሩ ነገ ሲጀመር በውድድሩ ላይ የሚጠበቁ ተጫዋቾች ቢኖሩም በዚህ ዓመት የአዳማ ከተማ ተከላካይ የሆነችው ወይንሸት ፀጋዬ (ኦሎምቤ) እና የንግድ ባንኳን ጥሩአንቺ መንገሻ በግል ጉዳዮች እንዲሁም መሳይ ተመስገንን የማንመለከታቸው ሲሆን በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት አንጋፋዋን አጥቂ ሽታዬ ሲሳይን ሳንመለከታት መቅረታችን ይታወሳል፡፡ በሀገር ውስጥ እግር ኳስ ግንባር ቀደም የመረጃ ምንጭ የሆነችው ሶከር ኢትዮጵያ የዘንድሮውን ውድድር በተለየ አቀራረብ ወደ እናንተ መረጃዎችን የምታደርስልዎ ይሆናል፡፡
የመጀመሪያ ሳምንት የጨዋታ መርሃግብር
ሀዋሳ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ (3፡00 አርቴፊሻል ሜዳ)
አዲስ አበባ ከተማ ከ ባህርዳር ከተማ (3፡00 ግብርና ኮሌጅ ሜዳ)
አዳማ ከተማ ከ አቃቂ ቃሊቲ (5፡00 አርቴፊሻል ሜዳ)
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ (5፡00 ግብርና ኮሌጅ ሜዳ)
ቦሌ ክፍለከተማ ከ መከላከያ (10፡00 አርቴፊሻል ሜዳ)
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ አርባምንጭ ከተማ (10፡00 ግብርና ኮሌጅ ሜዳ)