የአሰልጣኝ ተመስገን ዳና ጉዳይ…

\”ከእኔ ፍቃድ እና ዕውቅና ውጪ ነው ይግባኝ የተጠየቀው።\” አሰልጣኝ ተመስገን ዳና

\”ጉዳዩ አልቆ ይግባኙ ውድቅ ከሆነ በኋላ \’አልፈለኩትም\’ ማለት ብዙም አያስኬድም።\” የአሰልጣኙ ጠበቃ አቶ ብርሃኑ በጋሻው

በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና በኢትዮጵያ ቡና መካከል ሲደረግ የነበረውን ክርክር ጉዳዩን የያዘው ዲሲፒሊን ኮሚቴ \”ኢትዮጵያ ቡና ውሉን ያቋረጠበት አግባብ ተገቢ ነው\” በማለት ውሳኔ ቢያሳልፍም አሰልጣኙ በጠበቃቸው አማካኝነት ከአንድ ወር በፊት ይግባኝ መጠየቃቸውን ተከትሎ የእግርኳሱ የበላይ አካል በትናትናው ባወጣው ደብዳቤ መሠረት የመጨረሻ ውሳኔ ማሳለፉ ታውቋል። ሶከር ኢትዮጵያ ትናንት የይግባኝ ውሳኔ ዘገባውን ካቀረበች በኋላ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ውሳኔውን እንደማያቁ እና ከፍላጎታቸው ውጪ የተፈፀመ መሆኑ ከሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች አያይዘው ጠበቃቸው ብርሀኑ በጋሻውን በተመለከተ ሀሳባቸውን አንስተዋል። እኛም የጉዳዩ ባለቤቶችን አነጋግረን የሰጡንን ምላሽ እንደወረደ አቅርበነዋል።

\"\"

\”ለጠበቃዬ ይግባኝ እንደማልፈልግ እና ክሱ እንዲቋረጥ ተናግሬያለሁ። በክስ ከሚገኝ ጥቅማጥቅም የለም። ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለኝ ጉዳይ በሰላም እንዲጠናቀቅ ነበር የምፈልገው። አሁን ራሴን ከእንደዚህ ያሉ ክርክሮች አርቄ ሌላ ክለብ መያዙንም ነው የሚሻለው። ከእኔ ዕውቅና እና ፍቃድ ውጪ ነው ይግባኝ የተጠየቀው። ከጠየቀም ለእኔ ደብዳቤ መላክ ነበረበት። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ነው ዜናውን ያየሁት። በጊዜው ለኔ በጉዳዩ ዙርያ ደብዳቤ ያልደረሰኝ በመሆኑ ተደናግጬ ነበር። ሌላ ቡድን ለማሰልጠን እየጠበቅኩ ስለሆነ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለኝን ነገር ማጥራት ነው የምፈልገው።\” አሰልጣኝ ተመስገን ዳና

\”የይግባኝ ደብዳቤ ከገባ በኋላ \’ክሱን አቋርጥልኝ\’ አለኝ። እኔም \’ይግባኝ ተጠይቋል ከተወሰነ ሂደቱ ይወሰንልሀል ካልሆነ የሚሆነውን መጠበቅ አለብን\’ አልኩት። በእኔ እና በእሱ መካከል እስከ ይግባኝ ድረስ ስምምነት ነበረን። እንዲህ ዓይነት ጉዳይ ስትይዝ እስከ መጨረሻው ነው የምትይዘው ፤ ውል ያለው በመሆኑ። ከትናንቱ ውሳኔ በኋላ \’ይግባኙ ተጠይቆ እኮ አልተወሰነልንም\’ አልኩት እሱም \’መጀመሪያ እኮ ይግባኙ እንዲቆምልኝ ፈልጌ ነበር\’ አለኝ። ክርክሩ በሚደረግ ሰዓት ይግባኝ እንደጠየቅኩለት ያውቃል ፤ ማቋረጥ ከፈለገ እና የኔን ፍቃድ እንኳን ባይጠብቅ ደብዳቤ ፅፎ \’አንስቻለሁ\’ ብሎ ማሳወቅ ነበረበት። አሁን ከተወሰነ በኋላ እንዲህ ቢል እኔንም አይመጥነኝም። ምክንያቱም እኔ እሱን ለመጥቀም ነው ህግ እና ኃላፊነቴን ተጠቅሜ እንደዚህ ያደረግኩት። ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች አሉ እንደዚህ ዓይነት ጉዳይ የሚያጋጥማቸው እና ክሱን አንፈልግም ይቋረጥልኝ ካሉ ደብዳቤ ይልካሉ። አሰልጣኝ ተመስገን ግን ደብዳቤ አላከልኝም። ስለዚህ እኔ ሥራዬን ነው የሠራሁት ምክንያቱም ነገ ደግሞ \’ለምን ይግባኝ አልጠየቀልኝም ?\’ ሊለኝ ስለሚችል። ይህንን ማለት የነበረበት ዛሬ አልነበረም። ህጋዊ ስለሆነ የኔን ፍቃድ እንኳን ባይጠብቅ ለፌዴሬሽኑ ደብዳቤ አስገብቶ \’ይግባኙን ትቼዋለሁ\’ ማለት ነበረበት። ጉዳዩ አልቆ ከተወሰነ በኋላ ይግባኙን አልፈለኩትም ማለት ብዙም አያስኬድም። ይግባኝ እንደጠየቅኩ ያውቃል።\” የህግ ጠበቃ አቶ ብርሀኑ በጋሻው

\"\"