ሪፖርት | ዐፄዎቹ ከመመራት ተነስተው አሸንፈዋል

የኦሴይ ማዉሊ ሁለት ግቦች ፋሲል ከነማ ወላይታ ድቻን 2-1 እንዲረታ አድርገዋል።

በጨዋታው ጅማሮ ኦሴይ ማዉሊ በግራ መስመር ከበዛበህ መለዮ የደረሰውን ኳስ ሳጥን ውስጥ በሞከረበት ቅፅበት ወደ ግብ መድረስ የቻሉት ፋሲል ከነማዎች ጥሩ አጀማመር ነበራቸው። የተሻለ የኳስ ቁጥጥር በመያዝ በመስመሮች በኩል አድርጎ ተደጋጋሚ የማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር ይሞክር የነበረው ቡድኑ እንዳሳየው ብልጫ የወላይታ ድቻን የመከላከል አደረጃጀት ደጋግሞ መስበር ባይችልም ቀጣዩን ለግብ የቀረበ ሙከራ 13ኛው ደቂቃ ላይ አድርጓል። ዓለምብርሀን ይግዛው ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ኦሴይ ማዉሊ ጥሩ አድርጎ በግንባር ገጭቶት ቢኒያም ገነቱ በተመጣጣኝ ቅልጥፍና አድኖበታል።

ወላይታ ድቻዎች በእንቅስቃሴ ብልጫ ቢወሰድባቸውም ክፍተቶችን በቀላሉ ባለመስጠት በሚያገኙት አጋጣሚ ደግሞ በፈጣን ሽግግር እንዲሁም በረጅሙ ከተከላካዮች ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል። በዚህም 23ኛው ደቂቃ ላይ ቃልኪዳን ዘላለም ከረጅም ርቀት ቅጣት ምት ካደረገው ሙከራ አምስት ደቂቃዎች በኋላ ቢኒያም ፍቅሩ በዘላለም አባቴ አማካይነት ጥሩ የግብ ዕድል አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። የቡድኖቹ ፉክክር ፈጠን ባሉ ሽግግሮች ታጅቦ በቀጠለበት ሁኔታ 39ኛው ደቂቃ ላይ የዕለቱ አርቢትር ቢኒያም ወርቅአገኘው ሚኬል ሳማኪ ቢኒያም ፍቅሬ ላይ ጥፋት በመስራቱ የሰጡትን ፍፁም ቅጣት ምት ቃልኪዳን ዘላለም በማስቆጠር ወላይታ ድቻን መሪ አድርጓል።

ፋሲል ከነማዎች በደቂቃዎች ልዩነት በድቻ ተከላካዮች ስህተት መነሻነት ተፋሰ ሰለሞን እና ሽመክት ጉግሳ ተጋግዘው ባስገኙት ዕድል ኦሴይ ማዉሊ ጥሩ የማግባት አጋጣሚን ቢያገኝም ጠንካራ ያልነበረ ሙከራው በግቡ ቋሚ ተመልሶበታል ። እስከአጋማሹ ፍፃሜም ፋሲሎች በጨዋታው ቀዳሚ ደቂቃዎች የነበረቸውን የበላይነት መልሰው በማግኘት ከፍ ባለ የማጥቃት ጫና ቢጫወቱም የአቻነታን ግብ ሳያገኙ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ፋሲሎች ካቆሙበት በመቀጠል ወደ ወላይታ ድቻ ሜዳ አመዝነው የማጥቃት ጫናቸውን ቀጥለዋል።

\"\"

በአንፃሩ ወላይታ ድቻዎች ይበልጥ ወደ ግባቸው ተስበው መከላከል በመምረጣቸው ፋሲሎች 58ኛው ደቂቃ ላይ ከዕረፍት መልስ ተቀይሮ የገባው አስቻለው ታመነ ከረጅም ርቀት ያደረሰውን ኳስ በዛብህ መለዮ ሳጥን ውስጥ በቀጥታ ሞክሮ ለጥቂት ከወጣበት አጋጣሚ በፊት አደገኛ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም።

ወደ መከላከሉ ያመዘኑት ድቻዎች ፈጣን ሽግግሮቻቸው ከዕረፍት መልስ ደብዘዝ ብለዋል። ቡድኑ በተሻለ መልኩ 61ኛው ደቂቃ ላይ በቁጥር በዝቶ ጥሩ የመልሶ ማጥቃት ዕድል አግኝቶ ወደ ሙከራነት መቀየር ሳይችል ቀርቷል። ይልቁኑም ፋሲሎች ተደጋጋሚ ጥረታቸው ሰምሮ 68ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ዓለምብርሀን ይግዛው ከቀኝ መስመር ጥሩ አድርጎ ያሻገረውን ኳስ ኦሴይ ማዉሊ በግንባር በመግጨት ነበር ጎል ያደረገው።

ጨዋታው ወደ አቻ ከመጣ በኋላ በሁለቱም በኩል ጥሩ የማጥቃት ምልልስ ተስተውሏል። ለአብነትም 77ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ሰለሞን ከድቻ ተጫዋቾች የቅብብል ስህተት መነሻነት የግል ክህሎቱን ተጠቅሞ ከሳጥን ውስጥ ያደረገው ሙከራ በቢኒያም ገነቱ ከዳነበት ሰከንዶች በኋላ ወላይታ ድቻዎች በፈጣን ጥቃት በፋሲል ቀኝ ሳጥን ውስጥ ተገኝተው ሚኬል ሳማኪ ከቢኒያም ፍቅሬ ቀድሞ ኳስ ያወጣበት ቅፅበት ይጠቀሳል። ይህ ግለት ሳይበርድም ዐፄዎቹ መሪ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። 81ኛው ደቂቃ ላይ ኦሴይ ማዉሊ ከናትናኤል ገብረጊዮርጊስ የደረሰውን ኳስ በድቻ ተከላካዮች ፊት ራሱን ነፃ አድርጎ በመምታት ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ቀሪዎቹ ደቂቃዎች ጨዋታው ተቀዛቅዞ የቀጠለባቸው ሆነው ጨዋታው በፋሲል ከነማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ ተመርተው ማሸነፋቸው ትልቅ ነገር መሆኑን የገለፁት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከጎል ሙከራዎች አንፃር የሚያስቆጥሯቸውን ጎሎች መጨመር እንዳለባቸው አንስተው ኦሴይ ማዉሊን በማድነቅ ከአዲሱ አጥቂያቸው ከዚህ በላይ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል። አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም በበኩላቸው የተጫዋቾቻቸውን የመጀመሪያ አጋማሽ እንቅስቃሴ አድንቀው በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ኋላ መሸሻቸው እና ውጤት አለማስጠበቃቸው ከልምድ ማነስ የመነጨ መሆኑን በማንሳት ዕድሎችን መጠቀምም እንደነበረባቸው ጠቁመዋል።

\"\"