ሪፖርት | አዳማ ከተማ በታዳጊዎቹ በመታገዝ ወሳኝ ድል አሳክቷል

አጓጊ የመጨረሻ ደቂቃ ትዕይንቶች በታዩበት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአዳማ ቆይታ ማብሠሪያ ጨዋታ አዳማ ከተማ መቻልን 3-2 መርታት ችሏል።

የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ቆይታ ማብሠሪያ የሆነው የመቻል እና የአዳማ ከተማ ጨዋታ የክብር እንግዶችን በመተዋወቅ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙርን በጋራ በመዘመር 09፡00 ሲል ጅማሮውን አድርጓል።

\"\"

ገና በ3ኛው ደቂቃ ላይ እስራኤል እሸቱ ከሳጥን ውጪ ሞክሮት የግቡን አግዳሚ ታክኮ በወጣበት ኳስ የመጀመሪያውን የማጥቃት እንቅስቃሴ ባስመለከተን ጨዋታ አዳማዎች የራሳቸው የግብ ክልል ውስጥ ስኬታማ ቅብብል በማድረግ ዝግ ባለ የማጥቃት ሂደት መጫወትን ሲመርጡ መቻሎች በበኩላቸው የራሳቸው የግብ ክልል ውስጥ በሚደርሳቸው ኳስ ከጫና ለመውጣት በተለይም እስራኤል እሸቱን ማዕከል ያደረጉ ቀጥተኛ ኳሶች ለመጣል ሲሞክሩ ቀስ በቀስ ግን እየሻሻሉ በመሄድ 16ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ግርማ ዲሳሳ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው እስራኤል እሸቱ ያደረገውን ሙከራ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘው ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ በጥሩ ቅልጥፍና በእግሩ አግዶበታል።

በቀኙ የማጥቂያ መስመራቸው በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን መድረስ የቻሉት መቻሎች 42ኛው ደቂቃ ላይም በድጋሚ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። 23ኛው ደቂቃ ላይ ጉዳት በገጠመው ፍፁም ዓለሙ ተቀይሮ የገባው ሳሙኤል ሳሊሶ ከቀኝ መስመር ገፍቶ የወሰደውን እና ያሻረገረውን ኳስ በተከላካዩ ሚሊዮን ሰለሞን ተጨርፎ ያገኘው በረከት ደስታ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ ቢገኝም በደካማ አጨራረስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

እንደነበራቸው የኳስ ቁጥጥር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት አዳማዎች ወደ ዕረፍት ለማምራት በተጨመሩ የባከኑ ደቂቃዎች ውስጥ ዮሴፍ ታረቀኝ ሳጥን ውስጥ የግል ክህሎቱን ተጠቅሞ ተከላካይ አታልሎ በማለፍ ያደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ብቻ ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ሲሆን በሰከንዶች ልዩነት ግን ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። ከነዓን ማርክነህ በግሩም ክህሎት ተከላካዮችን አታልሎ በማለፍ ኳሱን ካዘጋጀበት እንቅስቃሴ አንፃር በወረደ አጨራረስ የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ከዕረፍት መልስ አዳማዎች እጅግ ተሻሽለው በመቅረብ ከግራ የተከላካይ መስመራቸው ውጪ ባለው ቦታ ሁሉ መጠነኛ ብልጫ መውሰድ ችለዋል። 55ኛው ደቂቃ ላይ ቦና ዓሊ ሳጥን ውስጥ በግራ እግሩ ወደግብ ሞክሮት በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት በወጣው ኳስ የአጋማሹን የማጥቃት እንቅስቃሴ የጀመሩት አዳማዎች 60ኛው ደቂቃ ላይ ከሰሞኑ በተሰጠው የመሰለፍ ዕድል የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች መሆን የቻለው ተስፈኛው ታዳጊ ዮሴፍ ታረቀኝ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ አክርሮ በመምታት በድንቅ አጨራረስ ባስቆጠረው ግብ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ በፈጠሯቸው የግብ ዕድሎች ልክ ግብ ማስቆጠር ይጠበቅባቸው የነበሩት መቻሎች ከዕረፍት መልስ በተደራጀ ቅብብል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ሲቸገሩ እና 65ኛው ደቂቃ ላይ በአጋማሹ የተሻለውን የመጀመሪያ የግብ ዕድል ሲፈጥሩ ግሩም ሀጎስ ሳጥን ውስጥ በሌሎች ተጫዋቾች ከተነካካ በኋላ ባገኘው ኳስ ያደረገውን ሙከራ ግብጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ እና ተከላካዮች ተረባርበው መልሰውበታል።

አዳማዎች በተረጋጋ የጨዋታ ስሜት ሲቀጥሉ 72ኛው ደቂቃ ላይ ሌላኛው ተስፈኛቸው ቢንያም ዓይተን በግሩም አጨራረስ ባስቆጠረው ግብ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ሁለተኛ ግብ ባስተናገዱበት ቅፅበት በከነዓን ማርክነህ የግብ ሙከራ ማድረግ የቻሉት መቻሎች በርካታ ቅያሪዎችን በማድረግ ጠንካራ እንቅስቃሴ ማድረግ ሲችሉ 86ኛው ደቂቃ ላይም ወደ ጨዋታው የተመለሱበትን ግብ አስቆጥረዋል።

በማራኪ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ በስተመጨረሻም ምንይሉ ወንድሙ ለሳሙኤል ሳሊሶ ሲያቀብል ከሳጥኑ የቀኝ ከፍል ላይ የነበረው ሳሙኤል ሳሊሶም ተከላካይ አታልሎ በማለፍ በተረጋጋ አጨራረስ ሲያስቆጥረው በአንድ ደቂቃ ልዩነት ደግሞ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ የአዳማው ተከላካይ ጀሚል ያዕቆብ ኳሱን በመሳቱ ከጀርባው የነበረው ግርማ ዲሳሳ አስቆጥሮትም ጨዋታውን አቻ በማድረግ ግለቱን ይበልጥ ሲጨምረው 91ኛው ደቂቃ ላይ ግን ዮሴፍ ታረቀኝ ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ በመቻሉ ግብጠባቂ ተክለማርያም ሻንቆ እጅግ የወረደ ብቃት ታግዞ መረቡ አርፎ አዳማ ከተማን የ 3-2 ድል እንዲቀዳጅ አስችሎታል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የመቻሉ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ሁለት የተለያዩ አጋማሾችን ማሳለፋቸውን እና በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻሉ እንደነበሩ እና አይጠቀሙባቸው እንጂ በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠራቸውን ሲናገሩ ጨዋታው የተወሰነ ኃይል የተቀላቀለበት እንደሆነ እና ዳኛውም ጨዋታውን ተቆጣጥረውታል ብለው እንደሚያስቡ ሲናገሩ ድል የቀናቸው የአዳማ ከተማ አሰልጣኝ ይታገሡ እንዳለ በበኩላቸው ያደረጓቸው ቅያሪዎች ትክክል እንደነበሩ እና ግብ ካገቡ በኋላ ትኩረት ማጣታቸውን ሲገልጹ ያሳኩት ነጥብም ወደ ላይ ለመጠጋት ወሳኝ መሆኑን ሲናገሩ ግብ ያስቆጠሩት ታዳጊዎች ያደረጉትን እንቅስቃሴ አድንቀዋል።

\"\"