ከፍተኛ ሊግ | የ16ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ \’ሀ\’ በዝናብ ምክንያት ለዛሬ የተዘዋወሩ ሁለት ጨዋታዎች ተከናውነዋል።

አዲስ ከተማ ክ/ከ ከቡታጅራ ከተማ ያገናኘው የጠዋቱ ጨዋታ አዲስ ከተሞች የበላይነት ተገባዷል።

ከተከታታይ ሁለት ጨዋታ ነጥብ ከጣሉበት ድክመታቸው ዛሬ ተሻሽለው የቀረቡት አዲስ ከተማዎች ገና በጨዋታው ጅማሬ ነበር የመጀመርያ ጎላቸውን ማግኘት የቻሉት። በ3ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን የመሐል ተከላካዩ አብዱሀሚድ ሙዘሚል በጥሩ አነሳስ በግንባሩ በመግጨት ወደ ጎልነት ቀይሮታል። በዚህች ጎል የተነቃቁት አዲስ ከተማዎች በተለይ የመሐሉን የሜዳ ክፍል በባለ ብዙ ልምዱ ቡርክ አየለ መሪነት ብልጫ ወስደው ማጥቃታቸውን ቀጥለው። ከደቂቃዎች በኋላ ሁለተኛ ጎላቸውን ማግኘት ችለዋል።

በጥሩ በየኳስ ቅብብሎሽ ወደ ግራ መስመር አድልተው የመጡት አዲስ ከተማዎች አህመድ አብዱ ሁለት ተከላካዩችን ቀንሶ በማለፍ አምስት ከሀምሳ ውስጥ ራሱን ነፃ አድርጎ ለቆመው ብሩክ አየለ ጣጣውን ጨርሶ ያቀበለውን ብሩክ ኳሱን በተገቢው መንገድ በመቆጣጠር ወደ ጎልነት ቀይሮታል። የመከላከል አደረጃጀታቸውም ሆነ በጨዋታ እንቅስቃሴ ክፍተት የነበረባቸው በደረጃው ሠንጠረዡ ግርጌ የሚገኙት ቡታጅራ ከተማዎች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን የጎል ዕድል መፍጠር ሲሳናቸው ተመልክተናል።

ከጨዋታው ነጥብ ይዘው ለመውጣት ብርቱ ጥረት ማድረጋቸውን የቀጠሉት አዲስ ከተማዎች ወደ ዕረፍት መደረሻው ላይ የጎል መጠናቸውን ወደ ሦስት ከፍ ማድረግ የሚችሉትን በ40ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ወጣቱ ተስፈኛ የመስመር አጥቂው አሸናፊ በቀለ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ብዙ የግብ እድሎችን ሳይጠቀም የቀረው ሰለሞን ጌዲዮን በስተመጨረሻ ለጥረቱ ምላሻ የሆነ ጎል አግኝቷል።

\"\"

አስቀድመው ሦስት ጎል በማስቆጠር ውጤታቸውን ያሰፉት አዲስ ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ ቀዝቀዝ ያለው እንቅስቃሴቸው በጥንቃቄ በመከላከል ውጤት የማስጠበቅ አጨዋወት ሲከተሉ ታዝበናል። በአንፃሩ ቡታጅራ ከተማዎች ከመጀመርያው አጋማሽ በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም ጎሎችን ማስቆጠር ባለመቻላቸው በአዲስ ከተማ ሦስት ለዜሮ ተሸንፈው ሊወጡ ችለዋል።

አምስት ሰዓት የቀጠለው የወሎ ኮምቦልቻ እና የባቱ ከተማ ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል።

ሁለቱም ቡድኖች ተቀራራቢ ደረጃ ለይ የሚገኙ በመሆናቸው ለመሸናነፍ ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ የተጠበቀው ጨዋታ ጎል አይቆጠርበት እንጂ ለተመልካች አዝናኝ የሆነ እንቅስቃሴ አስመልክተውናል። ከድል የመጡት ባቱ ከተማዎች ከወሎ ኮምቦልቻዎች በተሻል የጎል ዕድል መፍጠር ችለዋል።

በተለይ በሁለት አጋጣሚዎች አጥቂው ተመስገን ቃባቶ ከወሎዎች ከግብ ጠባቂ ጋር ብቻውን ተገናኝቶ ያልተጠቀመበት እና አማካይ በኃይሉ ተስፋዬ ሌላ ለጎል የቀረበ እድል አግኝቶ ያመከነው ተጠቃሽ ነው። በአሰላ አረንጋዴ ስታዲየም በሚካሄደው በዚህ ውድድር ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሉ እያስመለከተን የሚገኘው ወሎ ኮምቦልቻ መሐል ሜዳው ላይ ብልጫ እንዳይወሰድባቸው በመቆጣጠር አልፎ አልፎ በብቸኛው አጥቂያቸው አማካኝነት ጎል ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት ፍሬ ሳያፈራ ቀርቷል። በአንድ አጋጣሚ አጥቂው አኩየር ቻሞ ከውሳኔ ችግር ያልተጠቀመበት አስቆጪ ሆኗል። ጨዋታው ያለ ጎል ሊጠናቀቅ ችሏል።

ትናንት የተደረገው ተጠባቂው የሀላባ ከተማ እና የወልድያ ጨዋታ ብዙም የተጠበቀውን ሳይሆን ያለ ጎል መጠናቀቁ ይታወቃል።

\"\"