የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ቀጥለው ተካሂደዋል። እኛም የሰበታው ምድብ ለ ላይ ትኩረት አድርገን የዛሬ ውሎን እንዲህ ቃኝነተነዋል።
ዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ እጅግ ጠንካራ ፉክክር የታየበት እና አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔዎች የጨዋታውን መንፈስ የቀየረው ከንባታ ሺንሺቾ እና ቤንች ማጂ ቡና ያደረጉት ጨዋታ በቤንች ማጂ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል። ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ባስመለከተን በዚህ ጨዋታ አስቀድሞ ወደ ጎል በመድረስ ሙከራ ያደረጉት ከንባታዎች ነበሩ። በዚህም አንበሉ ኤፍራም ታምራት ከሳጥን ውጭ በግራ እግሩ አክሮ የመታው ነገርግን ግብጠባቂው አድኖበታል። አጀማመራቸው ቀዝቀዝ ያለ ቢመስልም ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው የገቡት ቤንች ማጂ ቡናዎች ኳሱን ተቆጣጥረው በተደራጀ ሁኔታ ባደረጉት ማጥቃት ከእረፍት በፊት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት አካሉ አቲሞ ወደ ጎልነት በመቀየር መሪ መሆን ችለዋል።
የዕለቱ ዳኛ አስቀድመው በሁለቱም በኩል እየተፈፀመ የነበረውን ጉሽሚያ በምክር በኋላም በካርዳቸው መቆጣጠር ሲገባቸው በዝምታ በማለፋቸው ጨዋታውን መምራት ሲቸገሩ ተመልክተናል። ከፍፁም ቅጣት ምቱ መቆጠር በኋላ የጨዋታው መልካም ፉክክር እና እንቅስቃሴ ተለውጦ በተደጋጋሚ በሚሰሩ ጥፋቶች ሲቆራረጥ ቆይቷል። በዚህ ሂደት ውስጥ ጥሩ እግርኳስ የሚጫወቱት ቤንች ማጂ ቡናዎች ከንባታዎች አቻ ለመሆን ጎል ፍለጋ ነቅለው በሚወጡበት አጋጣሚ በሚፈጥሩ ክፍት ሜዳዎችን በመጠቀም የጎል መጠናቸውን ለማስፋት የሚችሉበትን ዕድሎችን ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። በቤንች ማጂዎች ቡድን ውስጥ በተለይ አስራ ሰባት ቁጥር ለባሹ ሙልጌታ ጥላሁን የሚያሳየው እንቅስቃሴ እና ክህሎቱ አስገራሚ ነበር። በስተመጨረሻም ከምባታዎች አቻ ለመሆን የቀድሞውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኮከብ አንዷለም ንጉሴን ቀይሮ በማስገባት ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ሽንፈት ሲያስተናግዱ በአንፃሩ በቤንች ማጂ ቡናዎች ወደ አሸናፊነት ተመልሰው ጨዋታው ተጠናቋል።
ረፋድ ላይ በተካሄደው ሁለተኛው ጨዋታ የሆነው የክፍለ ከተማ ደርቢ ፍልሚያ በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል። በጨዋታው ጅማሬ የቂርቆሱ የመስመር አጥቂ ጅላሎ ሻፊ ራሱ ላይ በተሰራው ጥፋት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ኮልፌዎች ለጨዋታው ዝቅተኛ ግምት በመስጠት ቀዝቀዝ ያለው እንቅስቃሴያቸው ጎሉ ከተቆጠረባቸው በኋላ ከፈዘዙበት ተነቃቅተው የጎል ሙከራዎችን ማድረግ ጀምረዋል። ረጂብ ሚፊታ ግልፅ የጎል አጋጣሚ አግኝቶ ያልተጠቀመበት አብዱልከሪም ቃሲም ከግብጠባቂው ጋር ብቻውን ተገናኝቶ ግብጠባቂው ያዳነበትን በዚሁ እንክስቃሴ በተገኘው የማዕዘን ምት የተሻገረ ተከላካዮ ብስራት ያልተጠቀመበት አጋጣሚዎች ኮልፌዎችን ወደ ጨዋታው የሚመልሱ የጎል ሙከራዎች ነበሩ። በቂርቆስ በኩል ልምድ ያላቸው በርከት ያሉ ተጫዋቾች በቡድኑ ውስጥ በመኖራቸው የኮልፌን ፈጣን እንቅስቃሴ በማቀዝቀዝ ወደ ፊት በመሄድ አልፎ አልፎ አደጋ ለመፍጠር ይሞክሩ እንደነበረ አስተውለናል። የቂርቆስ ግብጠባቂ ዳግም አራጌ ስራ በዝቶበት በዋለው በዚህ ጨዋታ በሙሉ የማጥቃት አቅማቸው የተንቀሳቀሱት ኮልፌዎች እሱባለው ሙልጌታ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ከመስመር አጥብቦ በመግባት ጎል አስቆጠረ ሲባል ግብጠባቂው ያመከነበት አስቆጪ ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ ኮልፌዎች ጎሎችን ፍለጋ ተጭነው መጫወታቸውን ቀጥለው ከማዕዘን ምዕት የተሻገረውን ፍቃዱ አሰፋ በጥሩ ሁኔታ ኳሱ አየር ላይ እያለ በእግሩ በመምታት ቡድኑን አቻ አድርጓል። ከዚህች የአቻነት ጎል መቆጠር በኋላ ቂርቆሶች ከተከላካይ ጀርባ ለአስራት ሸገሪ የጣሉለትን ነገርግን አስራት ብቻውን ከግብጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሲያመነታ ከውሳኔ ችግር ከኋላው ተከላካዩ ደርሶበት ተደርቦ ያወጣበት አስቆጪ ነበር። የአጥቂ ቁጥራቸውን በመቀነስ ቂርቆሶች ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት ሲከላከሉ ኮልፌዎች በተቃራኒው የአጥቂ ቁጥራቸውን በመጨመር ለማሸነፍ ያደረጉት ጥረት ተቀይሮ በገባው አብርሀም አሰፋ አማካኝነት ለማመን የሚከብድ ለጎሉ ሁለት ሜትር ርቀት ላይ አምክኗል። ጨዋታው በዚሁ ውጤት አንድ አቻ ተጠናቋል። ሰበታ ከተማ በሚካሄደው የከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ ውድድር ላይ በቂርቆስ በኩል የቀድሞ ተጫዋች ፍሬህይወት አሳዬ በብቸኝነት እንስት የቡድን መሪ በመሆን እያገለገለች ትገኛለች።
የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ የሆነው የሰንዳፋ በኬ እና የቡራዩ ከተማ ጨዋታ በቡራዬ የበላይነት ተጠናቋል። ገና በጨዋታው ጅማሬ በፍጥነት ወደ ጎል የደረሱት ሰንዳፋ በኬዎች በመስመር አጥቂያቸው አቤል ታምራት አማካኝነት ያደረጉት ግልፅ የጎል አጋጣሚ የጎሉ አግዳሚ መልሶባቸዋል። በእንቅስቃሴ ብልጫ መውሰድ የጀመሩት ቡራዮዎች ምንም እንኳን ለጎል የቀረበ ሙከራ አያድርጉ እንጂ ወደ ፊት በመሄድ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ፍፁም ቅጣት ምት እንዲያገኙ አስችሏቸው ካሚል አህመድ ለቡራዩ ቀዳሚውን ጎል አስቆጥረዋል። በዳኛው ውሳኔ ደስተኛ ባለመሆን ተገቢም ተገቢም ያልሆኑ ቅሬታዎችን በተደጋጋሚ ሲያሰሙ የነበሩት ሰንዳፋዎች ወደ እረፍት መዳረሻ ላይ ከማዕዘን ምት በተሻገረ ኳስ እንዳልክ ሰይፉ ጎል አስቆጥሮ አቻ መሆን ችለዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ብዙም ሳይቆይ በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የቆየው ካሚል አህመድ ሳጥን ውስጥ በተሰራበት ጥፋት በድጋሚ ቡራዩዎች ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው እራሱ ካሚል አህመድ ለቡድኑም ለራሱም ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። ከጨዋታው ይልቅ ከዕለቱ ዳኛ ጋር ጭቅጭቅ ይፈጥሩ የነበሩት ሰንዳፋዎች በአንድ አጋጣሚ የቡራዩ ግብጠባቂ ኢብሳ ኳስ ለማረቅ የግብ ክልሉን አልፎ ያሳጠረውን ኳስ የሰንዳፋው አጥቂ ቅዱስ ግኝቶ ጎል አስቆጠረ ሲበል ያልተጠቀመበት አስቆጪ ሆኖ አልፏል። በስተመጨረሻም ከጨዋታ ጨዋታ ጥንካሬያቸውን እያሳዮ የሚገኙት ቡራዩዎች ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት ያደረጉት ጠንካራ መከላከል ሰምሮላቸው አሸንፈው በመውጣት ምድባቸውን መምራት ችለዋል።
ሆሳዕና ላይ እየተደረገ በሚገኘው የምድብ ሀ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ መሪነት ከፍ ያለበትን ድል አምቦ ላይ አሳክቷል። ኤሌክትሪክ 3-0 ባሸነፈበት ጨዋታ ኢብራሂም ከድር በ30ኛ እና 63ኛ ደቂቃ ሁለት ጎሎች ሲያስቆጥር ፊሊሞን ገብረፃዲቅ ሦስተኛውን አክሏል።
ሻሸመኔ ከተማ በውድድሩ መጥፎ አጀማመር እያደረገ የሚገኘው ገላን ከተማን 2-1 አሸንፏል። ባና ዓሊ እና ቴዎድሮስ ታምሩ የሻሸመኔ የድል ጎሎችን ሲያስቆጥሩ ኢዩኤል ሳሙኤል በመጨረሻ ደቂቃ የገላንን ጎል አስቆጥሯል።
በምድብ ሐ ነቀምቴ ከተማ በድንቅ አጀማመሩ በመቀጠል መሪነቱን ያጠናከረበትን ድል አስመዝግቧል። ሀምበሪቾን 4-1 ላሸነፈው ነቀምቴ ዋቁማ ዲንሳ ሁለት ሲያስቆጥር ምኞት ማርቆስ እና ኢብሳ በፍቃዱ አንድ አንድ ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።
ከተከታታይ ነጥብ መጣል በኋላ ባለፈው ሳምንት ወደ ድል የተመለሰው ኢትዮጵያ መድን ፌዴራል ፖሊስን 2-0 በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ አድርጓል። አብዱልለጢፍ ሙራድ እና መስፍን ዋጄ (ራሱ ላይ) የመድንን ጎል ማስቆጠር የቻሉ ተጫዋቾች ናቸው።