መረጃዎች | 68ኛ የጨዋታ ቀን

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአዳማ ቆይታ ነገ ሲጀመር በ17ኛ ሣምንት የሁለተኛ ቀን መርሐግብር የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንዲህ አሰናድተናል።

መቻል ከ አዳማ ከተማ

የዕለቱ ቀዳሚ መርሐ-ግብር በአራት ደረጃዎች እና በሁለት ነጥቦች ተበላልጠው 5ኛ እና 10ኛ ደረጃ የተቀመጡት መቻል እና አዳማ ከተማን ሲያገናኝ ሊጉ ከመቋረጡ በፊት ወሳኝ ተከታታይ ድል የተቀዳጁት ሁለቱም ቡድኖች እያሳዩት ያለውን መነቃቃት ለማስቀጥል ውጤቱ እጅግ ከማስፈለጉ አንጻር ከፍተኛ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ውድድሩን ሲጀምሩ ከተጠበቁት በተቃራኒው የውጤት ማሽቆልቆል ውስጥ ገብተው የነበሩት መቻሎች ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ግን በእጅጉ እየተሻሻሉ መጥተዋል። ከመጀመሪያዎቹ 10 ጨዋታዎች በሁለቱ ብቻ ድል ሲቀናቸው ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ግን ሦስቱን መርታት ችለዋል። ከውጤታቸው ባሻገር ካስቆጠሯቸው 17 ግቦች 11 የሚሆኑት (64.7 %) የተቆጠሩትም በእነዚህ አምስት ጨዋታዎች መሆኑ የቡድኑን መሻሻል በግልጽ ያስረዳሉ ( ከለገጣፎ ጋር ሊደረግ ታስቦ ፎርፌ የተሰጠበት ጨዋታ የቡድኑን እንቅስቃሴ ለመግለጽ ስለማይረዳን ከቁጥራዊ መረጃዎች ላይ አለማካተታችንን ልብ ይሏል)።

መቻሎች በ16ኛው ሣምንት ሀዲያ ሆሳዕናን 2-1 ሲረቱ በ15 ደቂቃዎች ውስጥ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥሩ ቀሪዎቹን ደቂቃዎች ታክቲካሊ ዲሲፕሊንድ በመሆን የመረጡት ጥንቃቄ የተሞላበት ጨዋታ በነገው ዕለትም ሲጠበቅ በአማካይ ስፍራ ላይ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘው እና ሁለቱን ሳምንታት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ያሳለፈው ከነዓን ማርክነህም በተሻለ የጨዋታ ስሜት ልዩነት ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

\"\"

ባህር ዳር ላይ ካሳዩት እንቅስቃሴ አንፃር እና ከሚመርጡት አጨዋወት ጋር ሜዳው ምቹ ባልሆነላቸው የድሬዳዋ ሜዳ አራት ተከታታይ ሽንፈቶች አስተናግደው የነበሩት አዳማዎች  በመጨረሻ ካደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች ግን በአራቱ ድል ሲቀናቸው አንዱን ብቻ ተሸንፈዋል። በነገው ዕለትም ለሚመርጡት ከኳስ ጋር የመቆየት አጨዋወት ምቹ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የአዳማ ሜዳም ለእንቅስቃሴያቸው ይረዳቸዋል ተብሎ ይታሰባል። በተለይም ወጣቱ አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በሥነምግባር እና በወጣቶች የመጫወት ዕድል ላይ ያላቸው የውሳኔ አፈጻጸም ውጤታማ እያደረጋቸው ይገኛል።

ከሰሞኑ በመጨረሻዎቹ ሁለት የሊጉ ጨዋታዎች ባስቆጠራቸው ሦስት ግቦች እና በሚያሳየው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ የብዙዎችን ትኩረት የሳበው ከአዳማ ተስፋ ቡድን የተገኘው አጥቂ ዮሴፍ ታረቀኝ ለብሔራዊ ቡድን የተደረገለትን ጥሪ ተከትሎም ሀገሩን ወክሎ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ አድርጎ መመለሱ የሚፈጥርለትን መነቃቃት ተጠቅሞ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለመቻሎች ፈተና ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

በመቻል በኩል ጉልበቱ ላይ ጉዳት አስተናግዶ የነበረው ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ እስካሁን ልምምድ ባለመጀመሩ ከነገው ጨዋታ ውጪ የሆነ ብቸኛው የቡድኑ አባል ሲሆን በአዳማ ከተማዎች በኩል ደግሞ አዲስ ተስፋዬ በህመም ምክንያት ከጨዋታው ውጪ ነው።

የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ በአዳማ 2-0 አሸናፊነት መጠናቀቁ ሲታወስ በአጠቃላይ ከዚህ ቀደም በሊጉ ለሰላሳ(30) ያህል ጊዜያት በተገናኙባቸው ጨዋታዎች አሥራ ሦስቱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ መቻል ለስምንት አዳማ ደግሞ ለዘጠኝ ጊዜያት ድል አድርገዋል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ከዕረፍት መልስ የሚደረገውን የሊጉ ቀዳሚ ጨዋታን በዋናነት ፣ ከኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና ዳዊት ገብሬ ጋር በረዳትነት ፣ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ በበኩሉ በአራተኛ ዳኝነት በጣምራ ይመሩታል።

ሲዳማ ቡና ከ ሀዲያ ሆሳዕና

ሊጉ ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ከመቋረጡ በፊት በነበረው የጨዋታ ሳምንት ሽንፈት የገጠማቸው ሀዲያ ሆሳዕና እና ሲዳማ ቡና ነገ ምሽት ከውድድሩ መመለስ በኋላ እጅግ አስፈላጊያቸው የሆኑ ሦስት ነጥቦችን ለማሳካት ይገናኛሉ።

ሀዲያ ሆሳዕና በደካማ ወቅታዊ አቋም ውስጥ ይገኛል። በሊጉ ከገጠሙት አጠቃላይ አምስት ሽንፈቶች ሦስቱን በተከታታይ የመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች አስመዝግቧል። ከዚህም ባለፈ ቡድኑ በመጨረሻው የመቻል ጨዋታ ካስቆጠራት ግብ ውጪ ከዚያ ቀደም በነበሩት አምስት ጨዋታዎች ኳስ እና መረብን ማገናኘት ተስኖት ቆይቷል። ይህንንም ተከትሎ ለሊጉ መሪዎች ቀርቦ ከነበረበት አሁን ላይ የሰንጠረዡን አጋማሽ ተሻግሮ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በመሆኑም ቡድኑ እያሳለፈ ካለው ደካማ የውድድር ጊዜ አንፃር የነገው ጨዋታ ውጤት አብዝቶ ያስፈልገዋል።

ሲዳማ ቡና ሁሉንም ጥሩ ነገሮቹን ባጣበት የድሬዳዋ ከተማ የመጨረሻ ቆይታ በባለሜዳዎቹ የደረሰበትን ሽንፈት በዕረፍቱ ቀናት በነበሩት ቆይታዎቹ ረስቶ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል። በወራጅ ቀጠና ውስጥ ያሉት ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ለገጠፎ ለገዳዲን በመርታት ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሰው የነበሩት ሲዳማዎች በድሬው ጨዋታ በተለይም ተሻሽለው የታዩበት የመስመሮች ጥቃት እና የፊት መስመር ተሰላፊዎቻቸው መናበብ መደገም ሳይችል ቀርቷል። ከዚህም በላይ በተጫዋች ተገቢነት ምክንያት ጨዋታውን በሦስት ጎል ዕዳ በፎርፌ ለማጣት ተገዷል። ከወትሮው ጠንካራ ተፎካካሪነቱ ወርዶ ከወራጅ ቀጠናው አንድ ነጥብ ርቀት ላይ የሚገኘው ሲዳማ የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ከአስጊው ዞን ፈቀቅ ያደርገዋል።

በሀድያ በኩል ቤዛ መድህን እና ቃልአብ ውብሸት በጉዳት የማይኖሩ ሲሆን ሲዳማዎች በበኩላቸው የይገዙ ቦጋለ እና የሙሉዓለም መስፍንን ግልጋሎት አያገኙም። አዲሱ ጋናዊ አጥቂ ፊሊፕ አጃህ ግን ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑ ተጠቁሟል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን ሰባት ጨዋታዎች አድርገዋል። ሁለቴ ነጥብ ሲጋሩ 14 ግቦች ያሉት ሀዲያ ሆሳዕና ሦስት ፣ 8 ግቦች ያሉት ሲዳማ ቡና ደግሞ ሁለት ድሎችን አስመዝግበዋል።

የምሽቱን ጨዋታ ለመምራት ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በመሀል ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል እና ሀብተወልድ ካሳ ረዳቶች ፣ ተስፋዬ ግሩሙ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።

\"\"